ከአንገቱ በላይ… “በጥቀርሻ ጉም የተሸፈነው የቱርኪሚርክ ተራራ”… ያደፈጠ አውሬ ይመስላል። በድብቅ ሳይሆን በግላጭ ያደፈጠ። ጉሙ ቢገለጥና ጭንቅላቱ ቢታይ ደግሞ አስፈሪነቱ ይብስበታል ብለው ያስባሉ - የራቶስ ከተማ ነዋሪዎች። የተከፈተ አፍ ሊኖረው ይችላል። በጣም የሚያስጨንቃቸው ግን፣ ጭንቅላት ባይኖረውስ የሚለው ስጋት ነው።
ከተማዋ መፈናፈኛ እንዳታገኝ ዙርያዋን የከበበ የእስር ቤት ግንብ ነው - ተራራው። ከእግሩ ሥር ቁልቁል በአይነ ቁራኛ የሚጠባበቅ አውሬም ይመስላል። የከተማዋ ነዋሪዎች አሁንም አሁንም ቀና ብለው ሽቅብ ያዩታል። ሁሌም ስለተራራው ያስባሉ። በሕልማቸውም በውናቸው ከአእምሯቸው አይጠፋም። ግን ሐሳባቸውንና ቅዠታቸውን በግልጽ አያወሩም።
በጥቀርሻ ጉም ከተሸፈነው አናት በታች የዝገት ክምር የመሰለ መልክ አለው። ሲነሳበት ግን መልኩና ቀለሙ ይለዋወጣል። በቁጣ ይንቀጠቀጣል። ሬንጅ የመሰለ ጅራት ያወጣል፡ መርዛማ ጭስ እየለቀቀ በከተማዋ ላይ ብናኝ ያርከፈክፋል።
ዶይቃዊው ንጉሥ ከሥልጣኑ በተባረረበትና አገር ጥሎ በጠፋበት ጊዜ ነው የተራራው ባህርይ የተቀየረው ይላሉ - ገሚሶቹ። ተለዋዋጭ መልክና አመል ያመጣው በዚያችው ዕለት እንደሆነ ይተርካሉ። ታሪክ ተበላሸ ብለው የድሮውን ይናፍቃሉ። ያልሠራነው ገድል፣ ያልሮጥንበት ዳገት የለም ብለው ይናገራሉ። ታሪክ ሁሉ ተፈጽሞ የተጠናቀቀ፣ ከእንግዲህም ማሰብና መስራት የማያስፈልግ ይመስል።
ገሚሶቹ ግን ተራራው ከነ ባህርይው ድሮም የነበረ ነው ብለው ይተማመኑበታል። ተለዋዋጭነቱ ባይጨበጥላቸውም፣ በጥቀርሻ ጉም ቢያጨልምባቸውም፣ ይሻለናል ይሉለታል።
ሌሎች እንደሚተርኩት ከሆነ ግን፣ ከሌሎች ተራሮች የተለየ ባህርይ አልነበረውም። እንዲያውም አፈጣጠሩና ተለዋዋጭ አመሉ ድንገተኛ ክስተት ነው። ከዕለታት አንድ ቀን፣ በድንገት ንጉሡ ጠፋ፤ በድንገት ተራራው ተከሰተ - ከተለዋዋጭ አመል ጋር።
(የሌሊሳ ግርማ አዲስ የረዥም ልብወለድ ድርሰት በእንዲህ ዓይነት ትረካ ነው መጽሐፉን የሚጀምረው፡፡ ማራኪ የፋንታሲ ዘይቤ ነው፡፡ ግን ምናባዊ ዓለም ብቻ አይደለም፡፡ የዛሬ የዘመናችን የዚህችው የዓለማችን ገፅታና መንፈስ ለማሳየት የተወጠነ ድርሰት ነው፡፡)
በራቶስ ነዋሪዎች ዘንድ የተለያዩ ወሬዎችና የተምታቱ ሐሳቦች ቢበዙ ላይገርም ይችላል። የለውጥ ዘመን ላይ የሐሳቦች ግርግር ይፈጠራል። ሲያስለቅሱ የነበሩ አስጨፋሪ፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ። የታችኞችም የበላይ። ተራራው ተንዶ ሜዳ ይሆናል፤ ሸለቆው አብጦ ተራራ ያክላል። የሐሳቦች መልክዓ ምድር ይለዋወጣል። ነገሮች በፍጥነት ይሾራሉ።
