Sunday, 23 February 2025 00:00

የማይገናኙ መስመሮች (በመንግሥት ሥራ ላይ የግል ሥራን መደበል)

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(1 Vote)

እንደ መግቢያ
የመንግሥት መዋቅርና በመዋቅሩ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ በርካታ ሠራተኞች ይደንቁኛል፡፡ በእኛ ጊዜ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ዝርዝር (job description) ነበረው፡፡ ባይሆን፣ ሁሉም የሥራ ዝርዝር በመጨረሻ ተመሳሳይ ማሰሪያ አለው - “በተጨማሪም አለቃው የሚሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት ተግባር ያከናውናል” ይልና ይደመድመዋል፡፡
የአሁኑ የመንግሥት ሠራኞች የሥራ ዝርዝር (job description) ይኖራቸው ይሆን? በግልጥ የምመለከተው ነገር አለ፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ የራሱን ገንዘብ ማግኛ መስመር በጉልህ ቀለም አስምሮ፣ የተቀጠረበትን የመንግሥት ሥራና ወንበር ይዞ፣ በመዋቅሩ ውስጥ የያዘውን የሥራ ቦታ ተገን በማድረግ፣ የግል ጥቅም የሚያገኝበትን ሂደት ደግሞ በትይዩ መስመር ለማቀናበር ሲጣደፍ  እመለከታለሁ፡፡
 በመንግሥት መዋቅር ውስጥ፣ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሚከተለው ሌላ የግል ጥቅም መስመር አለው፡፡ እንዴት ልገልጠው እችል ይሆን? በማለት ሳሰላስል ብዙ ቆየሁ፡፡ ሪሰርች (investigative journalism ዓይነት) ይፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ ጋዜጠኛ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ፣ የማቀርበው ጥቅል የሆነውን ኤኮኖሚያዊ ባሕሪውን ነው፡፡
ላይገናኙ የማሉ የሚመስሉ ሁለት ትይዩ መስመሮች ይታዩኛል፡፡ ሁለት ትይዩ መስመሮች ፍጹም የማይገናኙ ሲሆኑ (parallel lines) የየራሳቸውን ባህርያት ነው የሚይዙት (በሂሳብ ትምህርት አንድ ቦታ ሊገናኙ እንደሚችሉ መምህራችን አስተምሮን የነበር ቢሆንም ግን ረሳሁት፡፡ ወትሮም አንድ ትምህርት ከአርባ አምስት ዓመታት በኋላ ተምሬው ነበር ከማለት ውጪ፣ ብዙም አይፈይድም)፡፡ ይረሳል፡፡ “የተረሳ ዕውቀት ደግሞ እንደማይታወቅ ይቆጠራል” ይባላል፡፡
የመንግሥት ግልጽ/ያልተሰወረው መመሪያ፡- እያንዳንዱ ሠራተኛ የተሰጠውን የሥራ ድርሻ ደንበኛውን ሳያጉላላ እንዲያከናውን፣ ሁሉንም እኩል እንዲያስተናገድ፣ ተገልጋዩ በመጣበት ቅደም-ተከተል መሠረት ተራውን ይዞ አገልግሎትን እንዲያገኝ (አቅመ-ደካሞችን ማስቀደም እንደተጠበቀ ሆኖ)፣… በሚሉ ግድግዳ ላይ ደምቀው በተጻፉ ማስታወሻዎች ያጌጠ ነው፡፡ ይህ ያልተሰወረው መመሪያ ነው፡፡
