ደሳለኝ የኔአካል - ጠበቃና የህግ አማካሪ
የአድዋ ድል መልከ ብዙ ነው። ሁሉም ራሱን እያስመሰለ ይስለዋል። ራሱን እያስመሰለ ቢስለው ችግር አይደለም። ምክንያቱም የሁላችንም መልክ አድዋ ላይ አለ። ችግር የሚሆነው አድዋ እኔን ብቻ ይመስላል ካልን ነው። ለምሳሌ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናልና፣ ‘እግዚአብሔርን እመስላለሁ’ ብንል ስህተት አይሆንም። እግዚአብሔርን የምመስለው እኔ ብቻ ነኝ ካልን ግን ስህተትም ኃጢአትም ይሆናል።
እንግዲህ ወሩ የካቲት ነውና፣ ሁላችንንም የሚመስለውን አድዋን እናስታውሳለን። ዛሬ አድዋን የምናስታውሰው ብቻውን አይደለም። የተለመደውንና ስለ አድዋ በጠቀስን ቁጥር ከአፋችን የማንነጥለውን የአዘቦት አረፍተ-ነገራችንን አብረን እናስበዋለን። ይህ አረፍተ ነገራችን “እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ስልጡን የጣልያን ሰራዊት በኋላቀር መሳሪያ...” ብሎ የሚጀምር፣ ከድሉ እኩል ዝነኛ የሆነ አረፍተ ነገር ነው። ይህ አረፍተ ነገር ተራ አረፍተ ነገር አይደለም። ጀግንነታችንን ከስንፍናችን አጣምሮ የተሸከመ የማንነታችን መልክ ነው። ራሳችንን ያሞገስንበትና የሰደብንበት የአፋችን ቃል ነው። ለኢትዮጵያውያን (በተለይ ከአክሱም ስልጣኔ ውድቀት በኋላ ለበቀልነው ኢትዮጵያውያን) ፓስፖርትና መታወቂያችን ላይ ከጉርድ ፎቶግራፋችን ይልቅ ይህ አረፍተነገር ቢቀመጥ፣ እኛነታችንን የበለጠ ሊገልፅ ይችላል። ሁሉም መርህ (principle) በስተቀር (exception) አያጣውምና፣ ‘ከአክሱም ውድቀት በኋላ’ ብዬ በአንድ ሀረግ በጠቀለልኩት ሰፊ የዘመን ጥቁር ሰማይ ላይ ሽው እልም ያሉ ተወርዋሪ ኮከቦች መኖራቸው እርግጥ ነው። ይሁን እንጅ ትኩረታችን ከጥቂት ግለሰቦች ግላዊ ጥረትና ስኬት ይልቅ በአጠቃላዩ ማኅበረሰብና ሀገራችን ላይ ስለሆነ መደምደሚያዬን ችኩል ድምዳሜ (hasty generalization) አያደርገውም። መሠረታዊው ጥያቄ፤‘አድዋ እንዴት የኩራትና የቁጭት ምንጭ ሆነ?’ ከፍ ሲል የተጠቀሰው አረፍተ ነገርስ እንዴት የማንነታችን መልክ ሆኖ መጣ? የሚለው ነው።
፩) አድዋ እንደ ኩራት…
የአድዋን ድል ኩራትነት መፃፍ አስቸጋሪ ነገር ነው። እንኳን እኛ የነጭ ዘር ያውቀዋል። አያቶቻችን እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ስልጡን ሰራዊት አፍንጫውን ብለው መመለሳቸው እንደ ፀሐይ፡ እንደ ጨረቃ የዓለምን አንድ ገጽ ይዞ ፍንትው ያለ አጠቃላይ እውነት (geberal truth) ነው። በአንድ ግጥሜ ላይ ያልኩትን ደግሜ ብቻ ርዕሱን እዘለዋለሁ።
አድዋ ማለትኮ…
በእናት ሀገር አንገት - የአጥንት አበባ - የደም ጉንጉን ማጥለቅ፣
መስዋዕት እየሆኑ - የነፃነት ጠበል - ላገር መሬት ማፍለቅ።
አድዋ ማለትኮ…
የተግባር መልስ ነው - ለኡምቤርቶ ንቀት - ላንቶኔሊ ስድብ፣
በሞት መሻገር ነው…
የመቀሌን ምሽግ - ያምባላጌን ጉድብ፤
በባርነት ገደል በግዞት ሸለቆ…
ክቡር ደም ነስንሶ - አጥንት ጎዝጉዞ
ባህርን ሰንጥቆ - ሞቶ ማሻገር ነው - ያገርን እጅ ይዞ።
(ተይው ፖለቲን ዝም ብለሽ
ሳሚኝ - 2014 ዓ.ም)
፪) አድዋ እንደ ቁጭት…
“እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ስልጡን የጣልያን ሰራዊት በኋላቀር መሳሪያ...” የሚለው ወዝ ጠገብ (እና ጆሮ ጠገብ) አረፍተ-ነገር በአንድ በኩል ስልጡን የኢጣልያ ሰራዊት፣ በሌላ በኩል ኋላቀር የኢትዮጵያ ሰራዊት ግንባር ለግንባር የተፋጠጡበት አረፍተ ነገር ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያችን የሦስት ሺህ ዓመት (አምስት ሺህ የሚያደርጉትም አሉ) የመንግሥትነት ታሪክ ያላት፣ ዓለም ከመንቃቱ በፊት በሰማይ በራሪ በምድር ተሽከርካሪ የፈለሰፈች (በራሪ ሰዎችም የነበሯት)፣ ባህር ተሻግራ፣ ዱር መንጥራ በዚህ እስከ ምስርና የመን፣ በዚያ እስከ ማዳጋስካር የገዛች፣ ሱዳንን አስገብራ ወርቅ የምታፍስ (ሰርዶ አልግጥም አለ የፋሲል ፈረሱ፣
