ለምን እንደኾን አይታወቅም፡፡ ዛሬ መስኮት ከፈትኩ፡፡ “እረ ዛሬስ ማን ሊሞት ነው?” እያሉ የፊት ለፊት ጎረቤቶቼ ሲገሸልጡኝ ይታየኛል፡፡ “ምነው እናንተ ገንፎ አማረኝ ትሉ የለም? ቅንጨ አማረኝ ትሉ የለም? ጎመን አማረኝ ትሉ የለም? ጠላ ዐረቂ ክትፎ እንኳን…(የማያውቁት ሀገር ሊናፍቅ አይችልም) …ሌላው ቢቀር ዛሬ ስድብ አማረኝ ብላችሁ ሰፈሩን ባንድ እግሩ ታቆሙት የለም? በቃ ዛሬ እኔም መስኮት መክፈት አማረኝ” እላለሁ ለራሴ፡፡
መስኮቱን ከፍቼ ወጩ ወራጁን ዐያለሁ፡፡ እዚያ ማዶ ባጃጆች ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ ባለፉ ቁጥር ከባቢውን አቧራ አልብሰውት ይሔዳሉ፡፡ በግራም በቀኝ … በረንዳ ላይ፣ሱቆች በር ላይ፣አጥር ላይ የተኮለኮሉት ሰዎች አቧራ ምግባቸው የኾነ ይመስል አፍና አፍንጫቸውን እንኳን ሲሸፍኑ ዐይታዩም፡፡ ሰርክ በአፍና አፍንጫ ጭምብል ተሸፍኖ የማየው ቴፕና ራዲዮ ጠጋኙ በዚያ ያልፋል፡፡ የኾነ ነገር (የሚጠገን ነገር መኾን አለበት) በፌስታል ይዞ ከባጃጅ ሲወርድ:- “ታዴ ኮሮና ጠፍቶ መስሎኝ” አሉት ክብ ሠርተው የቆሙት የሰፈሩ ጎረምሶች፡፡ “እስኪ ዛሬስ መልክሽን እንየው፡፡ ምን እንደምትመስል ማስታወስ እየተሳነን ነው እኮ፡፡ አፍና አፍንጫህ በስፍራው ነው? ሰው ያስባል አትልም? ስንት ነገር አለ፡፡ ክፉ አለ ደግ አለ፡፡ መንገድ ላይ ልንተላለፍ እንችላለን እኮ” ብለው ጭምብሉን ከአፉ ላይ ለመግፈፍ ይታገሉታል፡፡ “ያዘው ያዘው…አዎ…” እየተሣሣቁ፣እየገለፈጡ፡፡
“…እስኪ ዞር በሉ ውሪ ሁሉ፣ አንተ ቢኒ ነግሬሃለሁ…ምን አስበህ ነው? ሰገጤ ልቀቀኝ እንጂ” እያለ ጭምብሉን ላለማስደፈር በአንድ እጁ ይታገላል፡፡ አንድ እጁ አልረዳው ሲል ፌስታሉን ድንጋይ ላይ አስቀምጦ ሲታገል የሀገሩን ዳር ድንበር ላለመስደፈር የሚታገል ኩሩ ወታደር ይመስላል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ ጀግና!