ስውሩን መመሪያ ለማወቅ ደግሞ፣ የእያንዳንዱን ሠራተኛ የአሠራር ባሕሪና የአለቃውን አመራር መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡ ስውሩ መመሪያ የተጻፈው በእያንዳንዱ ሠራተኛ አሰራር/አካሄድ ውስጥ ነው፡፡ ይኸው አሠራር የአለቆች እውቅና ተሰጥቶት የሚካሄድ ይመስላል፡፡ አለቃው ሳያውቅ በሠራተኛው ብቻ የሚፈጸም ደግ ወይም መጥፎ ሥራ የለም ተብሎ ይታመናል፡፡ አለቃ ሳያውቅ በስውር የሚከናወን ሥራ የሚኖር ከሆነ፣ ምንም ተቋማዊ የሆነ የአሰራር ግንኙነት የለም ማለት ነው፡፡
እያደገ የመጣ ጉልህ የአገልግሎት አሰጣጥ መስመር በሠራተኞችና አለቆቻቸው ዘንድ መዘውተሩ በግልጥ ይታያል፡፡ አንዱ ሕጋዊ ሌላው ኢ-ሕጋዊ ነው፡፡ ኢ-ሕጋዊ ያልኩት እኔ ነኝ እንጂ፣ መደበኛ የአገልግሎት መስመር እየሆነ ከመንግሥት የሥራ አፈጻጸም እኩል በትይዩ ተሰልፎ በተፎካካሪነት የሚሠራበት (ሠ ይጠብቃል) ደማቅ መስመር ከሆነ ቆይቷል፡፡ ይህንን ለማወቅ በቀደሙት መንግሥታት ቢሮክራሲ ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል፡፡ በቀድሞ ዘመን፣ አነሰም በዛ፣ የሥራ ዲሲፒሊንና ተጠያቂነት ነበረ ለማለት ነው፡፡ አለቃው የበታቹን የሚቆጣጠርበትና የበታቹም ትዕዛዝን የሚያከብርበት ዘመን እንደነበረ ማመልከት ያለፈን ናፋቂነት አይደለም፡፡ ሐቅ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በያዙት የቢሮ ስፋትና ውበት ካልሆነ በቀር፤ የትኛው የመንግሥት ሠራተኛ አለቃ፣ የትኛው ደግሞ ምንዝር እንደሆነ መለየት ያስቸግራል፡፡ አለቃው፤ ከሥራ ገበታቸው ላይ እየተነሱ ከአንዱ ዴስክ ወደ ሌላው፣ ከክፍል ወደ ክፍል የሚሯሯጡትንና የግል ሥራ ለመሥራት የሥራ ቦታቸውን ለቀው ውጪ የሚውሉትን ሠራተኞች እያየ እንዳላየ ዝም ብሎ ሲሞዳሞድ ታገኙታላችሁ፡፡ በተለይ የመሬት፣ የቤት ፕላን፣ የግንባታ ፍቃድና የውኃ ክፍሎችን አስመልክቶ የተሰማሩ ሠራኞች ሆድ ይፍጀው ማለት ብቻ ነው፡፡ የለም የሥራ ባህሪው ውጭ ወጥቶ ማየትንና መሥራትን የግድ ይላል ሊባል ይችላል፡፡ የአገልግሎት ጥያቄን በጥያቄ ተሞግቶ የተጉላላና እንግልት የደረሰበት ባለጉዳይ ያውቀዋል፡፡ “ተከድኖ ይብሰል” ይሉ ነበር ሆዳቸውን ጉዳይ የበላባቸውና አቤቱታ ይበልጥ እንደሚያስጠቃ የገባቸው አባቶች፡፡ “ሆድ ይፍጀው”፣ “ተከድኖ ይብሰል”፣ “ዝምታ ወርቅ ነው”፣ … የሚሉት ሥነ ቃሎች በከንቱ አልተነገሩም፡፡ አቤት የሚሉበት ባለመኖሩና ፈራጅ ያሉት ይበልጥ ሊያስጠቃ መቻሉን በማጤን የተነገረ ሳይሆን ይቀራል?
