እጣ ፈንታ እና ነፃ ፍቃድ ተባብረው የሎሊታ አይኖች ላይ አምጥተው ገተሩኝ፡፡
መፍትሄ የምትሻው የነፍሴ መንኮራኩር ወደየት እየተነዳች እንደሆነ ስላልገባኝ፣ እያስደሰተኝና ደህና አድርጎ እየቃኘኝ ያለውን ስቃዬን እንዲያክሙት ቃላቶቼን እስኪያልባቸው ድረስ አሯሩጬ መፍትሄ እንዲያድኑ ልላካቸው….
ለአስራ ሦስት አመት ያህል በሀያል ወጀብ ስጓዘው የነበረው የትዳር ህይወቴ ከዚህ በፊት እንዳልተከሰተ ሆኖ እያየሁት እንደ ጤዛ ሟሟ፡፡ ትዳር የራሱ የሆነ ሀገር ቢኖረውም የኔ ህሊና ውስጥ ያለው ግዛት ብቻውን መሰንበት ተመኝቶ ያፈቀርኳትን ከአይኔና ከህሊናዬ ውስጥ ይዞብኝ ኮበለለ፡፡ አሁን ሚስቴ የምላት ሴት ከርቀት እንደሚታይ ሚራዣ ሆና ሰንብታ ማግጄ ካቃጠልኩት ትዝታዬ ጋር አብራ ተናለች፡፡ አሁን የለችም፡፡ ሁለት አመታት ብቻዬን በራስ ፍቅርና በተመስጦ ብልጠት የፍቅር ህይወት የሚባለውን አምልጬው ከረምኩ፡፡
አሁን ግን ነፍሴ መፈቀርን ተመኘች፡፡ መወደድን ናፈቀች፡፡
***
የተስፋን ምንምነት እፈላሰፍበት ከነበረው አንዱ የቀን ቅርፊት ውስጥ…..
ከብዙ ጎረምሶች መካከል ውስጥ ሆና ነው ያየኋት… እንደቆነጀች፣ አተኩራ ላፕቶፑዋ ላይ በትጋት እየሰራች፣ መሀል ላይ ቀና ብላ አካባቢዋን በንቃት እየቃኘች….. ቁንጅና ያደከማት ትመስላለች፡፡ በጎረምሶች ግሪሳ ውስጥ ሆና መታየት የምትፈልግ አትመስልም፡፡ ሰው ሲበዛ የማትታይ መስሏት ነበር፡፡
እኔ አየኋት…
ሳያት አላየችኝም፡፡ ሳስባት አታውቅም፡፡
ለተከታታይ ሁለት ወራት ያለችበት እየሄድኩኝ እየሸሸኋት አየኋት፡፡ ልታየኝ ስትል እየተደበቅኋት ቃረምኳት፡፡ የምርም ረስቼ ነበር፡፡ ሴትን ልጅ ተጠግቶ በቃላት ዜማ ግለቷን ማብረድ፣ ሴትን ልጅ በትኩረት ማሰላሰልና መናፈቅ እንዴት እንደነበር ከመጀመሪያ ሚስቴ ጋር አብሮ የመነነ የስሜት ስልት እንደሆነ ካመንኩ ሰንብቻለሁ፡፡ ልቤ የተሰበረው ድረስ ደርሳ ለኔ ብላ በፈተለችው የቃላት ክር ትጠግነኛለች የምላት ሴት ምድር ላይ ያለች አይመስለኝም ነበር፡፡
አግብቶ መፍታት ውስጥ ያለው የህመም ጉልበት ከምንም ህመም የሚልቅ የሚመስለኝ እኔ ብቻ የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፤ በዛም ምክንያት ማፍቀር ብፈልግ እንኳን ትዕግስትና ፅናቱ አብሮኝ ይቆያል ብዬ አላምንም ነበር፡፡ ሆኖም መናፈቅ ውስጥ ያለውን ረቂቅ ፍቅር፣ አለመናፈቅ ውስጥም አገኘሁት፡፡ ራሴን ልፈልግ ህሊናዬ ውስጥ ስሰርግ ላገኘው የቻልኩት የራሴን ድምፅ ብቻ ነው፡፡ ካላፈቀርኩ ባዶነቴ መርዝ ሆኖ የሚገለኝ ይመስለኝ ነበር፡፡
በዚህ ሁሉ ትርምስ መሀል አየኋት….ሎሊታን አየኋት፡፡
