Saturday, 22 February 2025 11:27

ዘመናችን የሐሳቦች ግርግር የነገሠበት ዘመን ነው፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

የተበጣጠሱ ሐሳቦችን እርስ በርስ የሚያስተሳስር ማዕቀፍ እየደበዘዘ የጠፋበት ዘመን ላይ ነን።
የተበታተኑ የሰው ፍላጎቶችና ተግባራትም መልክ አጥተዋል። በቅደም ተከተልና በእርከን የሚያሰናስል ማዕቀፍ የላቸው። የዕለት ተዕለት ተግባራት ሁሉንም ከሚያቅ የኑሮ ዓላማና መርሕ ጋር የተፋቱበት ነው - ዘመኑ።
የተተበተቡ የስሜትና የባህርይ ዓይነቶችን የሚያሰባስብና የሚያስተካክል፣ ቅጥ የሚያስይዝና በኅብር የሚያዋሕድ መንፈስ ከዘመናችን ሕይወት ርቋል። የዘመናችን የሰው ማንነት የዘፈቀደ መረን ነው። ወይም ደግሞ በዘርና በሃይማኖት፣ በሀብትና በጾታ ልዩነት እያቧደነ የመንጋ ማንነትን እየሰበከ የግል ማንነትንና የእኔነት መንፈስን የሚደመስስ የማንነት ቀውስ ነው።
የሕይወትን ትርጉምና ጣዕም የሚያጠፋ የማንነት ቀውስ የዘመናችን ወረርሽኝ ነው።
የግል ማንነትን የሚቀርጽ፣ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል በሁሉም ጉዳይ ላይ የሚሠራ የሥነ ምግባር መርሕ የለም የሚል አስተሳሰብ የነገሰበት ዘመን ላይ ነው።
የብቃት ከፍታንና የሰብዕና ጥንካሬን በምሳሌነት ሊያሳዩ የሚችሉ አርአያዎች እንደ ቁምነገር የማይታዩበት ዘመን ነው። እንደ ንጋት ኮከብ፣ እንደ ማነጻጸሪያ፣ እንደ ምኞትና እንደ ራዕይ መንፈሳችንን የሚገዛ፣ ሕይወታችንን የሚቃኝ፣ በሙሉ ሐሳብና በሙሉ ልብ፣ በአድናቆትና በፍቅር ቀና ብለን የምናየው የክብር ከፍታ፣ የፍጽምና ጉልላት፣ የልዕልና ጫፍ ከምናባችን የደበዘዘበት ዘመንም ነው።
በአጠቃላይ የብተና ወይም የመፍረክረክ ዘመን ላይ ነን ማለት ይቻላል - the age of fragmentation, disintegration።

የምዕተ ዓመታት ማዕቀፎች - ዕውቀት ወይስ እምነት? ሳይንስ ወይስ ሃይማኖት?