የጥቅም መሰብሰቢያ መንገዶች
አንድ ቀላል ምሳሌ ላቅርብ፡፡ በአለቃው የታዘዘውንና ደመወዝ የሚያገኝበትን ሥራ ከመጤፍ ሳይቆጥር፣ ለባለጉዳዩ ስለሚሰጠው አገልግሎት ከባለጉዳዩ ጋር ይደራደራል፡፡ ባለጉዳዩ “ውኃ አጣሁ” በማለት ለአለቃው ያመለከተበትን አገልግሎት፣ መስመር መርማሪው/ቀጣዩ የራሱን ምክንያት እየሰጠ ውኃ ላለመልቀቅ እግሩን ይጎትታል፡፡ የሱ አለቃም ሆነ የአለቃው አለቃ ከድርድሩ ጀርባ ያዘዝንህ ሥራ ምን ደረሰ በማለት የሚጠይቁ ሳይሆን፣ እሱኑ እንዲያነጋግር ባለጉዳዩን ይገፋፉታል፡፡ “ሥራው ምን ደረሰ እያልክ ካለመሰልቸት ጠይቀው” ይሉታል - ባለጉዳዩን፡፡ በመካከል የውኃ እጦት ባለጉዳዩን ከማማረር አልፎ፣ በጋሪ እየገፉ በጀሪካን ለሚያቀርቡ ግለሰቦችና በቦቴ እየሞሉ ውኃ ለሚያከፋፍሉ ባለቦቴዎች ሲሳይ እስከመሆን ይደርሳል፡፡ ስምና አድራሻ ሳይጠቀስ በቀላሉ ሲቀርብ ይህንን ይመስላል፡፡ ግን ማን ሊሰማ? ዜጋ ሁሉ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪዎች በየቤቱ ፍዳውን እየቆጠረ ነው፡፡ “ሰውን እያማረራችሁና ኪሱን እያራቆታችሁ እናንተ በልጽጉ” ተብለው የሚሰማሩ ይመስል ሩጫው ተፋፍሟል፡፡ በውኃም፣ በመሬት ይዞታም ሆነ በግንባታ ፍቃድ፣… የሚሆነውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ለማሻሻል ብዙ ተሞክሮም እንኳን፣ በእምቢተኝነታቸው የጸኑ የሥራ ሂደቶችና ሠራተኞች አሉ ማለት ይቻላል፡፡
ብዙውን ጊዜ የመንግሥት ሠራተኛው ሌላኛውን ትይዩ (parallel) መስመር ተከትሎ ለራሱ ጥቅም ሲሠራ፣ በመንግሥት መዋቅር አማካኝነት በቀጥታ ለመገልገል የሄደው ትክክለኛው ተገልጋይ ላይ የተለያዩ ጫናዎች ሲደርሱበት ይስተዋላል፡፡ በመጀመሪያ፤ “የለም” ወይም “ለሥራ ወጥቷል” የሚል ተደጋጋሚ ቃል እየሰማ ተመላላሽ በመሆን ጉዳዩን ባሰበው ወቅት ለመፈጸም ያዳግተዋል፡፡ ሁለተኛ፤ በጣም ብዙ የሠራተኛ ደላሎች ያጋጥሙታል፡፡ “ብዙ” ከማለት መላው ትውልድ ደላላ ትውልድ ነው በማለት አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ ሠራተኛው ባለጉዳይን ከማስተናገድ ይልቅ የሚቀናው “ጉዳይ አስፈጻሚዎችን” ቅድሚያ ስጥቶ ማስተናገድ ነው፡፡ የመንግሥት ሥራውን ወደ ጎን አድርጎ፣ ራሱም የጉዳይ አስፈጻሚ ሚና በመጫወት ክፍያ እንዲሰጠው እጅ እጅ የሚያይ በርካታ ነው፡፡   
የአገልግሎት መስመሮች ሁሉ በእነዚህ የሠራተኛ ደላሎች የተጣበቡ ናቸው፡፡ ሁሉም  ሠራተኛ (አለቃውን ጨምሮ) “በጉዳይ አስፈጻሚ” ቀብድ የተያዘ ባለዕዳ ነው፡፡ አለቃው ራሱ ባለጉዳዩን ፊቱ አስቀምጦ እየተነጋገረ እያለ፣ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ባልሆኑ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ወይንም ጉዳይ አስፈጻሚ በሆኑት በራሱ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሚቀርብለትን ሥራ ቀድሞ ይፈጽማል፡፡ “ተራ ጠብቅ” የሚል ቃል እንኳን ከአፉ አይወጣውም፡፡ አለቃው ሁሉ ፈሪ ነው፡፡ ወይም የጥቅሙ ተካፋይ ነው፡፡ ከሁለት አንዱ፣ ወይንም ሁለቱንም ሊሆን ይችላል፡፡
