Saturday, 01 March 2025 21:33

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከጠብ አጫሪነት እንዲታቀቡ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት ወደ ጦርነት ከሚያስገቡ ጠብ አጫሪ ድርጊቶች መቆጠብ እንዳለባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ለሁለቱም አገራት የተሻለ ቀረቤታ ያላቸው ወገኖች የእርቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት መካከል የተፈጠረው የቃላት ጦርነት የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፤ አገራቱ ወደ ጦርነት እንዳይንደረደሩ በርካቶች ስጋታቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪና የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ምሁር አቶ ኢያሱ ሃይለሚካኤል ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለረዥም ጊዜ የቆየ ፍትጊያ እንደነበረና አሁን የሚስተዋለው የቃላት ግጭት ከፖለቲካዊና መልክዓምድራዊ ጉዳዮች ጋር እንደሚገናኝ ይገልጻሉ፡፡
“የሁለቱ አገራት ፍትጊያ በበርካታ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ውስጥና በተለዋዋጭ ሁኔታዎች መካከል የዘለቀ ነው” የሚሉት አቶ ኢያሱ፤ በተለይም ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀችበት ጊዜ በኋላ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በሰፊው መስተዋላቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አክለውም፤ በቀድሞው የኢሕአዴግ መንግስትና በኤርትራ መንግስት መካከል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ ልዩነቶች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
ለአብነት ያህል፣ ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከድንበር ይልቅ የኢኮኖሚ ጉዳይ መነሻ ምክንያት እንደነበር እኚሁ ምሁር አስረድተዋል። ጦርነቱ በአልጀርስ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የዘለቀው ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ፣ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንደታደሰ ጠቅሰዋል።
በኢጣልያ ለረዥም ዓመታት በኤርትራ የተተከለው የቅኝ ግዛትና ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሁኔታ ያስከተለው ተጽዕኖ ኢትዮጵያና ኤርትራን ሲያጋጭ መቆየቱን ያወሱት አቶ ኢያሱ፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የከረመው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፕሪቶሪያ ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት ሲቋጭ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት አዳዲስ ጥያቄዎች እንደቀረቡ አመልክተዋል። ከእነዚህም ጥያቄዎች ውስጥ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ አንዱ እንደሆነ በማንሳት፣ ይህንን ጥያቄ ለማሳካት የኢትዮጵያ መንግስት አጥቂ (offensive) የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መከተሉን አስረድተዋል።
አቶ ኢያሱ “የባሕር በር ጥያቄ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር እያደገ የሚመጣ ጥያቄ ነው። ይኸው ጥያቄ ግጭትና ጦርነትን ሊፈጥር ይችላል። በእነዚሁ ሁኔታዎች የሚፈጠረው ጉዳት ከፍተኛ ይሆናል” በማለት ማብራሪያቸውን ቀጥለው፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን እንደፈጠረ ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚስተዋሉ በሁለቱ አገራት የሚሰነዘሩ የቃላት ምልልሶች፣ በአገራቱ መካከል የተፈጠረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መቀዛቀዝ ምልክት መሆናቸውን አያይዘው ገልጸዋል።
“የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መርገብ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት እያሻከረው መጥቷል” ያሉት ምሁሩ፤ “ሁለቱም አገራት ወደ ጦርነት የሚሄዱበት ጊዜ አጭር ባይሆንም፣ የተወሰኑ የእርስ በርስ ትንኮሳዎች ሊኖር እንደሚችሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል።
“እንደ አገር ከአሁኑ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል። የቀይ ባሕር ጉዳይ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ያሉበት አካባቢ ነው” ያሉት አቶ ኢያሱ፤ ጦርነቱ ከተጀመረ የውጭ ሃይሎች ተጽዕኖ ሊታከልበት እንደሚችል ጠቅሰዋል። “የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ወደ ጡዘት ደረጃ ደርሷል። ከዚህም ባሻገር፣ የውክልና ጦርነት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ኤርትራ ይህንን ጦርነት ለማድረግ የኢኮኖሚ አቅም ‘አላት ወይ?’ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው” ብለዋል።
ከዚህ የጦርነት ስጋት ለመውጣት “መፍትሔው ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው አቶ ኢያሱ በሰጡት ምላሽ፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ቀረቤታ ያላቸው መንግስታት፣ ተቋማትና ቡድኖች የእርቅ እንቅስቃሴ የሚጀምሩበት መንገድ ቢፈጠር፣ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ በምሳሌነት ሩሲያ፣ ቻይና እና እንደ ኢጣልያ ያሉ የአውሮጳ አገራት፣ ብሎም የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችና ሳዑዲ አረቢያ ይህንን የእርቅ እንቅስቃሴ “መጀመር ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም፣ በሁለቱም አገራት በኩል ከጠብ አጫሪ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት አቶ ኢያሱ፤ “ከብሔራዊ ጥቅም አንጻር በኢትዮጵያ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
ከሁሉም በላይ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጥንቃቄ መያዝ ያለበት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

Read 1360 times