Saturday, 01 March 2025 21:31

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአማራ ክልል “ተፈጽሟል” ያሉትን የድሮን ጥቃት አወገዙ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ “አነገሽ” በተባለ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ “ሐሙስ ገበያ” በተባለ ስፍራ “ተፈጽሟል” ያሉትን የድሮን ጥቃት አውግዘዋል። ፓርቲዎቹ ጥቃቱን “የጦር ወንጀል” ሲሉ ጠርተውታል።
እናት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢሕአፓ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ በጋራ፣ ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ በዚሁ የድሮን ጥቃት ታዳጊ ህጻናትን ጨምሮ 16 ንጹሃን ሰዎች እንደተገደሉና ሌሎች 11 ሰዎች ክፉኛ እንደቆሰሉ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው እንደጄኔቫ እና ዘኼግ ያሉ ስምምነቶች፣ እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ እንደሰፈረው በጦርነት ወቅት ንጹሃን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትም የጦር ዒላማ መኾን እንደሌለባቸው ቢደነገግም፣ “መንግስት ግን መሰል ድንጋጌዎችንና አገር እየተመራችበት ያለውን ሕገ መንግስት ጭምር በጣሰና ሃላፊነት በጎደለው አኳኋን እንዲመራቸው ጭምር የመረጡትን ንጹሃን ዜጎችን፣ የጤና ተቋማትን፣ ትምሕርት ቤቶችን፣ የዕምነት ቦታዎችን የጥቃት ዒላማ ካደረገ ውሎ አድሯል” በማለት እነዚሁ ፓርቲዎች ነቅፈዋል።
ፓርቲዎቹ መግለጫቸውን ሲቀጥሉ፣ መንግስት ፖለቲካዊ ድክመቱን ለመሸፈን “የጸጥታ ሃይሉን ወደ ፖለቲካው በመሳብና እንዲህ ያሉ በጦር ወንጀል ጭምር የሚያስጠይቁ የንጹሃን ጭፍጨፋ፣ መሰወርና የዘፈቀደ ግድያዎችን እንዲፈጽም የእጅ ጥምዘዛ ያህል እያስገደደውና እያሳሳተው ይገኛል” በማለት ከስሰዋል።
አክለውም፣ “መንግስት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰከነና ቀልብ እየገዛ ከዚህ ዓይነት ሃላፊነት የጎደለው ተግባሩ ‘ይታቀባል’ ሲባል፣ የጥቃት አድማሱን እያሰፋ፣ ከመጸጸት ይልቅ በዕኩይ ድርጊቱ ይበልጥ እየተኩራራ፣ ለዕድገት ይውል የነበረን ከፍተኛ የአገር ሃብት ሰበብ እየፈለገ ለንፁሃን ጥቃት እያዋለው ይገኛል” ሲሉ ፓርቲዎቹ አመልክተዋል።
ጥቃቱን “መንግስታዊ ሽብር” እና “የጦር ወንጀል” ሲሉ የጠሩት ፓርቲዎቹ፣ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች እንዲቃወሙት ጠይቀዋል። አያይዘውም፣ ፓርቲዎቹ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ እናት ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል፣ ጅማ ዞን፣ ጌራ ወረዳ ከየካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰተው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች “አሁንም ያላስረከባችሁትን የጦር መሳሪያ አምጡ” የሚል ግፊት እየደረሰባቸው መሆኑን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በዚሁ መግለጫ ላይ ከቀድሞ ቀያቸው ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ካፋ ዞን፣ ጊምቦ ወረዳ የተፈናቀሉት እነዚሁ ነዋሪዎች፣ በወረዳ አስተዳደሩ አማካይነት በትምህርት ቤቶችና ድንኳኖች ተጠልለው ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል።
ይሁንና “በዜጎች ግድያና ቤት የማቃጠል ወንጀሎች የተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ለፍርድ አለመቅረባቸው ችግሩን አባብሶታል” በማለት አጽንዖት የሰጠው እናት ፓርቲ፣ በአካባቢው ሰፍሮ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የማረጋጋት ስራ እንዲሰራና መንግስትም ቤታቸው ተቃጥሎባቸው በድንኳኖችና ትምሕርት ቤቶች የተጠለሉ ነዋሪዎች በአፋጣኝ መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቋል።

Read 991 times