ባለጉዳይ ለማግኘት የመጣውን አገልግሎት በትክክልና በሰዓቱ ለማግኘቱ አይተማመንም፡፡ ከወንበሩ ሲነሳ፣ ሲንጠራራ፣ ካውንተሩ ላይ ሄዶ ዐይኑን በማቁለጭለጭ ከአሁን አሁን እጠራለሁ እያለ ጆሮውን ጉዳዩ ወዳለበት አቅጣጫ ሲቀስር ይውላል፡፡ ለምን ይመስላችኋል ተራ ይጠብቅ ዘንድ የተዘጋጀለትን መቀመጫ በመተው ካውንተሩ ላይ ቆሞ ሥፍራን የሚያጣብበው? አለመሰልጠን ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ጉዳዩ ተፈጽሞ እስኪገላገል ድረስ ምጥ ላይ ነው፡፡ ጉዳዩን የያዘው ፋይል ጠፍቷል ሊባልም ይችላል፡፡ ፋይል የመጥፋት ነገር የተለመደ ነው፡፡ ቤተኛ የሆኑ ቀብድ አስያዥ ጉዳይ አስፈጻሚ ደላሎች ውስጥ ድረስ ገብተው ጉዳያቸውን ያስፈጽማሉ፡፡ ደላሎቹ ከፈለጉም ፋይል እንዲደበቅ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ተተራማሹ ብዙ ነው፡፡ ጉዳይ አስፈጻሚውና የሠራተኛ ደላላው ይተረማመሳል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መተረማመስ የመቀነስ አዝማሚያን ያሳየ ይመስላል፡፡ ቅንነት (positive thinking) ከሌለ ምን ሊፈይድ! የመተረማመሱ መቀነስ የሚያሳየው ሠራተኞች ተቀንሰዋል ወይንም ወደ ሌላ ሥፍራ ተዘዋውረዋል የሚለውን ነው፡፡ በዚህም የሰው ኃይል እጥረት ያለ ለማስመሰልና ብዙ የጣረ መሆኑን በመግለጥ፣ በመንግሥት ተከፍሎት ላከናወነው ሥራ ባለጉዳዩ ተጨማሪ ጉርሻ እንዲሰጠው እጅ እጁን ያያል፡፡ በተለይ የውኃ አገልግሎት የሚደንቅ ነው፡፡ በውኃ እጦት እየተቸገረ ያለውን ሁሉ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አንዴ በመንገድ ሥራ፣ ሌላ ጊዜ በመስመር ብልሽት፣ አሁን አሁን ደግሞ በኮሪደር ልማት ይሳበባል፡፡ ፈጣሪ ደግ ነው፤ ፀሐይንና አየርን ነፃ አደረገልን እንጂ መኖር አንችልም ነበር የሚሉ በርካቶችን ታደምጣላችሁ፡፡
የ”ሥራ” ሪፖርቶች ጠባይ  
ድሮም ሆነ ዛሬ በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሩብ፣ የመንፈቅ፣ የዘጠኝ ወራትና የዓመት ሪፖርቶች ውስጥ የማይዘለሉ ችግሮች አሉ፡፡ ከማይዘለሉት ችግሮች ዋናዎቹ የሰው ኃይልና የበጀት እጥረት ይገኙባቸዋል፡፡ እጥረት አለባቸው ተብለው ሪፖርት የሚቀርብባቸው ሁለቱም ምክንያቶች ቢብራሩ በጣም ሰፊ ይሆናል፡፡ እኔ ላሳጥረው፡፡
በቂ የሥራ ድርሻ ሳይሰጣቸው መቀመጫቸውን ከወንበር ጋር እያለፉ የወንበር ልባስ የሚጨርሱ ወሬኞች በተትረፈረፉበት ሁኔታ ነው የሰው ኃይል እጥረት የመኖሩ ሪፖርት ሳያሰልስ የሚቀርበው፡፡
በጀትም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ በአጭሩ ሲብራራ እንደሚከተለው ነው፡-
የበጀት ዓመቱ ሐምሌ ወር ከመጀመሩ በፊት (ከሰኔ 30 በፊት) ካለፈው በጀት የተረፈ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ተመላሽ (ፈሰስ) ይደረጋል፡፡ በጀትን መመለስ (ፈሰስ ማድረግ) ጉዳት አለው፡፡ ከመለሰ፣ አስተዳደሩ ለወደፊቱ ለመሥሪያ ቤቱ የሚያዝለትን የበጀት መጠን አሳነሰው ማለት ነው፡፡ በቅሎ ገመዷን አሳጠረች እንዲሉ ቀድሞ ገመዷን ማስረዘም ያስፈልጋል፡፡ ገመዱ ካጠረ፣ መሥሪያ ቤቱ ተጨማሪ በጀት እንዲያዝለት ሲጠይቅ “የተመደበላችሁን በጀት መጠቀም አልቻላችሁም” ተብሎ ጭማሪ መጠየቅ ከባድ ይሆናል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ በጀት እየጨመረ እንዳይሄድ አቅጣጫውን/ትሬንዱን ያበላሸዋል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ በጀት መጨመር አስተዳደሪያዊ ጥቅም አለው፡፡ በግዢና እድሳት ስም የሚቆነጠር የመንግሥት ገንዘብ የሚገኘው ጥቅም ላይ ያልዋለ በጀት ሲገኝ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ኃላፊና ቁልፍ የሥራ ቦታዎች ላይ የተመደበ ሠራተኛ ሁሉ ሻኛው ያበጠው፣ 80 ግራም የማትሞላ ባለ 8 ብር ዳቦ በልቶ በመጥገቡ ይመስላችኋል?