የተከራየሁት ቤት ከፊት ለፊት በትዕግሥት ዐረቄ ቤት፣ቆሻሻ ማከማቻውን አልፎ ከማዶ ደግሞ በጋሽ ዘመኑ ዐረቄ ቤት ይዋሰናል፡፡ ከጋሽ ዘመኑ ዐረቄ ቤት ጎን ምንገድ አለ፡፡ አቧራ የለበሰ ምንገድ፡፡ በግራና ቀኜ ድምፅ የማይሰማባቸው ገዳም የመሰሉ መኖሪያ ቤቶች ዐቅፈውኛል፡፡ ከኋላዬ ምንና ማን እንዳለ አላውቅም፡፡
ሁለቱ ዐረቂ ቤቶች ያሉት አስተናጋጆች አንድ ደባል ትጉህ ሠራተኛ አላቸው፡፡ ቴፕ፡፡ እነዚህ ቴፖች ከትጉህ ሠራተኛ ይልቃሉ፡፡ ’እገሌ እኮ 24 ሰዓት የሚሠራ ባተሌ ነው’ ከተባለ፣ ‘ዓባይን ያላየ’ ያስተርትበታል፡፡ በተለይ የጋሽ ዘመኑ ቴፕ ከባተሌም በላይ ናት፡፡ ማለዳ ወፍ ሳይንጫጫ በመዝሙር አሐዱ ትልና ሌሊት እኩለ ሌሊት ላይ በአስረሽ ምቺው ታሳርጋለች፡፡ (የሚንቋቋ ወገቤን ላሳርፍ ወደ መኝታዬ ስለምሔድ እንጂ ከእኩለ ሌሊትም ልታልፍ ትችላለች)፡፡ ሁለቱ ዐረቂ ቤቶች መፎካከራቸውን እንጂ ሙዚቃቸው ነዋሪውን እንደሚረብሽ ታስቧቸው የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ሙዚቃውን በድምፅ መመጠን የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ መስኮት የምዘጋው ይሄን ሽሽት ነበር፡፡
እዚያ ሰፈር የገባሁ ሰሞን ቅሬታዬን ባሰማም ሰሚ ጆሮ አላገኘም፡፡ “እሱ እቴ እንጀራውን ጋግሮ እየበላ፣ እኛን አትብሉ ይላል፡፡ የዛሬ ጊዜ ደምበኛ ያለሙዚቃ ይጠጣ ይመስል…ምን ሐሳብ አለበት በየወሩ ደመወዙን መንግሥት ይከፍለዋል…” እያሉ ሳምንት ሙሉ ማጉተምተማቸው አይቀርም፡፡
ያለማጋነን ሙዚቃው ከመደጋገሙ የተነሣ ከማንኛው ድምፃዊ ቀጥሎ ማን እንደሚመጣ ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡ ሰው እንዴት በተመሳሳይ ሙዚቃ በተመሳሳይ ስልተ ምት ከማለዳ እስከ ማታ ሳይሰለች ሊዘልቅ ይችላል? ምግብ እንኳን ሲደጋገም ቋቅ ይላልኮ፡፡
በግድም ቢኾን የሙዚቃው ተቋዳሽ በመኾኔ (በጆሮዬ ላይ አስገድዶ መድፈር ስለሚፈጸምብኝ) የፊት ጥርሷ የተሸረፈውን በአንድ ልብስ የቆረበች የምትመስል አስተናጋጅ ‘ሙዚቃ ልስጥሽ’ ብዬ ወደ ቤት ወሰድኳት፡፡ ይሄ ቴፕ ያረፈው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው ብል ማጋነን አይኾንም፡፡ የቤት አገልጋይ ‘ጠላ አምጣ’ ተብሎ ተልኮ ጠላው በያዘው ማንቆርቆሪያ እስኪቀዳለት ድረስ ሰማይ ሰማይ ዕያየ የሚያርፋትን ዕረፍት ያለ፡፡ ‘አንቺ ቀስ አርገሽ! ዋ’ የሚሏትን ቀጣሪዋን (የጋሽ ዘመኑ ሚስት) ችላ ብላ ፍላሹን ስትነቅለው ‘ይህ ኤፍ ኤም ምንትሴ ነው’ ብሎ ዜና ማሰማት ጀመረ፡፡ ወሬ አቡክተው ሐሜት የሚጋግሩ ከበረንዳና ከሱቅ በር ላይ የማይጠፉት ለአፍታ ወጋቸውን አቁመው ገልመጥ እያሉ፣ በዚያ የሚልፉት ምንገደኞች እንደ ላም ቆመው ‘ጉድ! ይሄ ዐረቂ ቤት ዛሬስ ምን ነካው?’ እያሉ…
ከኮምፒውተሬ ላይ እንደ እንቁላል በመሐረብ ቋጥራ በያዘችው ፍላሽ ያገር ሙዚቃ ጫንኩላት፡፡ ወደ ቤቴ ይዣት ስገባ በሬን ክፍት ማድረጌ በጀ እንጂ በር ላይ ዐይናቸውን ለግተው የሚኾነውን ለማየት የሚያጮልቁ ብዙዎች ነበሩ፡፡ የተለየ ነገር የምናደርግ ይመስል… ብናደርግስ ወንድና ሴት የሚያደርገውን ነው የምናደርገው፡፡ ወንደላጤ ቤት ሴት ጎራ ካለች ለምን ዐይንና ምላስ እንደሚበዛ አላውቅም፡፡
ልፋቴ ግን የጨበጠ አይመስልም፡፡ ከሰጠኋት ሙዚቃ አንድስ እንኳ ሰምቼው አላውቅም፡፡ ከአንድ ቀን ውጭ፡፡ ያም ቀን ሙዚቃው የተጫነበት ነበር፡፡ ስልቴ ገብቷት ይኾን?