እንደ ጥንቱ ቢሆን፣ በለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጊዜያዊ የሐሳቦች ግርግር፣ ውሎ አድሮ ይረጋጋል። መልክ ይይዛል። የዛሬው ዓለም ግን ከጥንቱ ይለያል። በመላው ዓለም የሚታየው የዘመናችን የሐሳቦች ግርግር፣ ጊዜያዊ የሽግሽግ ሆይሆይታ ወይም የሽግግር ሁካታ አይደለም።
አንድ የሐሳቦች ማዕቀፍ በብጥብጥ ደፍርሶ፣ ሌላ የተጣራና የተንጣለለ የሐሳቦች ማዕቀፍ አይፈጠርም። ነባሩ ተደፍቶ በቦታው ሌላ አዲስ ተተክቶ አያድርም። የፈራረሱት ጠጠሮች፣ የተበታተኑት ነጠብጣቦች እንደገና በአዲስ መንገድ እንዲሰባሰቡ፣ ሥርዓት እንዲይዙና ምስል እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚችል ወይም የሚፈልግ የለም።
የጠጠሮች ክምችትና የነጠብጣቦች ትርምስ ነው የዘመናችን ግብ። ጠጠሮችን አዋቅሮ ወደ ቅርጽ ማድረስ፣ ነጠብጣቦችን አገናኝቶ ወደ መስመርና ወደ ምስል ማሸጋገር ድሮ ቀረ ተብሏል። ወይም እንደ ኋላቀርነት ተቆጥሯል።
ይህን የዘመናችንና የዓለማችንን መንፈስ ለመግለጽና ለማሳየት የሚሞክር ድርሰት ይመስላል - የሌሊሳ ግርማ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ።
“በታችም በምድር” በሚል ርዕስ ከሰሞኑ ለሕትመት የበቃው ድርሰት፣ የዘመናችንን የሐሳብ ግርግር በማሳየት ብቻ አይመለስም።
በሐሳቦች ግርግር በታመሰው ዓለም፣ የዓለማ አቅጣጫ በተምታታበት ቅብዝብዝ፣ በማንነት ቀውስ እየታመሰ ትርጉም ባጣ ሕይወት ውስጥ፣ ነጠብጣቦችን ሁሉ የሚጠቀልል ትልቅ ነጥብ የማግኘት ውጣ ውረድን ይተርካል - ድርሰቱ።
በኤሎምና በወላጆቹ ታሪክ።
ተወርዋሪ ኮከብ በመሰለው በኤሎምና በሃቴሉ የፍቅር ብልጭታ።
በተለይ ደግሞ በጠመዝማዛው የኤሎምና በአብነር ታሪክ።
እንደ ደቀ መዝሙርና እንደ መምህር ሆኖ የተጀመረው የኤሎምና የአብነር ታሪክ ወደ ሰማይ ለመምጠቅ ይምዘገዘጋል። የመምጠቂያ ጉልበቱ “እምነት” የተሰኘ ኃይል ነው። እየበረከተ እየበረታ የሚሄድ ኃይል ነው? ወይስ አላቂ ነዳጅ? ከምድር ከራቀ፣ ከዓለም ስበት ከተላቀቀስ ምን መተማመኛ ይኖረዋል?
እምነትን እያቀጣጠለ የሚምዘገዘገው የደቀ መዝሙርና የመምህር ግንኙነት፣ ሲብሰለሰል በቆየ ምክንያት ሳቢያ፣ ቁልቁል ገደል መግባት ይቀርለታል? ወደ ልዩነትና ወደ ተቀናቃኝነት ከመቀየር ይድናል?