በየዓመቱ በሰኔ ወር ውስጥ የዕቃ ግዢዎችን በመፈጸም የዕቃ ገዢዎችንና የአለቆችን ኪስ ማዳበር አንዱ የበጀት ፈርጅ ነው፡፡ ለሰው ኃይል ቅጥር የሚውለውም በጀት በአምቻ፣ ጋብቻ፣ በአገር ልጅነት፣… ሥራን በማደል የራስን ማህበራዊ ሥፍራን የማደላደያ መንገድ ነው፡፡ ይህን ራሱን የሥራ ፈጠራ በማለት ይጠሩታል፡፡ ሥራ ይፈጠራል፡፡ ሥራው ያስገኘው ውጤት ግን መለኪያው ዜሮ ላይ ነው፡፡ ሁሌም ለሚዛን የሚቀመጠው የተዛባ ሚዛን ነው - ዜሮ ላይ የተገሸረ፡፡ ገንዘብና የሥራ ውጤት ሲመዘኑ መዛኙ ገንዘብ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ሥራ ባለመኖሩም ነው የመንግሥት ደሞዝ እየተከፈለው የሚገኝ የሠራተኛ ደላላ ሁሉ ከጉዳይ አስፈጻሚው ጋር እኩል አብሮ የሚተረማመሰው፡፡
የሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባሕርይ፣ ገንዘብ በወጣበት ሥራ ልክ ውጤትን በመተመን የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ አይደለም፡፡ ይህን ያህል ታቅዶ ይህን ያህል ተከናወነ ለማለት ለሪፖርት ፍጆታ የሚውል የጥቅም ተመን ማቀነባበሪያ ነው፡፡ በወጣው የገንዘብ መጠን የሚሰፈር የሥራ አፈጻጸም ባህል የለም፡፡ ባህሉ ገንዘብ የማይጠግበውን ቢሮክራሲ ሆድ መሙላት ነው፡፡ ቢሮክራሲውን የሚያሽከረክረው ሰው ደግሞ ቢሮክራት ይባላል፡፡ ዛሬ አንድ የውኃ መስመር የሚፈትሽና መስመር የሚቀጥል ሠራተኛ ወይንም አንድ የግንባታ ፍቃድ የሚፈቅድ ባለሙያ ሁሉ ቢሮክራት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፣የውኃ መስመር ሠራተኛ ሲፈልግ ቤት ለይቶ ውኃ ይለቃል፤ ሲያስፈልገው በመቀነስና በመዝጋት ጭምር ጥቅሙን ያሟላል፡፡ ሁሌም የሚጎድልበት ባለጉዳዩ ነው፡፡ መሬትና የግንባታ ፍቃድ የተለየ ባህሪ ስላላቸው፣ ጥቅማቸውም ካዳሚያቸውም ብዙ ነው፡፡
በእርሻ ሥራ ላይ ብዙ ገበሬ በትንሽ መሬት ላይ ሲገኝ የግብርናው ሥራ ከሚፈልገው በላይ የሆነ ገበሬ/የሰው ኃይል ይዟል ይባላል (over employed የሆነ የሰው ኃይል/ገበሬ መኖሩን ለማመልከት)፡፡ ያ በሚሆንበት ወቅት ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ ይፈልሳሉ፡፡
በቢሮ ሥራ ረገድም ቢሆን ሥራውን ለመሥራት ከሚያስፈልገው የሰው ኃይል በላይ መቅጠር ያጋጥማል፡፡ በቢሮም ውስጥ ለትንሽ ሥራ ብዙ ሠራተኛ (over employed የሆነ የሰው ኃይል) አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን በዐይን ተመልክቶ ብቻ መፍረድ ይቻላል፡፡ ሥራ አጥ (unemployed) የሚባለው ያልተቀጠረው ብቻ አይደለም፡፡ ተቀጥሮ ደሞዝ እየተከፈለው በቂ ሥራ ሳይኖረው ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን የራሱን ትይዩ የሥራ መስመር ዘርግቶ የሚያውደለድለው ሁሉ ሥራ የሌለው ወይንም ትርፍ ቅጥር (unemployed/over employed) ነው፡፡ ለምን ከሥራው ጋር ያልተመጣጠነ ብዙ የሰው ኃይል ኖረ? በርካታ ምክንያት ሊቀርብበት የሚችል ጥያቄ ነው፡፡ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የመንግሥት ወይንም የግል ሠራተኛ ተደርጎ የተቀጠረ ሰው ከሥራው ቢፈናቀል፣ ጦሙን እየዋለ ሌላ ሥራ ሲፈልግ ይኖራታል እንጂ ከተማን ለቅቆ ወደ ገጠር ተመልሶ ይሄዳል ብላችሁ አትጠብቁ፡፡ ባለው የኤኮኖሚ ሁኔታ/ደረጃ ፍልሰቱ ከገጠር ወደ ከተማ እንጂ ተገላቢጦሹ አይሰራም፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ችግር በተቃለለ ነበር፡፡ የኤኮኖሚ ልማት ከገጠር ወደ ከተማ ይሁን ብለው ርዕይ የነበራቸው መንግሥታት ምክንያት ነበራቸው፡፡ ይህ በራሱ የርዕዮት መስመር የሆነ ሰፊ ርዕስ ነው፡፡   