እኔም አበዛሁት መሰል፡፡ አሁን ማ ይሙት ‘አድርሻሽ ጠፋብኝ’ የሚል የባሕታ ገ/ሕይወት ዜማ ለዐረቂ ቤት ይሰጣል? አሁን ‘እኔ ተሳስቼ ወድጄሽ ነበር’ የሚል የሙሉቀን መለሰ ዜማ ለዐረቂ ቤት ይሰጣል? አሁን ‘አንቺ ሀገር አንዴት ነሽ‘ የሚል የኤፍሬም ታምሩ ዜማ ለዐረቂ ቤት ይሰጣል? አሁን ‘አሳድገሽኛል በማር በወተት’ የሚል የወሮታው ውበትን ዜማ ለዐረቂ ቤት ይሰጣል? አሁን ‘ትዝታ አያረጅም’ የሚል የምኒልክ ወስናቸው ዜማ ለዐረቂ ቤት ይሰጣል? ደብለቅ ብላ የገባችው ትክሻን ነቅነቅ የምታደርግ የጌቴ አንለይ አንድ ዜማ ብቻ ነበረች፡፡ እሷ ብቻ በቀን ሁለትዜ ዕድል ታገኛለች፡፡ “እስክስ እስከስ ያዝ እንግዲህ…” እያሉ ሲያስነኩት ይታየኛል፡፡
ይሄን ሁሉ የምናዘዘው እኔ ገብሩ ነኝ፡፡ ይሄን ሁሉ የምብሰከሰከው እኔ ገብሩ ነኝ፡፡ ይሄን ስም ያወጣችልኝ ወላጅ እናቴ ናት አሉ፡፡ ይህን ስሜን አባቴ አልወደደውም፤አይወደውም፡፡ አድጌ እንኳን የመፋቂያውን አፍ በጁ እየጠረገ ‘ገብሩ’ ብላ ስትጠራኝ “አንድኛውን ገብሬ አትይውም ኖሯል? የባርያ ስም” ሲል ሰምቸዋለሁ፡፡
ገብራ፣ገብርሻ፣ገብሩዬ፣…እንደ ቁልምጫ ስም ኾነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ለምን እንደኾን አይታወቅም ዛሬ መስኮት ከፈትኩ፡፡ “እረ ዛሬስ ማን ሊሞት ነው?” እያሉ የፊት ለፊት ጎረቤቶቼ ሲያሽሟጥጡኝ ይታየኛል፡፡ ሥራቸው ያውጣቸው! እንድያውም ይግረማቸውና ዛሬ ዐረቂ አምሮኛል፡፡
ከመሸ ወጥቼ ዐላውቅም፡፡
ዛሬ ግን ውጣ ውጣ የሚል ጋኔን ሰፈረብኝ፡፡ ዐረቂ አሰኘኝ፡፡ ከጋሽ ዘመኑ ዐረቂ ቤት ዘው ስል፣ በዚያ የነበሩት ደንበኞች የተመካከሩ ይመስል የያዙትን ወግ አቆሙ፡፡ ክፋታቸው መቼ ጠፋኝ፡፡ መነጽር ያደረገ ሰው ክፍላቸው አይደለም፡፡ እንደጉድ ያዩኛል፤እንደ ብርቅዬ እንስሳ፡፡ መነጽር ያደረገ ሰው ዐይኑ ሰው የሚወጋ ይመስላቸዋል፡፡ በነሱ ቤት ‘እኔ ቡዳ’ ነኝ፡፡ ፈራ ተባ እያሉ ሰርቀው ያዩኛል፡፡ እኔ ደግሞ ያለመነጽር መሔድ አልችልም፡፡ ብርሃን የሚመጥን መነጽር(photo solar) ነው፡፡
‘ስትተኛ ብቻ ነው የምታወልቀው‘ ያልሽኝ ጀርመናዊት ሐኪም እግዜር ይይልሽ!’