ያየኋት ሰሞን ሴት ሳይሆን ምክንያት ያገኘሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ህመሜን የማክምበት ምክንያት፣ የምፀልይበት ምክንያት፣ ጠዋት ስነቃ ፈገግ የምልበት ምክንያት፣ በላዬ ላይ ተለጥፎ የሚከተለኝን የተስፋ መቁረጥ ጥላ በአይኖቿ ውዝዋዜ ብቻ የምረታበት ምክንያት….እነዚህ ሁሉ ነገሮች የኔ ብቻ እንደሚሆኑ ምንም ሳትናገር…ሳታውቀኝ ቀድማ ያረጋገጠችልኝ ነበር የመሰለኝ፡፡
በተቀመጠችበት…ምንም ሳትናገር እያዳነችኝ እንደሆነ አታውቀውም፣ በስራ ተጠምዳ ወዲያ ወዲህ ስትል እያየኋት የምረጋጋውን ነገር እሷ አልተረዳችውም፣ እንደ ድንገት ፈገግ ስትል ለማየት የአይኔን ብሌን በየባዶ አየሩ ላይ ሳስጋልበውና ስጠብቃት ሎሊታ አላየችኝም፣ የሷን ትኩረት ለመሳብ ምድር ላይ የተሰማውን ወሬ ባወራ ሎሊታ የምታዳምጠው እኔን አልነበረም፣ እያየኋት በቆየሁባቸው ሁለት ወራት ውስጥ እሷን ለማናገር የነፍሴን ጉሮሮ አንቄ ቃላት ውለድ ስለው እሷ አልነበረችም፣ የድፍረት ጉልበቴን የነጠቀውን የፍቅር እጦት ብተርክላት እችል ነበር…ሎሊታ ግን ከጅምሩም ያለችበት የስራ ቦታ እንደምመጣ ራሱ በቅጡ ያስተዋለችው ስለማይመስለኝ ሊንደረደር ያለው ድፍረቴን መልሼ እንደ ውሀ እውጠዋለሁ፡፡
***
አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡ ከስራ ቦታው ፎቅ ላይ ባለ በረንዳ ላይ ተቀምጬ በተመስጦ እያጨስኩ ባለሁበት ሰዓት ላይ ሎሊታ እንደ አስገዳጅ ህልም መስላ ድንገት ከፊቴ መጥታ ቆመች፡፡ በጆሮዬ ላይ ያጠለኩትን የጆሮ ማድመጫ አውልቄ ተመለከትኳት፡፡ ሳትናገር ለጥቂት ሰከንዶች አየችኝ፡፡ ፈራኋት፡፡ ሰከንዶቿ በሙሉ አልባከኑም…እስካሁን ህሊናዬ ውስጥ ጥዑም ዜማ ሆነው ፀጥታን ይዘምራሉ፡፡
“ስምህ ሉሲፈር ነው?” ብላ ጠየቀችኝ፡፡
“እያሉ ይጠሩኛል…ለምን እንደሆነ ግን ላውቅ አልቻልኩም፡፡”
“ኤደን እባላለሁ” አለች፡፡ በንዴት የምታወራ ነው የምትመስለው፡፡ ልክ አስገድጄ ጠርቻት እየተዋወቅኋት ነው የመሰለኝ፡፡
“የኔ…” አላስጨረሰችኝም፡፡
“አንተ ሉሲ ነህ፡፡ ሉሲ ብዬ ነው የምጠራህ፡፡” አለች፡፡ እሷ ሉሲ ብላ ብትጠራኝና ሉሲፈር ተጠራሁ ብሎ አብሮኝ ቢመጣ ዳግም በመሀላችን እንዳይከሰት አድርጌ መጀመሪያውኑም ከመጣበት የሰማይ ቤቱ ጣጣውን እዛው እንዲጨርስ መልሼ የማባርረው ይመስለኛል፡፡
“እኔም ሎሊታ ብዬ ነው የምጠራሽ፡፡”
ጥላኝ ሄደች፡፡
የዛን ቀን ነው ከሎሊታ ጋር የተዋወቅሁት፡፡ እንዴት ደስ እንዳለኝ የቅፅበቱን እድሜ አሳጥሬ ብናገር እንኳን የምድር ቃላቶች ስብስብ የስሜቴን ጠብታ ግለት መናገር የሚችሉ አይመስለኝም፡፡
ከቀናት በኋላ ስልክ ተቀባበልን፡፡ ምሽቱንና ቀኑን በሜሴጅ እናወራ ጀመር፡፡ በጥልቀት እያወራኋት በሄድኩ ቁጥር በጥልቀት እየወደድኳት መጣሁ፡፡ እያየኋት በተመኘኋት ቁጥር ብዙ ቆንጆ ነገሮች እየሆነችብኝ መጣች፡፡ ከሷ ውጭ ማንንም ማውራት አስጠላኝ፡፡