ከሥራ ጋር ያልተመጣጠነ በርካታ የሰው ኃይል መኖር ምክንያቱ በርካታ ሊሆን ቢችልም፣ አንዳንዶቹን ግን መገመት ይቻላል፡፡ ወይ ለሰው ሥራ ለመፍጠር ሲባል (ፖለቲካ) ባልተመጣጠነ ሥራ ያልተመጣጠነ የሰው ኃይል እንዲሰማራ ተደርጓል፡፡ ወይንም የሰው ኃይል ሲበዛ፣ ተያያዥ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችም ከፍ ተደርገው ስለሚመደቡ ከዚያ ለመቦጨቅ የሚሻ አስተዳደር አለ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር የአስተዳደር ባህል ሆኖ ዘመናትን ያስቆጠረ አካሄድ ነው፡፡ በእርግጥ ከዘመነ ኢህአዴግ ጀምሮና ዛሬም “የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” አስተዋጽኦ የሚባል ነገር አለ መሰለኝ? ያ በራሱ ሠራተኛን ለማብዛት ግድ ይላል፡፡ ለሁሉም ክፍት የሆነ የሥራ መስክ መኖሩ የሚያኮራ ጉዳይ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሥራን በውል አውቆ በሐቅ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ሠራተኛ እንዲፈልስ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ልማትን ፍትሐዊ አያደርግም፡፡ በየቢሮው ሥራ የሌለውና ሥራውንም የማያውቅ በርካታ ሠራተኛ አሁንም ይተረማመሳል፡፡ ያንንም አብሮ ማሰብ ነው፡፡  
ማጠቃለያ
ከዘመነ ኢህአዴግ ጀምሮ የመንግሥት ሥራ (public service) ባህልና ዲስፒሊን በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ ሠራተኞች  ባልተመጣጠነ ሥራ (ሊሠሩበት የሚገባው ሰዓትና የተመደበላቸው ሥራ ሳይመጣጠን) በቢሮ ውስጥ በመገኘታቸው ብቻ ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ክፍያቸው የኑሮ ወጪያቸውን የሚሸፍን አይደለም፡፡ ይህ ግን ቀድሞም ላለመቀጠር መወሰንን እንጂ፣ የተቀጠሩበትን ሥራ ላለመሥራት ምክንያት መሆን የለበትም፡፡ ከተቀጠሩ በኋላ ሥራንና የሥራ ሰዐትን አክብሮ መሥራት ግድ ነው፡፡    
ክፍያውና በአገሪቱ የተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ባለመመጣጠናቸው የተነሳ፣ ሠራተኞች ኑሯቸውን ለመደጎም ከመንግሥት ሥራ ጎን ለጎን የግል ሥራ በመሥራት ራሳቸውን ለመደጎም ሩጫ ላይ ያተኩራሉ ተብሎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል፡፡ የሥራ ባሕሉ የተበላሸ መሆኑንም በሐዘኔታ የሚገልጡ ብዙ ናቸው፡፡ ያገኙት የተትረፈረፈ ሰዓት በያዙት የመንግሥት ሥራ ላይ ሌላ ደርበው እንዲሠሩ ዕድልን ሰጥቷቸዋል፡፡ በትርፍ ጊዜ መሥራት የሠራኛው ምርጫ ነው፡፡ ደሞዝ በሚከፈላቸው የመንግሥት ሥራ ደርበው መሥራት ግን ሙስና ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉም ሠራኛ ሙሰኛ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡  