መነጽሩ ከዐይኔ ተጣብቆ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ በሰፈሩ፣ በመ/ቤት ማንነቴ ሲያስቸግራቸው መለያ መታወቂያዬ ኾኗል፡፡ “ገብሩን ታውቀዋለህ? ገብሩ ገብሩ? ገብሩ ማ? ያ መነጽር የሚያደርገው ….ሃሃሃ፡፡”
የጋሽ ዘመኑ ሚስት (የቤቱ እማወራ) በድሮው ፎቴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ ገብስማ ጠጉራቸው ከሩቁ ያበራል፡፡ ሥራ መፍታት ዕረፍት የነሣቸው ይመስላሉ፡፡ ልክ የምታባዝተውን ጥጥ እንደጨረሰች ባልቴት ያለ፡፡ ዛሬ የሚለቀም እህል የለም፡፡ ዛሬ የሚቀነጠስ ጎመን የለም፡፡ ዛሬ የሚከተፍ ሽንኩርት የለም፡፡ ዛሬ የሚላጥ ድንች የለም፡፡ ዛሬ የሚታጠብ መለኪያ የለም፡፡ ዛሬ የሚጠበቅ ስጥ የለም፡፡ ዛሬ የሚቀመል የልጅ ራስ የለም፡፡ የቤቱ ሥራ ሁሉ አልቆ የጎረቤት ሥራ ለማገዝ ጠይቃ ‘እረ ምንም የለም’ ያሏት የምትመስል፡፡ ዐይናቸውን የሚጥሉበት ስፍራ ያጡ ይመስላሉ፡፡ ልብ ብሎ ላስተዋላቸው “ይተናኮሉት ይኾን?” በሚል ስጋት እየተናጡ አምሽቶ የሚገባ ልማደኛ ልጃቸውን የሚጠብቁ እናት ይመስላሉ፡፡ ወደ ውጭ ያያሉ… ሕፃኑን የልጅ ልጃቸውን ያያሉ… ነጠላቸውን ያፍተለትላሉ… ጉሮሮው የተዘጋውን ቴሌቪዥን ዞር ብለው ገልመጥ ይላሉ…
ሕፃኑ ልጅ ወዲያ ወዲህ ይላል፡፡ አምስት ዓመት ቢኾነው ነው፡፡ ከአንዱ ደንበኛ ጭን ዘልሎ ሌላው ላይ ይፈናጠጣል፡፡ ከኔ ውጭ፡፡ እኔን ሊደፍረኝ አልቻለም፡፡ መነጽሩ እሾህ ሳይኾንበት አይቀርም፡፡ ሁለት መለኪያ እንደለጋሁ “ና እስኪ” አልኩት፤ ሊቀርበኝ ፈልጓል፡፡ ግን በየት በኩል? አያቱን ዞር ብሎ ዐየ፡፡ እንደተለመደው “ና እያለህ አይደል? ሒድ..ሒድ በል አትፍራ” ብለው ሊያደፋፍሩት አልቻሉም፡፡ መዳፉን እየፈተገ ከጠረጴዛው ጀርባ ቆመ፡፡ “ና እንጂ” አልኩት እጄን ዘርግቼ፡፡ “እንቢ አለ” በአንገቱ፡፡ ልብና አፍ አልገጥም አለ፡፡ ሆዱን እየራበው ‘በልቻለሁ’ ብሎ እንደሚግደረደረው እንግዳ ዐይነት፡፡ ሦስተኛ ዐረቂ ደገምኩና ለሦስተኛ ጊዜ “ና እንጂ” አልኩት፡፡ ጠጋ አለኝና ወደ አያቱ ሲዞር አበገነኝ፡፡ ‘እንዴት ያመነበትን ነገር አያደርግም?’ (ሕፃን መኾኑን ረስቼ) ፈራ ተባ እያለ ሲቅለሰለስ ሞቅ አለኝ መሰል መነጽሬን አወለቅኩና “በላ…ውህ” ስለው “ዋዋዋዋይ” ብሎ አያቱ ጉያ ተሸጎጠ፡፡ ሣቄን ለቀቅኩት፡፡ በዚያ ያሉት ደንበኞች በተቆጠበ ፈገግታ አጀቡኝ፡፡
