የአማርኛ ግጥም ታሪክ ከቃል እስከ ጽሑፍ ሰንሰለቱ ረዥም፣ ጉዞውም ሩቅ፣ ሕዝባችንም የግጥም ወዳጅ ነው ይባላል። በዚህ የተነሳ ሀገራችንም የግጥም ሀገር መባሏ የሚያከራክር አይደለም። ይሁን እንጂ ከቃል ግጥሞች አልፈን ወደ ኅትመቱ ስንመጣ የአንባቢው ፍላጎት ብዙ የሚያረካ አይደለም። በርግጥ ከተሜውም ገጠሬውም የመስማትና ሥነቃላዊ ፍቅሩ ዛሬም የጋለ ይመስላል።
ዘመናዊ ግጥም ካበበበት የእነ መንግሥቱ ለማ፣ የእነ ጸጋዬ ገብረመድህኅን ዘመን ወዲህ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በርካታ የግጥም ምንጮች ገንፍለው ምድሪቱን አጥለቅልቀዋታል። ግን ደግሞ ብዙዎቹ የቁጥራቸውንና የጫጫታቸውን ያህል የተዋጣላቸው አይደሉም።
ግጥም የስሜት ጡዘት ውጤትና የወጣትነት ዕድሜ ምርጫ እንደመሆኑ ወጣቶች እንደ ቢራቢሮ ፍቅር አበቦች ላይ እያረፉ ቀስመው፣ በወረቀት ላይ ማር መጋገራቸው በየቱም የዓለም ክፍል የተለመደ ነው። ከዚህ አንጻር፣ ወጣቶች በሚበዙባት ሀገር ለምን የግጥሞች ኅትመት በዛ አይባልም። በፍቅርም ጉዳይ እንደ ቀደሙት ዘመን ደራስያን ሸፈንፍን አይሉም። ይልቅስ በአደባባይ በይፋ መተረክ ከጀመሩ ከራርሟል። ስለዚህም ባብዛኛው የዘመኑ ግጥሞች ፍቅር ተኮር ናቸው። ይሁንና ባይበዙም ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ይካተታሉ።
በአጠቃላይ ከምንጊዜውም ይልቅ የግጥም መጻሕፍት አደባባዮችን መሙላታቸው ግር ቢለንም፣መልስ ሊሆኑን ይችላሉ የምንላቸው ግምቶችም ግን አሉ። ከነዚህ ግምቶች አንዱ በየአዳራሹ ይካሄዱ የነበሩ የሥነጽሑፍ ምሽቶችና ዝግጅቶች የፈጠሩት መነቃቃትና መነሳሳት ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ “ጦቢያን” የመሳሰሉ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ለመነሳሳቱ እንደ ሰበብ ሊወሰዱ ይችላሉ።
ታዲያ የመጻሕፍቱ ኅትመት ብዛት አነጋጋሪ ከመሆኑም ባሻገር፣ብቻውን እንደ ስኬትና ዕድገት ሊታሰብ አይችልም። ምክንያቱም ገበያ ላይ ከወጡት አብዛኛዎቹ ዘመን ተሻጋሪም ብስለታቸው አርኪና አመርቂም አይደለምና፣ማለትም ጥሩ ግጥም ማሟላት የሚገባውን አያሟሉም። አልፎ አልፎ ከወንበር የሚነቀንቁት ጥቂቱ የግጥም ሥራዎች የሚገርም ጥበብና ብስለት ያላቸው ስለሆኑ ለዘመኑ የጥበብ ዓለም ተስፋ ይሰጣሉ።
በዙ ከሚባሉት የታተሙ ግጥሞች፣አንዳንዶቹ ደግሞ ለወደፊት የተሻለ ሆነው ሊመጡ የሚችሉና ጥሩ ቁመና ላይ ያሉ፣የስኬት ደፍ ላይ የቆሙ ናቸው። ገጣሚዎቹም ከዕድሜያቸው አንጻር ሲታዩ ብዙ ይሠራሉ ብለን እርሻ ላይ እንዳሉ ቡቃያዎች በጉጉት የምንጠብቃቸው ዓይነት ይመስላሉ።