ለአራት ለአምስት ሺ ዓመታት… በተለይም ባለፉት ሦስት ሺ ዓመታት፣ ሐሳቦችን በቅጡ እያመሳከሩ፣ እያጣሩና እያስተካከሉ ሥርዓት ለማስያዝና ለማሳደግ የተለያዩ የአስተሳሰብና የእምነት ማዕቀፎች ተሞክረዋል።
ሁሉንም ነገር በሳይንሳዊ ዘዴ መምራት፣ በዕውቀት መንገድ መቃኘት ይቻላል የሚል ማዕቀፍ በበርካታ አገራት የተስፋፋበት ዘመን ታይቷል። የኢንላይትመንት (የአብርሆት) ዘመን፣ የሪዝን (የአእምሮ) ዘመን፣ የሊበራሊዝም (የግል ነጻነትና የሕግ የበላይነት) ዘመን የሚሉ ስያሜዎችን መጥቀስ ይቻላል። ዕውቀት ኃይል ነው፤ ሳይንስ ዓለምን ያድናል ብለው የተናገሩት የእንግሊዝና የፈረንሳይ ፈላስፎችንም ታስታውሱ ይሆናል - ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት።
ለፍልስፍናና ለዕውቀት ከፍተኛውን ቦታ የሚሰጥ ዘመን በጥንታዊው የግሪክ ስልጣኔ ላይ ለሁለት ለሦስት መቶ ዓመታት ታይቷል።
ጥንታዊቷ ንግሥተ ሳባ ደግሞ፣ ከሁሉም ነገር ጥበብ ይበልጣል የሚል የመርሕ ማዕቀፍ እንደነበራት ተተርኳል።
የሰዎች ሐሳብና ተግባር፣ ባሕርይና የግል ማንነት፣… የሰዎች ግንኙነትና ባሕል፣ የመንግሥት መዋቅርና የአገር ሕግ ሁሉ በዚሁ የጥበብ ወይም የዕውቀት ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተቱና የተቃኙ መሆን አለባቸው እንደማለት ነው - የሥልጣኔ ማዕቀፍ።
በሌላ ዘመን ደግሞ፣ ሃይማኖት ሁሉንም ነገር መምራት መቃኘት አለበት የሚል እምነት በእጅጉ ሲስፋፋ ታይቷል። የሕይወት ገጽታዎች በሙሉ ሁሉ የሃይማኖት ተገዢ ለማድረግ በሁሉም አገራት ተሞክሯል ማለት ይቻላል።
ትምህርትና ሳይንስ፣ ባህልና ኪነ ጥበብ፣ የመንግሥት ሥርዓትና ሕግ፣ የሰዎች የዕለት ውሎና አዳር ሁሉ በሃይማኖት ስር እንዲሆን ለብዙ ዘመናት ሰፋፊ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። አለበለዚያ እንደጠላት ይታያሉ። ጠላት ተብለው የማይወገዙት፣ ተገዢ ከሆኑ ብቻ ነው። ሳይንስና አእምሮ የሃይማኖት አገልጋይ መሆን አለባቸው የሚሉ አባባሎችን መጥቀስ ይቻላል።
ሁሉም ነገር የሃይማኖት ተገዢ ባይሆንም እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ ከሃይማኖት ጋር የተጣጣመ ቅርጽ እንዲይዝ ሲደረግ ነበር - በየዘመኑ በየአገሩ። የሁሉም ነገር ምንነትና ቦታ፣ ፋይዳና ክብር የሚመዘነው በሃይማኖት ዓይን ይሆናል። በሃይማኖት ማዕቀፍ ውስጥ፣ በሃይማኖት ልዕልና ሥር።

የማስታረቅ ወይም የማዳበል ማዕቀፍ
ሃይማኖትን ከሳይንስና ከእውቀት ጋር ለማስታረቅ ወይም ለማጎዳኘት የሚደረግ ሙከራ አዲስ ነገር አይደለም። ለረዥም ዘመናት ተሞክሯል።
የሃይማኖት ምክሮችን ከነባር ታሪክና ባሕል ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን ከመንግሥት ሕግ ጋር እንደ አቻና እንደ አማራጭ እንዲታዩ ለማድረግ ብዙዎች ጥረዋል።