የጋሽ ዘመኑ ሚስት የልጅ ልጃቸውን በጉያቸው ሸሽገው “ተው እንጂ ገብሩ ምን ነካህ? ልጅ መኾኑን ረሳህ?” ሲሉ ተቆጡኝ፡፡ ሣቄን ማቆም አቃተኝ፡፡ መነጽሬ እስኪርገፈገፍ ሣቅኩ ሃሃሃሃሃሃ… ከጓዳው በር ላይ ያለውን መጋረጃ በጇ ይዛ አስተናጋጇ ትንፈቀፈቃለች፡፡ አያት ሕፃኑን በእጃቸው ወደ ጓዳ እየገፉ፣ ወደ ጓዳ እየተሳቡ ንዴት በተጫነው ድምፀት “አንቺ ገጣጣ፣ ጥርስሽ ይርገፍ! መቼም መግጠጥ ዓመልሽ ነው፡፡ በይኮ መለኪያውን አንሺ!” አሉ፡፡ ዐይኔን ባዟዙር ባዶ መለኪያ የለም፡፡ ወይስ ዐይኔ ነው? ሰከርኩ መሰል፡፡
እኔም ተነሣሁ፡፡ “እንግዲህ ይቅርታ ማዘር” አልኩ፡፡ “ካለ ይቅርታ ይ..ቺ ዓለም ከንቱ ናት፡፡” (ተለፋደድኩ መሰል)፡፡ “ደኅና እደሩ፡፡ አይ የኔ ነገር ሞት ይርሳኝ ሒሳብ ሳልከፍል” ብዬ ሒሳቡን ጠረጴዛ ላይ አኖርኩ፡፡ “መልስ አለህ?” አለች ጥርሰ ሸራፋዋ አስተናጋጅ ሳቋ ሳያባራ፡፡ “ለነገ ይቀመጥ፡፡ ደና እደሩ፡፡”
ጠረጴዛውን የጎሪጥ ዕያዩ “ደና እደር ገብሩ” አሉ፡፡ “እረግ…እረግ…በቀደም ዕለት የዶልከውን ሙዚቃ ወዲያ አጥፋውማ ደንበኞቼ እያ….ስተኛን ነው ብለዋል፡፡ ለመኝታውማ ቤት ስንሔድ ይደርሳል ብለዋል …” ወርቅ ጥርሳቸውን ብልጭ አድርገው፡፡ “ደንበኛ ንጉሥ ነው …”
ምንም ሳልል እኔም የእጅ ባትሪየን ብልጭ አድርጌ ወደ ጨለማው ገባሁ፡፡ ወደ ቤት ልገባ ስል ..አጥር ተደግፎ ሽንቱን የሚሸና ሰው ውልብ ሲል ዐየሁ፡፡ አጥሩ ግንብ አይደለም፤ ጥቅጥቅ ያለ ስሚዛ ነው፡፡ አለፍ አለፍ ብለው በባሕር ዛፍ ይጠበቃሉ…ኾን ብለው ስሚዛውን እንደ ጨፈቃ ፣ባሕር ዛፉን እንደ ቋሚ ያዋቀሩት ይመስላል፡፡
“አንተ ባለመነጽር!” አለ፡፡ ብልግና ይኾናል በሚል ባትሪውን ዐይኑ ላይ ላለማብራት ስሽኮረመም “…አብራውና ዕየኝ፡፡ ሀገር ያወቀኝ ሰ….ካራም ነኝ” አለ፡፡
“…መነጽር የሚያደርጉ ምሁራን ናቸው ይባላል፡፡ እናንተ ምሁራን ምን ሠራችሁ? ኣ…ኣ ንገረኝ እስኪ ምን ሠራችሁ?“ ሳግ ሲያቋርጠው ወዳንዱ ባሕር ዛፍ ጠጋ ብሎ ደገፍ አለ፡፡ ባሕር ዛፉን እየዳበሰ “ንገረኛ ከዚህ ዛፍ የተሻለ ታሪክ አላችሁ? ከዚህ ዛፍ በምን ትሻላላችሁ? እንድያውም ይህ ዛፍ ይበልጣችኋል፡፡ በታሪክም በጥቅምም፡፡ ጥቅመኛ ሁላ!” ዛፉን ደገፍ ብሎ እንደምንም ቆመ፡፡ አቅቶታል፡፡ ምላሱ ግን ይሸነትራል፡፡ “የካምቦዲያውን መሪ ፖል ፖትን ታውቀዋለህ? ይሄን ባለመነጽር በመደዳ ነበር የረሸነው፡፡ ደግ አደረገ፡፡ እኔ የፖል ፖት አድናቂ ነኝ፡፡ ሃሃሃ…”