እንደነዚህ ካሉትና የተስፋ አጸድ ውስጥ ከቆሙት መካከል ፈክቶ የሚታየው በቅርቡ “የዱር አበባ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተመው ቴዎድሮስ ካሳ የተባለው ወጣት ገጣሚ ነው። ይህ ገጣሚ ከዕድሜው አንጸር በጣም የተሻለና አንዳንድ የራሱ የሆኑ መልኮች ይዞ የመጣ በመሆኑ ቀጣይ መንገዱን የሚያሳዩ በርካታ ፍንጮች አሉት።
መጽሐፉም በ100 ገጾች 24 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ግጥሞቹ ረዣዥም ናቸው። በሌላ በኩል፣ በቅርብ ጊዜያት በወጣት ገጣምያን የተለመዱት ዓይነት አጫጭርና መዝጊያቸው አካባቢ ያልተጠበቀ ዓይነት አጨራረስ ያላቸው አይደሉም። ግጥሞቹ በጭብጥም እንደተለመደውና በወጣትነት እንደሚጻፉ ግጥሞች በጾታዊ ፍቅር፣በተለይም በኢሮስ የተሞሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ለገጸሰቡ ሁለነገር ስለሆነች ሌላ ገጸሰብ የሚናገረውንና የሚያስጌጠውን አንዱን የፍቅር ግጥም ማየት በቂ ነው።
እነሆ!
ሽሙንሙን ሽሙንሙን
የማትጠገቢ
አንቺ ቆንጆ
የቆንጆ ቋት
የልብ ጌጥ
የዓይን መብራት።
አንቺ ገንቦ
የፅጌ ማፍያ፣
ቢራቢሮ
ዓይን ማረፊያ።
አንቺ ንጋት፣
ገላጭ
ብራ
አንቺ ኮከብ
ፀሐይ
ጮራ
አንቺ ፀዳል
የውበት ኩል
የት እንጣሽ
በዬት በኩል!?
ወቅትም አንቺ
በልግ
በጋ
ሀገር አንቺ
ቆላ
ደጋ
አንቺው መዓልት
ምሽት
ንጋት
አንቺው ዕድሜ
ማታና
ጧት።
እዚህ ጋ ገጣሚው በለዋጭ ዘይቤ ኳሽቶ የሚያቀርባት ገጸሰብ ዝንጉርጉር ናት። በሁሉም ትመሰላለች። የቆንጆ ቋት ናት-የልብ ጌጥ! ደግሞ የዓይን መብራት። የጽጌ ማፍያም ናት፣ቢራቢሮም። ፀሐይም፣በልግም በጋም፣ቆላም ደጋም አድርጓታል። ይህ እንግዲህ ትርጉሙ ብዙ ሊሆን ይችላል። የስሜት ፍርርቅም ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ንጋትም ምሽትም ስትሆን፣ፀሓይም ጨረቃም አርግዛ ነው።
ማቀማጠል እንዲህ ነው። በፍቅር ዓለም ሰማይ መዝለቅ ኮከብ መፍጠርም አይሳንም።
ስለ ሕይወት ፈትልና ውስብስብ መንገድና መልክ የምትናገር ግጥም አለችው።
የአብሮነት በረከት ትላለች። እንዲህ፣
እናንተ ‘ሩቃን ፣
ቅረቡ።
ክበቡ ወደገበታው፣
ልባችንን አሰናኝተን
የሕይወትን ቅኔ እንፍታው።
ወዲህ በሉት፣
ኹል ሁሉን
ገበታውን፣ወይኑን፣ዘቢቡን።
ደግሞ እንዝፈን፣
አቀብሉኝ ያንብ መቃ
ደግ ስራን እንዋልለት፣
ለ’ራሱ ርቃን መሆን ባይችል
የእኛን እርቃን እንጋርድበት።
እያለ ይቀጥላል።
ይህ ሌላ ዓለም ነው። ሌላ የሕይወት መልክ ነው። ድፍርሱን ለማጥራት፣ሁከቱን ለማርጋት ገጸሰቡ የራሱን መንገድ፣የራሱን መላ ይመታል።
ሌላው ግጥም፣
ድል መስሎን...