ሥነ ምግባራዊ፣ መንፈሳዊና ሰማያዊ ጉዳዮች በሃይማኖት ግዛት ሥር፣
የእውኑ ዓለም ዕውቀት፣ የኑሮ መተዳደሪያ ሥራ፣ ምድራዊ የሰዎች ግንኙነቶችና ጉዳዮች ደግሞ፣ በሳይንስ ትምህርትና በመንግሥት ሕግ ሥር መሆን አለባቸው በሚል የሐሳብ ማዕቀፍ የተመራ ነው - አብዛኛው የሰው ልጆች ታሪክ።
አንዳንዴ የሃይማኖት ግዛት እየሰፋና እየከረረ ይሄዳል። እናም የዕውቀትና የሳይንስ ተቆጣጣሪ ለመሆን ይሞክራል። የኢቮሊሽን ንድፈ ሐሳብ በመማሪያ መጻሕፍት ውስጥ እንዳይገባ ይከለክላል። የሃይማኖት እጅ ሲበረታ፣ የመንግሥትን ሕግ የማርቀቅና ንጉሥ የመሾም ሥልጣን ይኑረኝ ይላል።
የዕውቀትና የሳይንስ እጅ ሲበረታ ደግሞ፣ የሃይማኖት ስብከቶች ከሳይንስ ጋር መጣጣም አለባቸው የሚል ጫና እያየለ ይመጣል። የመንግሥት ጉልበት የጨመረ ጊዜም፣ የሃይማኖት መሪዎችን ለማባረርና ለማሰማራት፣ ለመሾምና ለመሻር ያምረዋል።
እንዲያም ሆኖ፣ የግዛታቸው መጠን ቢሰፋም ቢጠብም፣ ድንበራቸው ቢወፍርም ቢሳሳም፣ የየራሳቸው ግዛት አላቸው የሚለው የሐሳብ ማዕቀፍ ሳይቀየር ለሺ ዓመታት ዘልቋል።
የሃይማኖትና የዕውቀት ወይም የእምነትና የሳይንስ ማዕቀፎች በተናጠል፣ ለተወሰኑ ዘመናት ለየብቻቸው ነግሠዋል። ሁለት የማዕቀፍ አማራጮች ናቸው
ሦስተኛው አማራጭ ማዕቀፍ፣ ዕውቀትንና ሃይማኖትን (ወይም እምነትንና ሳይንስን) ያዳበለ ማዕቀፍ ነው። ለዚያውም ለረዥም ዘመናት የገነነ ማዕቀፍ።
እነዚህ ሦስት ማዕቀፎች፣ ስህተትም ይሁኑ ትክክል፣ ውጤታቸውና መዘዛቸው ቢለያይም፣ አንድ የጋራ ባህርይ አላቸው። በየፊናቸውና በየዘመናቸው፣ “ሁሉን አቀፍ ናቸው” ተብለው ሲታመንባቸው የነበሩ ናቸው። ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ጉዳይ ላይ፣ ሁልጊዜና በሁሉም ቦታ የሚያገለግሉ የአስተሳሰብ ማዕቀፎች ናቸው የሚል መንፈስ አላቸው።
ከእነዚህ የተለዩ ሁለት ማዕቀፎች ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ታይተዋል። ግን ለሁሉም ሰው የሚሰሩ አይደሉም።
ሰዎችን በሀብትና በጾታ፣ በዘርና በቋንቋ የሚያቧድኑ (የሚከፋፍሉ) “ማዕቀፎች”
“የሰዎች ሐሳብና ተግባር፣ ባሕርይና ማንነት፣ በአንድ ማዕቀፍና በአንድ መመዘኛ መታየት አይችሉም፤ እንደ ኑሮ ደረጃው ይለያያል” የሚል የሶሻሊዝም ወይም የኮሙኒዝም የሐሳብ ማዕቀፍ አለ። ለሀብታምና ለድሀ፣ ለጉልበተኛና ለሚስኪን፣ ለባለሥልጣንና ለገባር… ለኢንቨስተርና ለሠራተኛ፣ የየራሳቸው የተለያየ የሐሳብ ማዕቀፍ ይኖራቸዋል እንጂ፣ ሁሉንም የሚያካትት “እውነተኛ ማዕቀፍ” የለም እንደ ማለት ነው።
የሰው ሐሳብ እንደ የአገሩና እንደ የባሕሉ ይለያያል የሚል የናሽናሊዝም የሐሳብ ማዕቀፍ ደግሞ አለ። የጀርመኖች ሳይንስ ከእንግሊዞች ሳይንስ ይለያያል እንደማለት ነው። ኬሚስትሪ የሚል የዕውቀት ማዕቀፍም፣ የጣሊያን ኬሚስትሪና የፈረንሳይ ኬምስትሪ ተብሎ መለየት ሊኖርበት ነው። ለነጮችና ለጥቁሮች አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር መርህ ሊኖራቸው አይችልም፤ ተገቢ አይደለም እንደማለት ነው።