ምክንያቶቹ ከጠቀስኳቸው ውጭ የመሆን እድላቸው ጠባብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት እያደገና የሥራ ባህል እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡
በቢሮ ውስጥ እያንዳንዱ ሠራተኛ “ሊሸከመው ከሚችለው” የሥራ ድርሻ በታች ቢሰጠው ምን ይፈጠራል? የእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ዲሲፒሊን ምን ይመስላል? ምን ያህል ሥራ ነው አንድ ሠራተኛ መሥራት የሚገባው? ያንንስ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? የመሥሪያ ቤት አስተዳዳሪዎች በቅድሚያ ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደርም ሠራተኛን እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባው ሊያውቅ ይገባል፡፡ የሥራ ሥነ-ምግባር ከነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ይወለዳል፡፡
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ካሮትና ልምጭ (carrot and stick) መኖራቸው የግድ ነው፡፡ ካሮቱ ታታሪውን ማበረታቻ፣ ልምጩ ደግሞ ዳተኛና ዋልጌውን ለመሸንቆጫና የሥራ ሥነ-ምግባርን ለማስከበር ይውላሉ፡፡ በፍርሃት የተሸበበ አለቃ ሥራን ይበድላል፡፡ አለቃውን፣ ሥራውንና (የሥራ ሰዐቱን ጨምሮ) ተገልጋዩን የማያከብር ሠራተኛ ደግሞ የትም ሥፍራ ሊኖረው አይገባም፡፡ ካልሰራ አይበላም፡፡ አለቃውም እንደዚያው፡፡ ይሁን እንጂ፤ የሠራተኛ አለቃው ሕግን መሠረት ያደረገ ሠራተኛን የመቅጫ/የማባረሪያ ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ ልምጩ እሱ ነው፡፡
በየመንግሥት መ/ቤቶች ተዟዙሬ በጥቅሉ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የአስተዳደርን ጥበብ የተጎናጸፈ አሰሪ/አለቃ ገና አልተፈጠረም፡፡ ቢኖርም ጥቂት ነው፡፡ ዘመነ ሕወሓት ያንን ፈጥሮ ብቻ አላለፈም፡፡ አለቃና ምንዝሩን ማወቅ ይከብዳል፡፡ አለቃው ፈሪ፣ አድር ባይና በራሱ የመይተማመን ነው፡፡ ሕወሓት፣ ባለማወቅም ይሁን ወይንም ለራሱ ፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ሲል ትውልድና ሥራን ቀያይሯል፡፡ በዚህም፣ በርካታ ግዴለሽ (Laze fare) የትውልዱ አባላት ተፈጥረዋል፡፡ ጊዜና ቴክኖሎጂ ተጭነውት ይሆን? ወይንስ ሴራ?
ዘመነ ሕወሓት የሠራተኛ ስርዓት እንዳይኖር ሲጥር የኖረ የዘረፋ አስተዳደር እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ ዘረፋ ለኦዲት የማይመች ምስቅልቅል ሁኔታን ይፈልጋል፡፡ ሰዎችም ኦዲት እንዳይደረጉ ቶሎ ቶሎ ከቦታቸው ይነሳሉ፡፡ የኦዲት ነገር ሲነሳባቸው ዘራፍ የሚሉ አለቆችና ጭፍራዎቻቸው የበዙ ናቸው፡፡
በመሥሪያ ቤቱ ስለሚገኘው ያልተፈጸመ ጉዳያችሁ ስትጠይቋቸው “እኔ ለቦታው አዲስ ነኝ” ይላችኋል፡፡ ቢሮዎች በሙሉ ተተራማሽ የሚበዛባቸው ናቸው፡፡ ስርዓትን ስትፈልጉት ብትውሉ አታገኙትም፡፡ ማስመሰል ብቻ!