“ከዓለም ቀድማ ፊደል የቀረጸች….ሀገር ንባብን የማይወድ ትውልድ ፈጠረች፡፡ ለዘመናት በዳበረ ዕሴትና ባህል የተገነባች ናት ትሉናላችሁ፡፡ ፈሪሃ ፈጣሪ ያለባት ናት ትሉናላችሁ፡፡ የታለ? ባንድ ጀንበር የሚናድ ባህል አለ? ባንድ ጀንበር የሚናድ ዕሴት አለ? ንገረኝ፡፡ ጉም ካልኾነ በቀር ወዴት ተነነ ታድያ?“
“ምሑር በ ሐመሩ ሐ ሲኾን ምሕረት የፈሰሰ..ለት (መናገርም ሊያቅተኝ ነው ዛሬስ) ምሕ…ሕረት የተደረገለት ማለት ነው፡፡ ምሁር በሃሌታው ሀ ሲኾን የተማረ የተመራመረ ብለው አስተምረውኛል፡፡ እናንተ ከየትኛው ናችሁ? ከሁለቱም የላችሁም፡፡ ክፋት ሤራ ትጠምቃላችሁ..መጠፋፋት መታወቂያችሁ ነው፡፡ መመረቂያ ጋውናችሁን የት ነው የምታስቀምጡት ሳ…ሎን አይደለም? መማሬን ዕወቁልኝ ለማለት ቱ ደንቄም ትምርት እቴ!...”
“ሳስበው ሳስበው ሽርክ የም..ንኾን ይመስለኛል ብዬ ተጠግቼ ገብሩ እባላለሁ” ብዬ እጄን ስዘረጋ፣ ”…ክላልኝ! ጅል! እንትኔን ባልመዘመዝኩበት እንድጨብጥህ ነው?” አለና ሲሸሸኝ ክልትው አለ፡፡ ላነሣው ስጠጋ “አልፈልግም…ወግድልኝ! መጀመሪያ ራስህን አንሣ!” አለና ተፍገምግሞ ብድግ አለ፡፡
ከአጥሩ ማዶ አንድ ሰው አድፍጧል…
ዋዋዋዋ ዋው … ውሻዋ መጮህ ጀመረች፡፡ የአድፋጩ ሰውየ ሚስት (መኾን አለባቸው) “ያስደንግጥሽ እቴ! ምን ዐይታ ነው? አሁን ጅብ ያየች አትመስልም? ሰውየው “እሻ እስቲ…” ይላሉ አጥሩ ስር ፊታቸውን ለግተው፡፡
ከአጥሩ ማዶ ድምፅ ይሰማኛል… ከአጥሩ ማዶ ብርሃን ይታየኛል፡፡ ሾጠጥ ያለ ብርሃን…ብርሃኑን ተከተልኩ፡፡ አንዲት ሕፃን በሊጥ የተላገገ እጇን ይዛ ያደፈጠው ሰው ጭንቅላት ላይ ለመፈናጠጥ ትሞክራለች፡፡ ሰውየው ድምፁን ለመቀነስ እየጣረ “እሻ እስቲ …ወዲያ ክይማ” ብሎ ዐይኑን መለስ ሲያደርግ ሊጥ በሊጥ መኾኗን ተመለከተ “... እሰይ እሰይ እህል መጫወቻ … እረ የእህል ጡር አለው.. ምናለ ብትቆጫት ጥሩነሽ…” ይላል፡፡
ዐይኑ ግን እኛ ላይ ነበር፡፡
ያጮልቃል…ያጮልቃል…ያጮልቃል…
ይሄን ትዕይንት ታዝቤ ቀልቤን ስመልስ በሳግ እየተደናቀፈ ካቆመበት”…ትምርት ለሥራ እንጂ ለመኮፈሻ አይነፋም፡፡” እያለ ቀጠለ፡፡
ምን እያለ ነበር?