ኤሎች የዘመናችንን የሐሳብ ግርግር አደብ ማስገዛት፣ ፍሬና ገለባውን ማጣራት፣ ትክክለኛ ሐሳቦችን በአንድ ማዕቀፍ መልክ ማስያዝ የሚቻለው፣ በሃይማኖት ወይም በእምነት አማካኝነት ነው ማለት ጀምሯል።
ዓለማ የጠፋበት አሰልቺ የመቅበዝበዝ ኑሯችን የሚፈወሰው፣ ዘላለማዊ እውነትን የምናገኘው እንዲሁም ዘላለማዊ የሥነምግባር መርህን የምንጨብጠው በሃይማኖት ነው የሚል ሆኗል እምነቱ።
ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው፣ ቅዠት ከመሰለው የማንነት ቀውስ የምንድነው፣ የሕይወትን ክብር ለማጣጣም የምንችለው፣ በእምነት እንደሆነ (የክብር አናት፣ የፍጽምና ጫፍ፣ የመልካምነት ከፍታን በማምለክ) እንደሆነም ያምናል። ይህን የማገኘው በሃይማኖት በእምነት ነው ይላል።
የሰው ልጅ በሐሳብ ግርግር የሚቃዠው፣ በዓላማ ቢስነት የሚቅበዘበዘው፣ ትርጉም ባጣ ሕይወት የሚባክነው… እምነትን በማጣት ነው እንደማለት ነው።
ለተበጣጠሱ ሐሳቦች አሰባሳቢ ማዕቀፍን፣ ለተበታተኑ የኑሮ እርምጃዎች የጉዞ መስመርን፣ ለተቃወሰ ማንነት ከውረደት ወደ ከፍታ የሚያመላክት የክብር ሰገነትን ማበጀት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብና ለዚህም በጽናት መነሣት ትልቅ ቁምነገር ነው።
ሁሉንም ጉዳይ፣ ሁሉንም የሕይወት ገጽታ የሚያካትትና የሚያስተሳስር፣ ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚያገለግል የሐሳቦች ማዕቀፍ ከሌለን፣ መውጫ በሌለው አዙሪት ቁልቁል እንወርዳለን፡፡ ሐሳባችንም፣ ኑሮና ተግባራችንም፣ የግል ባህሪያችንና መንፈሳችንም ሁሉ በቅዠት እየተዋጠ እንደሚሄድ የሚመሰክር ነው - የዘመናችን አዝማሚያ።
ነገር ግን፣ የዚህ ሁሉ ችግር መንሥኤ የሃይማኖት ወይም የእምነት እጦት ነው ወይ? ችግር የሚደርስብንስ ከእምነት ስለተራራቅን ነው ወይ?
መፍትሔውስ ራሳችንን ለእምነት ማስገዛት ብቻ ነው?
በእርግጥ እምነት መያዝና መጽናት ቀላል ነገር እንዳልሆነ በኤሎም ሕይወት ተተርኳል። ከቤተሰብና ከወዳዶች ጋር የመጣላት ፈተና ይመጣበታል። በሐሰት የሚወነጅሉና የሚያሳድዱ ይነሡበታል። የጠረጠሩት እርግጠኛ ሆነው ይመሰክሩበታል። ያመናቸው ይክዱታል።…
እምነት ለብዙ ችግር ይዳርጋል፤ ያመነ ፈተና ይበዛበታል ያስብላል - ነገሩ።
ግን ደግሞ፣ ችግርና ፈተና የሚበረታው እምነት በሌላቸው ሰዎች ላይ እንደሆነ፣ እምነት የችግሮች መፍትሔ እንደሆነም ይናገራል።
እምነት ችግሮችን ይጠራል ወይስ ችግሮችን ያባርራል? በሁለቱም አቅጣጫ የተምታቱ ሐሳቦችን እየያዘ ይሆን እንዴ?
በኤሎም ታሪክ ሲነሡ ካየናቸው ጥያቄዎች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ግን ገና ብዙ አስቸጋሪ ጥያቄዎችንም ሸውዶ ማለፍ አይችልም፡፡
ከ40 በላይ ሃይማኖቶችን በያዘች ከተማ ውስጥ ነው የሚኖረው። እርስ በርስ “መናፍቅ” እየተባባሉ ይወጋገዛሉ።
የትኛው ሃይማኖት ወይም የትኛው እምነት ነው ትክክል?
የሱ እምነት ከሌሎቹ እምነቶች በምን ይበልጣል?