ባለሙያ ተብሎ በየክፍሉ የተመደበው ሠራተኛው በብልጠትና በጉልበት ለማደር የተዘጋጀ ነው፡፡ ትክክለኛ ጥያቄ የሚጠይቅ ባለጉዳይ ሁሉ “ሀርደኛ” ይባላል፡፡ ሠራተኛው የታዘዘውን ከመሥራት ይልቅ፣ “ሀርደኛ ላይ” ድንጋይ አንስቶ ለመወርወር የቀረበ ነው፡፡ ሠራተኛው በራሱ ጊዜ፣ በራሱ ውስጥና ለራሱ ጥቅም ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ በተለይ የ60ዎቹ ትውልድ አባል የነበረ “ሀርደኛ” ተብሎ እንደሚፈረጅ ታዝባችኋል?
የትምህርት ስርዓቱ አበላሽቶት ይሆን እያልኩኝ እጠይቃለሁ፡፡ በራሱ ሥራ ላይ ከማትኮር ይልቅ አብረውት ከሚሠሩት ሠራተኞች ጋር ማውራትና ለነሱ ሥራ መተባበር ይቀናዋል፡፡ ብዙው ራሱን ችሎ የመሥራት ባህል ገና አላዳበረም፡፡ መቀዳዳት ባህል ተደርጎ በነበረ የትምህርት ሥርዓት አልፎ የለም? የሚያሳየው ባህሪ የሚያውቀውን ብቻ ነው፡፡ መጠየቅ ስትጀምሩ ነው “ሀርደኛ” የምትባሉት፡፡ ትኩረት የሚሻን ጥያቄ የሚጠላ በርካታ ነው፡፡ ለአንድ ጉዳይ፣ ሦስት ሰዎች ሦስት ዓይነት መልስ ይሰጧችኋል፡፡ የቱን ትይዙት?
ያንን ስመለከት ሠራተኛው ተማሪ ሆኖ ያለፈበት የአምስት ለአንድ የሚለው የትምህርት ሥርዓት ትዝ ይለኛል፡፡ ያ የአምስት ለአንድ “የጥርነፋ ሥርዓት” ለስለላ እንጂ እድገትን ዓላማው ላደረገ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥ አያገለግልም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢን ያበዛል፡፡ በራሱ ዕውቀት የሚተማመን ሠራተኛን ቀርጾ አያወጣም፡፡ ራሱን ችሎ የሚሠራ ትጉህ ሠራተኛን ማግኘት ምጥ ነው፡፡ “ሀርደኛ” ሆንኩኝ ልበል?
የዘመነ ሕወሓት ስርዓት ለአገሪቷ ካወረሳት መልካም ካልሆኑ እሴቶች አንዱ ከራሱ ጥቅም ውጭ ለአገር የማያስብ ስግብግብ ሠራተኛን ማበራከቱ ነው፡፡ የመንግሥት የሥራ መመሪያ ሌላ፣ የሠራተኛው የሥራ አካሄድ ሌላ - አልተገናኝቶም፡፡ ይህንን መለወጥ አንድ ሌላ ትውልድ በናፍቆት እንድጠብቅ ያደርገኛል፡፡ ትውልዱ በ30 ዓመታት ያዳበረውን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሊተወው ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጥሩ ተቋም፣ ካለ መልካም ሠራተኛ እንዴት ተደርጎ ይታሰብ ይሆን? በሠራተኛው የሥራ ዲሲፒሊን፣ ችሎታና ፕሮፌሽናሊዝም ላይ ገና ብዙ ብዙ መሥራት ይፈልጋል፡፡ በሁሉም መስክ ደላላ ሠራተኛ በዝቷል፡፡ መንግሥት በበጀቱ የዘረጋውን የሥራ መስክ ተጠቅሞና ተገን አድርጎ ሠራተኛው የግሉን ትይዩ የድላላ/ጉዳይ አስፈጻሚነት የሥራ መስክ ከፍቷል፡፡ ከሌበር ኤኮኖሚክስ ባሕሪያዊ እይታ አኳያ የሪሰርች መነሻዬ ላደርገው የማስበው አንዱ ጉዳይ ይህን ነው፡፡ ለአገር ጥቅም ሲባል ይህንን ትይዩ መስመር እንዴት ማገናኘት ይቻል ይሆን? ሰላም ለሁላችን፡፡


Read 362 times