***
ቀናት በገፉ ቁጥር ሎሊታ ራሷን ለኔ ግልፅ እያደረገችልኝ መሄድ ጀመረች፡፡ እንደኔው አግብታ እንደነበርና እንደፈታችም ማወቅ ቻልኩ፡፡ እውነት ለመናገር እውነቶቿ ብዙ ናቸው፡፡ እውነቶቿ ያስፈራሉ፡፡ ሀቀኝነት አፈር የሚያስበላበት ዘመን ላይ የሎሊታ ቃላት ጉልበታም እውነቶችን ይሰብካል….ጆሮዋ ውሸት ሲያገኘው ሮጦ ለአይኖቿ ያሳብቃል፡፡ ሎሊታ የምትናደደው በአይኗ ነው፡፡
***
“ስላንተ ሳስብ ትንሽ ለየት ያለ ስሜት እየተሰማኝ ነው፡፡”
“አልገባኝም ሎሊታ…ምን ማለት ፈልገሽ ነው?” ምን ማለት እንደፈለገች ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም…፡፡
“ብወድህ የምትወደኝ ይመስልሀል? ብታፈቅረኝ የምደሰተውን ደስታ መሸከም ትችላለህ?” እየጠየቀችኝ ነው….አይ ሎሊታ፡፡
“ሎሊታ እወድሻለሁ…እኔ…” ሃሳቤን ሳልጨርስ ሎሊታ በከንፈሮቿ ሀሳቤን ከነቃላቴ ዋጠቻቸው፡፡ ስማኝ ጥላኝ ካይኔ ተሰወረች፡፡ አይ ሎሊታ…ያፈቀረን ሰው ከአይን ብቻ በመሰወር የምታመልጠው መስሏታል፡፡
***
በየቀኑ መገናኘት ጀመርን፡፡ ብዙም አናወራም፤ የሚያስደስተን መተያየት ነው፡፡ የልባችንን ትርታ በአይናችን እንጮኸዋለን…የውስጣችንን ሰላም በመሳሳም እናረጋግጠዋለን…
“አሁን የእኔና ያንተ ግንኙነት ምንድን ነው የሚባለው?” ይሄን ጥያቄ ለምን እንደጠየቀችኝ አውቃለሁ፡፡ ማፍቀር ከሚያመጣው ጣጣ መካከል አንዱ ይህ ነው… ያፈቀርነውን ሰው በጣም ስላሰብነው እሱ ያደመጠን ይመስለናል…ወይንም አብሮን ቁጭ ብሎ በተመሳሳይ ህሊና የተረጎመው ይመስለናል፡፡
“እሳሳልሻለሁ ሎሊታ፡፡ ራሴን በጣም ስለምፈራው እሳሳልሻለሁ፡፡ ሆኖም ያንቺ መሆን ነው የምፈልገው፡፡ አንቺስ?”
“ያንተ”
***
ሁሉም ነገር ያለ እንከን እየሄደ ነው በምልበት የህይወቴ ምዕራፍ ላይ፣ ከሎሊታ ጋር የራሳችን የሆነ ቤት ይዘን የህይወቶቻችንን ደቂቃዎች በእኛነታችን ልናደምቀው በማስብበት ዘመኔ ላይ፣ እርግጠኝነት ውስጥ ያለውን ጉልበት ልሰብክ የህሊናዬን ድርሳን እያፀዳዳሁ ሳለሁ፣ ሎሊታን በልዩ ዝግጅት አሽሞንሙኜ እንድታገባኝ…ሚስቴ እንድትሆን ልጠይቃት የሰማይና የሁለንታን ሸማኝ በማማክርበት ጊዜ ላይ….አንድ ቀን….ሎሊታ ደወለች፡፡
“ሉሲዬ ስኮላርሺፑ ተሳካልኝ…በዚህ አመት ውስጥ ሁሉን ነገር ጨርሼ ከሀገር የምወጣ ይመስለኛል…ደስ አይልም ሉሲዬ፡፡” ሎሊታ ሳትደሰት ታምራለች…ሳትስቅ ታረካለች…ሳትናገር ትደመጣለች፡፡ የዛን ቀን ግን ደስታዋን ጠላሁት፡፡ ቃላቶችዋ ጣቃ ሆሄያት ሆነው በየግላቸው እየገደሉኝ ነበር ጆሮዬ ውስጥ ሲሰርጉ የነበሩት፡፡
“ትሄጃለሽ ሎሊታ?”