በአጭሩ፣ ሁሉንም የሚያካትት “እውነተኛ ማዕቀፍ የለም” የሚል ነው መደምደሚያው።
የሐሳብ ብዝኃነት ወይስ መርሕ አልባነት
በኑሮ ደረጃና በአገር ተወላጅነት የሰውን ተፈጥሮ መሸንሸን የጀመሩት የሶሻሊዝምና የናሽናሊዝም ቅኝቶች፣ በዚያው አላበቁም።
የሴቶችና የወንዶች፣ የከተሜና የገጠሬ፣ የፋብሪካ ሰራተኛና የገበሬ፣ የአካል ጉዳተኞችና የእናቶች፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች፣ የዚህኛው ቋንቋና የዚያኛው ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ የዕፅዋት አፍቃሪዎችና የእንስሳት ተቆርቋሪዎች፣ የስደተኞችና የነዋሪዎች… ሁሉም በየጎራው የየራሱ የሐሳብ ማዕቀፎች ሊኖሩት ይገባል የሚል “የሐሳብ ብዝኃነትን” የሚሰብክ ቅኝት ተስፋፍቷል።
እንዲያውም፣ ለአንድ ሰው ትክክል የሆነ ለሌላኛው ሰው ስህተት ይሆናል፤ ስለዚህ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል ማዕቀፍ የለም ይላሉ።
አምና ጠቃሚ የነበረ ዘንድሮ ጎጂ ሊሆን ይችላል፤ ለታች ሰፈር የሚጣፍጥ ሐሳብ ለላይ ሰፈር መራራ ይሆንባቸዋል፤ እናም ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ ትክክለኛ የሆነ የሐሳብ ማዕቀፍ ወይም የሥነ ምግባር መርሕ ሊኖር አይችልም ይላሉ።
ስርቆትና ንጥቂያ፣ ድብደባና ግድያ… እልፍ አእላፍ ድርጊቶች የሚያጠቃልሉና “ወንጀል” በሚል ሥያሜ ሥር የሚካተቱ ሐሳቦች መሆን የለባቸው የሚሉም ሞልተዋል። እያንዳንዱ ተግባር በየፊናው እንደሚለያይ፤ ምንነቱና ትርጉሙም እንደየ ተመልካቹ ለየቅል እንደሆነ ይሰብካሉ። “የጥፋት ተግባር” ወይም “የወንደል ድርጊት” ብለን ልንጠቀልላቸው አይገባም ይላሉ።
የሰዎች እይታና ስሜት ይለያያል፤ እንደየ ጎራቸው፣ ወይም እንደየ ግል ስሜታቸው በተለያየ ሐሳብ የተለያየ ስያሜ መጠቀም ይችላሉ ብለው መረን ይለቁታል።
የሁሉንም ስሜት ያከብራል የተባለለት የሐሳብ ብዝኃነት፣ እንዲህ እየተተረተረና እየተሰነጣጠቀ… መያዣ መጨበጫ አጥቷል።
የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የሰዎችን ፆታና ብዛት የሚጠቁሙ፣ “አንተ” እና “አንቺ”፣ “እናንተ” የመሳሰሉ ቃላትን እንደተለመደው መጠቀም አይቻልም ብለው አዳዲስ ደንቦችን ሲያወጡ የነበሩት በዚህ ምክንያት ነው።
አንዱ ተማሪ “እናንተ” ብላችሁ ጥሩኝ፤ “አንተ” አትበሉኝ ማለት ይችላል። ምርጫውንና ስሜቱን ካላከበራችሁና “አንተ” ብላችሁ ብታናግሩት አስተዳደራዊ ቅጣት ይጠብቃችኋል። ሴቷ ተማሪም እንደምርጫዋ ነው።