በሙታን መኃል አሾርናት
ነፍሳችንን ያለ ዓቅሏ፣
በፍቅር እሳት አቃጠልናት
ልባችንን ያለ በደሏ፣
ቢጤ ቢጠፋ እኩያ
አደርን ከሃሳብ ጉያ፣
የነበልባሉ ወላፈን
ወበቁ በሩቅ ቢጋረፍ፣
ለአንዲት መናኛ ሕይወት
የሃሳብ ሰይፈኛ ቢሰለፍ፣
ምንድነው ሰው ቁምነገሩ
ከማበብና ከመርገፍ!?
ግጥሙ አሳዛኝ፣ጠያቂና እንቆቅልሽ ያለበት ቢሆንም፣በሌላ ቅኝት “እናምልጠው፣እንሽሸው “ብሎ የማርያም መንገድ እየፈጠረ ይመስላል።
በቅርጽ ሌሪክ የበዛባቸው የቴዎድሮስ ግጥሞች በአሰነኛኘት ጥሩ ተደርገው ተደርድረዋል።
ከአንድ ሌላ የፍቅር ግጥሙ ጥቂት ስንኞች ተውሼ ዳሰሳዬን ብቋጭ የሚበቃ ይመስለኛል።
“ልጃገረድ ሕይወት” ነው ርዕሷ።
በወደዷት ቁጥር
ቃጠሎዋ ‘ሚንር
በወደዷት ቁጥር
ሰይፏን የምትስል፣
በወደዷት ቁጥር
አንጀት የምትበጥስ፣
ተለሳልሳ ገብታ
እሳት የምትለኩስ፣
እያለ ይቀጥላል።
ሌላም ነፍስ የምታስደንስ ግጥም አለችው። ርዕሷ “የሌሊት ሽክሹክታ”ይላል።
ጥቂት ስንኞች እዋሳለሁ።
በተንጣለለው ሌት፣...
አንተም እንደስንኝ
አንተም እንደኖታ፣
ታስውባለህና፣የሌሊቱን ቅኝት የሌሊቱን ኖታ፣
እባክህ አትንቃ፣
ነፍስህን አትጠራት፣ወደ እስር በረቷ።
አካልህን ጥለህ
ሆነው ሌሊቱ ኩል፣
ግጥም መጻፍ ልመድ
በዝምታህ በኩል።
ብዙ ስፍራ ላይ ወይን፣ዘፈን ዳንስ የሚጠቀስባቸው ግጥሞች እዚህም እንዲህ ከፍ ብለዋል።
ከወይኔ ቅመስ
ከፍቅሬ ጠጣ፣
ከሃሳቤ ጠለቅ
ከመኖሬ ዕጣ።
ከእርሻዬ ዝለቅ
ፍሬ እና አበባ፣ከማበቅልበት
ከጎጆዬ... ና!
ብቻዬን ስሆን ከማለቅስበት፣
ና! ካንገቴ ስር
ሙቀቴን ለካ፣
ና! ከደረቴ
ከትርታዬ ጠጥተህ እርካ።
ይህ የግጥም ጥራዝ፣አያያዙ ጥሩ፣ከዕድሜው ጋር ሲተያይ ተስፋ ሲጪና ብሩህ ሕልም የሚያሳይ ነው። ቢሆንም መስተካከልና መሻሻል ያሉባቸው ነገሮች አሉ። ብዙ የሀገራችን ገጣምያን ችግር የሆነው የቤት አመታት ላይ ያሉ ፈተናዎች አሉበት።
ይሁንና፣ ለወጣት ሁልጊዜም የለውጥና የዕድገት ዕድል ስላለ ጊዜ ሰጥቶ ቢያነብብ፣ ከዚህ ከፍ ብሎ እንደሚመጣ ጥርጥር የለኝም። በሕይወቴ ያየሁትና የታዘብኩት ነገር፣ ምክር የሚሰሙና ራሳቸውን ለመለወጥ የሚተጉ ሰዎች ያለጥርጥር ያድጋሉ። ይህ ጥሩ ዳና፣መልካም መዓዛ ያለው ወጣት ገጣሚ፤ በሚቀጥለው ዘመኑ ከፍ ብሎ በጎመራ ፍሬ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
Saturday, 22 February 2025 12:28
የቴዎድሮስ ካሳ ግጥሞች!
Written by ደረጀ በላይነህ
Published in
ጥበብ