ማስረጃ ልዘርዝር፤ ማረጋገጫ ላቅርብ ካለ… ጉዳዩ የዕውቀት ጉዳይ ይሆናል። ትልቁ ማዕቀፍ ሃይማኖት ወይም እምነት ሳይሆን፣ በማስረጃ የተረጋገጠ ዕውቀት ነው ወደ ማለት ያመራል።
ማስረጃና ማረጋገጫ አያስፈልገኝም፤ የኔ እምነት ከሌሎች እምነቶች እንደሚበልጡ “አምናለሁ”… የሚል ከሆነ ደግሞ… ከሌሎች እምነቶች ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። ሌሎች ሰዎችም ለእምነታቸው ማስረጃና ማረጋገጫ እንደማያሻቸው ይናገራሉ። “የኔ እምነት ከሌሎች እንደሚበልጥ አምናለሁ” እያሉ ነው እርስ በርስ የሚወጋገዙት፤ የሚዘምቱት። ቢያንስ ቢያንስ፣ መናፍቅ ወይም ከሃዲ እያሉ ይሰዳደባሉ።
የኤሎም መንገድ ከነዚሁ ማህበር የተለየና የተሻለ መሆኑን እንዴት ማሳየት ይችላል?
እምነቱ በሚያመጣው ፍሬ? የኤሎምና የተቀናቃኙን ፉክክር በማነጻጸር ይሆን የእምነቱን ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚቻለው?
የኤሎም ፈተና ይህ ብቻ አይደለም። በየአቅጣጫው ከእልፍ ሰዎች አእምሮ እንደ አሸን እየተፈለፈሉ የሚያድሩና አገር ምድሩን የሚያጥለቀልቁ የዓመጽ ሐሳቦችን ማበጠርና ለማዕቀፍ ማስገዛት፣ አገር ምድሩን የሚያዳርሱ የዓመጽ ሤራዎችንና ጥፋቶችን ማሸነፍ ይችላል ወይ? ካልቻለ ፍሬው ምኑ ላይ ነው?
በተለዋዋጭ ዓመል ከተማዋን ከሚያስጨንቃት ከግዙፉ ተራራ ጋር እንደመፋለም ነው - ፈተናው።
ጭንቅላት ይኑረው አይኑረው የማይታወቅ የዘመናችን ተለዋዋጭ የሐሳብ ግርግርን በሃይማኖታዊ እምነት ማሸነፍ እንደማለት ነው።
ከአንገት በላይ በጥቀርሻ ጉም የተሸፈነ፣ መርዛማ ጭስ እየተፋ ብናኙን የሚያርከፈክፍ፣ መልክና ቀለሙን የሚለዋውጥ፣ አገሬውን የከበበ አውሬ ወይም የዝገት ክምር የመሰለ ግዙፍ አመለኛ ተራራ ነው የዘመናችን የሐሳብና የመንፈስ ግርግር።
እና በቅንጣት እምነት ተራራውን “ወግድ” ብሎ መናድና ማባረር ይቻላል?
ድርሰቱን ብታነብቡና ብንነጋገርበት መልካም ይመስለኛል።
አቀራረቡና አጻጻፉ ለንባብ የተመቸ ነው። ትኩረትን በየሚስቡና በሚያስደንቁ ገጸ ባሕርያት የበለጸገ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን የዘመናችንን የሐሳብና የመንፈስ ግርግርን ለማሳየት፣ በዚሁ የትርምስ ዓለም ውስጥ የነባር ትውልድና የአዲስ ትውልድ ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማስቃኘት የሚሞክር ድርሰት ነው።
የመዳኛው መንገድ የኤሎም እምነት ነው ከማለት ጎን ለጎን፣ የፕሮቴስታንት የመሰለ ሃይማኖት ነው መፍትሔው የሚልም ይመስላል።
እንዲህ ከማለት ግን፣ የእምነት አዳኝነት ወይም የሃይማኖት መፍትሔነት ላይ ያተኮረ ድርሰት ቢባል ይሻላል። ግን በትረካው ላይ የምናየው እምነት፣ የእውነት አዳኝ ነው ወይ? የምር መፍትሔስ ነው ወይ?
Monday, 24 February 2025 00:00
ዘመናችንን የሚገልጽ አዲስ ልብወለድ፣ ወደ ‹እምነት‹ ይጠቁመናል! የትኛው እምነት?
Written by Administrator
Published in
ነፃ አስተያየት