• ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬንን ማዕድን እወስዳለሁ ማለታቸው ከኛ ጋር ምን አገናኘው?
የአሜሪካ (የUSAID) እርዳታ የተቋረጠባቸው ድኻ አገራትና ተቋማት የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተዋል። እንደ ድሮ ቢሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት ላይ ወቀሳና ውግዘት ያወርዱበት ነበር። ዛሬ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ግን፣ የድሮው ልምድ አያዋጣም።
“እርዳታ አልተሰጠንም” ብለው ቢሳደቡ፣ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። እና ምን ቢሉ ይሻላል? ምንም እየተናገሩ አይደለም ማለት ይቻላል። በእርግጥ፣ “ሌሎች የእርዳታ አማራጮችን ማፈላለግ አለብን” ብለው የሚናገሩ አልጠፉም። አንዳንዳቹ ስለ ጨነቃቸው ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ፊት ለፊት ሳይሆን በተዘዋዋሪ የእልህ ብሽሽቅ ውስጥ መግባት ስለሚያምራቸው ነው።
በዚህም በዚያም የተሳካላቸው አይመስልም። በጭንቀትም ይሁን በብሽሽቅ ስሜት፣ “ሌሎች የእርዳታ አማራጮች” ተፈልገው አልተገኙም። በዚህ መኻል ነው ሌላ ዱብዳ በድኻ አገራት ላይ ከሰሞኑ የመጣባቸው።
በ6 ዓመታት ለኢትዮጵያ የተሰጠ እርዳታ በቢሊዮን ዶላር
አሜሪካ 6.2
እንግሊዝ 2
አውሮፓ ሕብረት 1
ጀርመን 0.75
ለኢትዮጵያ በየዓመቱ እርዳታ የሚሰጡ ዋናዎቹ ለጋሽ አገራት፣ አሜሪካና እንግሊዝ ናቸው። የአውሮፓ ህብረት በጥቅሉ እንዲሁም፣ ጀርመንና ኔዘርላንድ የመሳሰሉ አገራት በተናጠል ተጨማሪ እርዳታ ይሰጣሉ።
አሜሪካ በስድስት ዓመታት ውስጥ 6 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለኢትዮጵያ እንደሰጠች የገንዘብ ሚኒስትር ዓመታዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ የድርቅ ተጎጂዎችንና ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ከዓመት ዓመት የእህል እርዳታና ዘይት የሚመጣው ከአሜሪካ ነው።
የእህል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው አንዳንዴ ከ10 ሚሊዮን ይበልጣል። ከ5 ሚሊዮን በታች ግን ወርዶ አያውቅም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት የሚሻገሩት በእህል እርዳታ ነው። አለበለዚያ በረሀብ ብዙ ሕዝብ ያልቃል።
እንግሊዝ በስድስት ዓመታት ውስጥ 2 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለግሣለች። የአውሮፓ ህብረት 1 ቢሊዮን ዶላር። ጀርመን 0.75 ቢሊዮን ዶላር።
የአሜሪካና የእንግሊዝ እርዳታ እየተቋረጠና እየቀነሰ ሲመጣ፣ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ላይ ትልቅ የኢኮኖሚ ምስቅልቅል እንደሚፈጥር አትጠራጠሩ፡፡ ግን የባሰስ አይመጣም ወይ? የአውሮፓ ሕብረትና እንደ ጀርመንና ኔዘርላንድ የመሳሰሉ አገራትስ እርዳታ አይቀንሱም ወይ?
ቀድሞውንም እርዳታ ከየአቅጣጫው እየቀነሰ እንደሚመጣ መገመት ይቻል ነበር፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ግን እንደ ጉድ አፈጠኑት፡፡ በዚህ አካሄዳቸው፣ በሌሎች እርዳታ ሰጪ አገራት ላይም ጫና ማሳደራቸው አይቀርም - በእንግሊዝ ላይ እንደታየው፡፡ እንዴት?
ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬንን ማዕድን እወስዳለሁ ማለታቸው ከኛ ጋር ምን አገናኘው?