ሳትመልስልኝ የስልክ መስመሩ ላይ ቆየች፡፡ እንደዚህ ከሆነች ደግሞ ምን እንደምትመልስልኝ አውቀዋለሁ፡፡
***
የዛን ቀን መልስ ሳትመልስልኝ ስልኩን ዘጋሁባት፣ ስልኩን ወስጄ እየደጋገምኩ መሬት ላይ ከሰከስኩት፣ አርቄና እንዳልደርስበት አድርጌ ወረወርኩት፡፡
ምን ያህን ፈርቼ እንደነበር የማውቀው እኔ ነኝ፡፡ ድጋሚ መረታት ምን ያህል እንደሚያሳምመኝ እያወቅሁት ነበር የገባሁት፤ እዚህ የኤደን አፀድ ውስጥ፡፡ በኤደን ገነት ውስጥ ያለችው ሴት አዳምን ጥላው አልሄደችም….እስኪሞት ድረስ አብራው ነበረች፡፡
ትዝታ ያደክማል፤ ተስፋ እጅግ አስፈሪ ነገር ነው፤ ፍቅር በተወለደበት አይሞትም፤ ሲገድልም አያማክርም…
ሎሊታን ቀስ ብዬ ማፍቀር እችል ነበር?
የማይታሰብ ነገር ነው….
አሁን የት እንዳለች አላውቅም…ደጋግሜ የስራ ቦታዋ ብሄድም ያለችበትን የሚነግረኝ የለም፡፡
እየፈለገችኝ ሊሆን ይችላል….ምናልባት አጠገቤ ናት….ደስታዋን ለምን እንደፈራሁት አሁንም አሁንም እያሰላሰለች ሊሆን ይችላል…ወይ ደግሞ እኔ ውስጥ አይታው የነበረውን ወንድ ፍለጋ ብዙ ወንዶች እየተዋወቀች ሊሆን ይችላል፡፡
ጭንቅላቴ ግን የሚያርፈው ሎሊታን ሳገኛት ሳይሆን፤ ህሊናዬ ውስጥ ከልብ ትርታዬ እኩል…በያንዳንዱ እስትንፋሴ ውስጥ የሚነዝረውን የጥያቄ ሰልፍ ማስተናገድ ስችል ነው፡፡ ለምን ሎሊታ አንድ ቀን ጥላኝ እንደምትሄድ ማወቅ አልቻልኩም? እንዴት የበፊት ልምዴ ሊያድነኝ አልመጣም? ለምን ሎሊታ ሆነች…ለምን እሷ ሆነች? ልነሳ? ልፈልጋት? ምክንያቴን ላስሳት? ባገኛት ደግማ አትሄድም?
የፍቅር ውስብስብ ባህሪው ይህ ነው፡፡ ከራስ ተነስቶ ሲፈቀርና በድንገት በፍቅር መለከፍ ውስጥ ያለው ውስብስብ አያዎ ለሰው ልጅ ህሊና የፍቅርን ትርጉም እንደ ልቡ እንደሚያመናሽረው አጥርተን አልተረዳነውም፡፡ ሎሊታን እኔ ውስጥ ካለው የተስፋ ቁመት በላይ ሆኜ ነበር ማየት የነበረብኝ…በራሷ አፀድ ውስጥ ነበር አስሼ ማግኘት የነበረብኝ…መውደዷን እያደመጥኩ ነበር መከተል የነበረብኝ፡፡
ቀደምኳት…
ሳታመልጠኝ…ቀድሜ ህልማችን ጋር ልጠብቃት ፈጥኜ ከስፍራው ስደርስ መንገድ አሳትኳት…ሳታመልጠኝ ጠፋችብኝ፡፡
***
ሎሊታ…እዚህ ነኝ፡፡ ነይ፡፡
Saturday, 22 February 2025 11:55
ሎሊታ
Written by በኪሩቤል ሳሙኤል
Published in
ጥበብ