ዝም ብየ አዳምጠዋለሁ፡፡ ዝም ብየ ዐየዋለሁ… ዝም ብየ ሳየው ያልፈቀድኩለት እንባ ዐይኔን ሊከድነው ይታገላል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ? ሰክሬያለሁ?
ቀጠለ “…ሰምተሃል እባክህ፡፡ ምሁር አዛኝ ነው፡፡ እንኳን ለሰው፣ ለእንስሳት የሚራራ አንጀት ያለው እንጂ እንደናንተ አንጀት የሚበጥስ አይደለም፡፡ እንኳን ሰውን ኣ ኣ…እንስሳትን የሚ…ወድድ ድድ ነው…” ሲል ከጨለማው ውስጥ የፈለቀው ድምፅ አደናቀፈው፡፡ “ቁም! ማነህ? “ ያው ድምፅ ከፍ አለ፡- “ቁ..ምም ብያለሁ፡፡“
የሰውየውን ድምፅ ውሻዋ ታጅበዋለች፡፡ አሳዳሪዋን እምቧለሌ እየዞረች (‘አለሁልህ’ ለማለት ያህል) ዋዋዋዋ ዋው ዋዋዋዋ ዋው ዋዋዋዋ ዋው ዋው…“ ስትል ታክላላለች፡፡
ትንፋሹን ሰብስቦ “…ያለኝ ሀብት ሽንቴ ነው፡፡ ትቼልሃለሁ፤ ያው ውሰድ! ሃሃሃ…”
ዋዋዋዋ ዋው ዋዋዋዋ ዋው ዋዋዋዋ ዋው ዋው…
“ውሻ አልወድም፡፡ …ማርያምን ውሻ አልወድም …” ይላል ለመሮጥ እያኮበኮበ፡፡
“ቁም! ብያለሁ፡፡”
“እንትንህ ይቁም!“
ይሮጣል…ይሮጣል…ይሮጣል…ይሮጣል…
… የሰከረ ሰው እንደዛ ይሮጣል? …ዐውቆ ዐበድ እንደሚባለው ዐውቆ ሰከር አለ ይኾን?
ወደ ቤቴ ልገባ በር ላይ ቆሜ አድራሻቸው ያልታወቁ የድምፅ ብናኞች ጆሮዬን ያሳክኩኝ ጀመሩ፡፡ “ያዘው ያዘው ሌባ ነው… ያዘው…” ሰፈሩ ተቀወጠ፡፡ ሰፈሩ ባንድ እግሩ ቆመ፡፡ ተዘግተው የነበሩት በሮች እዚህም እዚያም መከፈት ጀመሩ፡፡ ጓጓጓ… ሲጢጢጥጥ … ተከፍተው የነበሩት በሮች እዚህም እዚያም መዘጋት ጀመሩ… ድው ድው ኳኳኳ…“ምንድን ነው? ማነው ?”
“…በሸራፋ ጥርስ እንዲህ ተስቆ፣ አማረልኝ ብለሽ ነው? ጥርስሽ ይርገፍ! አንቺ ገጣጣ በሩን ዝጊ እኮ ነው የምልሽ” የሚል ድምፅ ኩስስስ እያለ ጆሮዬ ላይ ተጋድሞ ይወድቃል፡፡ ከየት ነው?
Saturday, 22 February 2025 12:26
ገብርሻ!
Written by ሙሉጌታ ቢያዝን
Published in
ጥበብ