የአሜሪካ መንግሥት ዕዳ ከ36 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። በሌላ አነጋገር እየተበደረ ነው የእርዳታ ገንዘብ የሚመድበው። በእርግጥ በዓመት የሚመደበው የ60 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ፣ ከመንግሥት በጀት ጋር ሲነጻጸር 1 በመቶ ያህል ብቻ ነው። ቢሆንም ግን ‹እየተበደረ እርዳታ ይሰጣል ተብሎ ሲወራ አሜሪካውያንን ግራ እንደሚያጋባቸው አያጠራጥርም።
በዚያ ላይ ለዩክሬን የተሰጠ ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ አለ። ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሉት ደግሞ፣ እስከ 350 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።
አሜሪካ በየዓመቱ እየተበደረች ነው ይሄን ሁሉ እርዳታ የምትሰጠው? ለዶናልድ ትራምፕ እንደ እሬት ነው የመረራቸው፡፡
ዓለምን ሲያወዛግብ የሰነበተው ትልቁ ዜና ግን ሌላ ነው። ‹እርዳታው እንደ ብድር መቆጠር አለበት፤ ብድር ደግሞ መመለስ ይኖርበታል‹ ብለዋል ፕ/ት ትራምፕ።
በርካታ ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት… እነ ቢቢሲ እነ ሲኤንኤን የትራምፕን ንግግር እንደ መሳለቂያ ነበር የመሰላቸው። ‹የትራምፕ ነገር‹ ገና በደንብ አልተዋጠላቸውም። እውነት እውነት አልመስል ብሏቸዋል። ለዩክሬን የተሰጠ እርዳታ እንደ ብድር ተቆጥሮ መመለስ አለበት? ለበርካታ ጋዜጠኞች እንደ ቀልድ ነው የሆነባቸው። ነገሩን እንደ ቅዠት ይቆጠራል ብለው የተናገሩ የፖለቲካ ተኝታኞችም ጥቂት አይደሉም።
ዶናልድ ትራምፕ ግን ከምራቸው ነው የተናገሩት። ብዙዎቹ ተንታኞችና ጋዜጠኞች ከእስከ ዛሬው ልምድ አልተማሩም ማለት ነው። ወይም ‹ከምር ሊሆን ይችላል‹ ብለው ለማመን አልፈለጉም።
ዩክሬን ከአሜሪካ ያገኝችውን እርዳታ በቀጥታ መመለስ እንደማትችል ይታወቃል። ዶናልድ ፕራምፕ ግን ምላሽ አዘጋጅተዋል። “ዩክሬን ብዙ የከርሰ ምድር ነዳጅ አላት፤ ሌሎች ውድ ማዕድናትም አሏት” ብለዋል - ትራምፕ። የአሜሪካ ኩባንያዎች ነዳጅና ማዕድን ቆፍረው እንዲያወጡ ዩክሬን መፍቀድ አለባት። ከማዕድንና ከነዳጅ ከሚገኘው ገቢ ለአሜሪካ መክፈል ትችላለች ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
አሁንም በርካታ ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት የትራምፕን ንግግር እንደ ነውር ወይም እንደ ቅዠት ነበር የቆጠሩት። ‹የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፣ የትራምፕን ሐሳብ አይቀበሉም‹ የሚሉ ዜናዎችንና ዘገባዎችን በሰፊው አሰራጭተዋል። ጉዳዩ በዚሁ ተድበስብሶ እንዲያልፍ ነበር የተጠበቀው፡፡ ‹እርዳታ ብድር ነው‹ የሚለው ጉዳይ ተረስቶ ወደ ሌላ ዕለታዊ ርዕሰ ጉዳይ የሚሸጋገር ነበር የሚመስለው።
ግን አልሆነም።
የራሺያ ጦር ዩክሬንን የወረረበት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ከሰሞኑ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲዘከር ሰንብቶ የለ! ለዩክሬን ተጨማሪ ድጋፍ ለማስገኘት እንደሚረዳም ተገምቶ ነበር።
ራሺያ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ አማካኝነት ውግዘት እንዲደርስባት፣ ዩክሬን “የውግዘት መግለጫ” አዘጋጅታ አቀረበች። እንደተለመደው ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገራት በኩል ድጋፍ አግኝቶ እንደሚጸድቅ ጥርጣሬ አልነበራትም።
ትራምፕ ግን ሌላ “ለዘብተኛ መግለጫ” አዘጋጅተው ለተመድ ጉባኤ ልከዋል። ራሺያን የሚያወግዝ አይደለም። ጦርነቱ መቆም አለበት የሚል ሐሳብ የያዘ ነው። ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት “ጉድ ነው፤ ጉድ ነው” ብለው ዘገቡ። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪም ወዲያውኑ የትራምፕን ሐሳብ ውድቅ አደረጉት።
ትራምፕ ከሐሳባቸው ንቅንቅ አላሉም። እሳቸው በአጸፋው የዩክሬንን መግለጫ ውድቅ አደረጉት። በዩኤን ጉባኤ ላይ የአሜሪካ አምባሳደር ለመጀመሪያ ጊዜ ከራሺያ ጋር በመወገን ድምጽ ሰጡ።
ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት ነገሩ ሁሉ ግራ ሆነባቸው። እኚህ ዶናልድ ትራምፕ ነገሩን አምርረው ይዘውታል ማለት ነው እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ!
ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት እንዴት ነው የተጋረደባቸው? እስካሁን የዶናልድ ትራምፕን አቋም በደንብ መገንዘብ ነበረባቸው። እንደ ቀልድ እየቆጠሩት እስከ መቼ ለመዝለቅ እንደፈለጉ እንጃ!
ትራምፕ በየዕለቱ አቋማቸውን እየደጋገሙ መናገራቸውን አላቋረጡም። “ዩክሬን 350 ቢሊዮን ዶላር መመለስ አለባት። ለዚህም የከርሰ ምድር ነዳጅና ውድ ማዕድናትን በማስያዣነት አቅርባ ትፈርም” ብለው እንደገና ተናግረዋል። “ሊሆን የማይችል ነገር ነው፤ ቅዠት ነው” ሲሉ ብዙዎች ተችተዋል።
በማግስቱ ግን፣ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የስምምነት ውል ለመፈራረም ፈቃደኛ እንደሆኑ ገለጹ።
“ዓለም ክው አለ” ቢባል ይቀልላል።
ዶናልድ ትራምፕስ ምን አሉ?
“ዩክሬን መፈረም አለባት፡፡ የግድ ነው። አሜሪካ ገንዘቧን መልሳ ታገኛለች። ጦርነቱ እንዲቆም አሜሪካ ጫና ታደርጋለች። ለዩክሬንም ለራሺያም የሚበጅ የሰላም ስምምነት ይፈጠራል። የአውሮፓ አገራት ለዩክሬን የወደፊት ሕልውና አለኝታና ዋስትና መስጠት አለባቸው” ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ በአውሮፓ አገራት ላይ ያላቸው ቅሬታ - ‹ለአሜሪካ ሸክም ሆነውባታል‹!
አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት “ኔቶ” በተሰኘው የጋራ ወታደራዊ መከላከያ ውስጥ የታቀፉ ናቸው - ከአሜሪካና ከካናዳ ጋር። ምንም እንኳ አንዳንዶቹ አገራት ደህና የመከላከያ ኀይል የገነቡ ቢሆኑም፣ በአብዛኛው ግን በአሜሪካ ኀያልነት ላይ ነው የሚተማመኑት። በአሜሪካ ከመተማመናቸው የተነሳም፣ ቀስ በቀስ የመከላከያ በጀታቸውን በጣም እየቀነሱ ቸል እስከማለት ደርሰዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን አልታገስም ባይ ናቸው። የአውሮፓ አገራት የመከላከያ በጀታቸውን ካልጨመሩ፣ በአሜሪካ ትከሻ ላይ ተቀምጠው መቀጠል አይችሉም ብለዋል - ትራምፕ። የየራሳቸውን ድርሻና ኀላፊነት የማይሸከሙ አገራት፣ ከራሺያም ሆነ ከቻይና በኩል ጥቃት ቢመጣባቸው፣ አሜሪካ እንድትደርስላቸው መጠበቅ አይችሉም ሲሉ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።
በዚህ መኻል ነው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታመር ሰሞኑን ድንገተኛ መግለጫ የሰጡት። ለእርዳታ የምንመድበውን በጀት ቀንሼ፤ ለመከላከያ ኀይል ተጨማሪ በጀት እጨምራለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትና በርካታ ጋዜጠኞች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዐይነት ንግግር አልጠበቁም። ግን ብዙም አልተጯጯሁም። አሁን አሁን እየገባቸው ሳይሆን አይቀርም። የዶናልድ ትራምፕ ንግግርና ማስጠንቀቂያ ‹ከምር” ሊሆን ይችላል ብለው ማሰብ የጀመሩ ይመስላል።
የዶናልድ ትራምፕ ጫና በእንግሊዝ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ሌሎች የአውሮፓ አገራትም ላይ የበጀት ለውጦችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ለመከላከያ ኀይል በጀት ሲጨመር፣ ለእርዳታ የሚመደበው በጀት መቀነሱስ ይቀራል?
እንግዲህ፣ የእርዳታ ነገር፣ በዶናልድ ትራምፕ፣ በዩክሬን፣ በእንግሊዝ በኩል እንዲህ ተያይዞ እየተተረተረ ነው፣ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት ፈተና የሚሆንባቸው፡፡