“አንቺ” የሚል ቃል መምረጥ ትችላለች። “አንተ” ብላችሁ ጥሩኝ ማለትም ትችላለች። ምርጫዋንና ስሜቷን ያላከበረ ሰው፣ የእርማት ወይም የባሕርይ ማስተካከያ ሥልጠና እንዲከታተል ይወሰንበታል። እምቢ ካለ፣ ሊባረር ይችላል።
በዚህ ወር ነው እንዲህ አይነት “የብዝኀነት ደንቦች” በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ የተሻሩት። ሙሉ ለሙሉ አልተሻሩም። ዶናልድ ትራምፕ የዩኒቨርስቲዎችን ደንብ በቀጥታ መሰረዝ አይችሉም። በተዘዋዋሪ ግን ጫና ይፈጥራሉ። “የብዝኃነትን ደንብ” ያልሰረዙ ዩኒቨርስቲዎች ከመንግሥት የሚያገኙት የምርምር ድጎማ እንዲቋረጥባቸው ወስነዋል - ፕሬዚዳንቱ።
ዩኒቨርስቲዎች ድጎማ እንዳይቋረጥባቸው፣ “የብዝሃነት ደንቦችን” ለጊዜው እየሰረዙ ነው። ነገር ግን፣ “አንተ” የሚለው ቃል ለወንድ፣ አንቺ ደግሞ ለሴት፣ እናንተ ለብዙ ሰዎች የሚያገለግሉ ቃላት ናቸው በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። እንዲህ አይነት የሐሳብ ማዕቀፍ በሁሉም ቦታ ለሁልጊዜ ያገለግላል ብሎ ማሰብ ከጭቆና አስተሳሰብ የሚመነጭ ስሜት ነው ይላሉ። አንድ የሐሳብ ማዕቀፍ በሁሉም ሰው ላይ “መጫን” የሰውን ክብር የሚነካ አምባገነንነት ነው ብለው ይወቅሳሉ።
“አንተ”፣ አንቺ እና እናንተ” የሚሉ ቃላት ለእያንዳንዱ ሰው የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ይገባል ባይ ናቸው። እናንተ ብላችሁ ጥሩኝ ስትል የነበረች ተማሪ፣ ነገ ወይም ከነገወዲያ ስሜቷ ተቀይሮ “አንተ” ብትሉኝ እመርጣለሁ ልትል ትችላለች ማለት ነው።
ለነገሩ ይሄ ላይገርም ይችላል። ካናዳን ጨምሮ በርካታ አገራት፣ የፓርስፖርት ላይ እያንዳንዱ ሰው እንደየ ምርጫው “ሴት” ወይም “ወንድ” ወይም “ሌላ” ብሎ ማስመዝገብ ይችላል የሚል “የብዝኃነት ሕግ አውጥተዋል። ለምን እንደሆነም ምክንያታቸውን ገልጸዋል።
ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚያገለግል “የጾታ መመዘኛ” የለም ባይ ናቸው። የተፈጥሮ እውነታስ? የተፈጥሮ እውነታ በተጨባጭ እንደሌለና እንደተመልካቹ እንደሚታይ በማብራራት ምላሽ ይሰጣሉ። “የተፈጥሮ እውነታ” የሚሉት ነገር በተጨባጭ ቢኖር እንኳ፣ በተመልካች ላይ የሚያሳድረው ስሜትና ለተመልካች የሚኖረው ትርጉም እንደየ ሰዉ ይለያያል ይላሉ።
ያሁኑ ዘመንና ያለንበት ዓለም ከቀድሞዎቹ ዘመናትና ታሪኮች ጋር የቱን ያህል የተለየ እንደሆነ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል። የድሮዎቹ ዐዋቂዎችና አስተማሪዎች፣ ምሁራንና ሰባኪዎች፣ ቢከፋም ቢለማም፣ “የሐሳብ ማዕቀፍ” ነበራቸው። ወይም ሊኖረን ይገባል ብለው ያምኑ ነበር። የዛሬዎቹ ብዙ ዐዋቂዎችና ምሁራን ግን፣ “የሐሳብ ማዕቀፍ” እንዳይኖር የሚሰብኩ፣ “ነባር የሐሳብ ማዕቀፎችን ማፍረስ” እንደዋነኛ የአብዮት ትግል የሚቆጥሩ ናቸው።

Read 270 times