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለእሱ፤ የሚለው ሕዝባዊ ግጥም ለዚህ ምስክር ነው)፣ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ደቡባዊ ግማሽ ኢትዮጵያ ውቅያኖስ ተብሎ ለስሟ ክብር የተሰየመላት (ለሙሽርነቷ ስም ሲወጣላት ዳቦ ሳይሆን ውቅያኖስ የተቆረሰላት ሀገር ናት ልንል እንችላለን)፣ ከሮማ ግዛተ-አጼ (Roman empire) ጋር የሚገዳደርና ትከሻ ለትከሻ የሚገፋፋ የአክሱም ስልጣኔ የሚባል ግዙፍ ስልጣኔ የነበራት፣ የመስቀል ጦረኞች (Crusaders) ቄስ ንጉሥ ዮሐንስ (Prester John) የሚባል ንጉሥ መጥቶ ያድነናል የዚያ ንጉሥ ሀገርም ኢትዮጵያ ነች ብለው ተስፋ ያደረጉባት፣ የተስፋቸው ምድር (ከተስፋቸውም ከኢትዮጵያ የተነሳ እንዲል ታላቁ መፅሐፍ) ነበረች። ከአክሱም ውድቀት በኋላ አንዱ በአንዱ ላይ እየተነባበረ እንደ ህልም ሩጫ እያንሸራተተ ሲደፍቃት በኖረው ተከታታይና ተቀጣጣይ ጦርነት ምክንያት ስትወድቅ ስትነሳ ኖረች። የጎንደሩ ማዕከላዊ መንግሥት እየፈዘዘ መምጣቱን ተከትሎም፣ በስሁል ሚካኤል እግር የገባው ዘመነ መሳፍንት ከትልቁ ራስ አሊ እስከ ትንሹ ራስ አሊ ድረስ ለሰባ አመታት ያህል ሀገሪቱን በመሳፍንቱ ኮቴ ስር ሲያስደከድካት ቆዬ። በኋላም የቋራው ካሳ ራዕዩን ስሎ ጦሩን ወልውሎ መጣ። መሳፍንቱ በጦርና በቁማር (Conspiracy) የተካፈሏትን ሀገር፣ ከየእጃቸው ነጥቆ አንድ ላይ ሰበሰባት። ይህ የሆነው እ.ኤ.አ በ1855 (1848 ዓ.ም) ነው።
ኢጣልያ በሌላ አንፃር ከስመ ገናናው የሮማ ግዛተ አጼ (Roman Empire) መፈራረስ በኋላ አንድነት ያልነበራት፣ የናፖሊዮኗ ፈረንሳይ ፍዳዋን የምታበላት በኋላም፣ ኦስትሪያ የተፅዕኖ መዳፏን ትከሻዋ ላይ የጫነችባት፣ ጳጳሳትና ፊውዳል መሳፍንት እንደ ጉሊት ሸቀጥ በመደብ በመደብ ከፍለው የሚሸጧቸው የሚለውጧቸው ግዛቶችና የከተማ መንግስታት መደብር ነበረች። እ.ኤ.አ ከ1830ዎቹ ጀምሮ ያቆጠቆጠውና በዋናነትም በአብዮተኛው ጉሴፔ ጋሪባልዲና በቀይ ለባሽ ጦሩ የተመራው የውህደት እንቅስቃሴ ተጀምሮ በፔድሞንቱ ንጉሥ ዳግማዊ ቪክቶር ኢማኑኤል ንግሥና ተጠናቀቀ። ጣልያኖች Risorgimento (እንደገና መነሳት) ብለው የሚጠሩት የውህደት ንቅናቄ እ.ኤ.አ በ1861 ተጠናቋል የሚሉ ቢኖሩም፣ የጳጳሱ መዲና የነበረችውን ሮምን የመላው ኢጣልያ ዋና ከተማው አድርጎ የተጠናቀቀው ግን እ.ኤ.አ በ1871 ነው። በብዙ ፍላጎቶች መፋተር ወዲያና ወዲህ ተወጥሮ የነበረው የውህደት መንገድ፣ የኢጣልያ ውህደት እ.ኤ.አ በ1871 ተጠናቀቀ።
1861ን እንኳን ብንይዝ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከመሳፍንቱ የፍዳ ዘመን ከተላቀቀችና ካሳም ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ ከነገሠ (እ.ኤ.አ 1855) ከስድስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። የሁለቱንም ሀገራት ውህደት መጠናቀቂያ እንያዝ ካልንም እንጦጦ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1871 ዓ.ም ዋና ከተማ የነበረች በመሆኑ አነሰም በዛም ተቀራራቢ ጊዜ ላይ ውህደት የጨረሱ ሀገራት መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል።
እንግዲህ ጣልያኖች ከእኛ በፊት ወድቀው… ከእኛ በኋላ ተነስተው… እ.ኤ.አ በ1896 (ውህደታቸውን ጨርሰው ሀገር ከሆኑ ከ25 ዓመት በኋላ) ባህር ተሻግሮ ሀገራትን ማብረክረክ የቻለ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ዘመናዊ ሰራዊት እና ክንደ ብርቱ ሀገር ገነቡ። በዚያ ፍጥነት አፍሪካ ተሻግረው እግራቸውን በቀይ ባህር ውሃ ታጠቡ። እኛ ከእነሱ በኋላ ወድቀን… ከእነሱ ቀድመን ተነስተን… እ.ኤ.አ በ1896 (1888 ዓ.ም) (ዘመነ መሳፍንትን ካጠፋን ከ41 ዓመት በኋላ) አድዋ ላይ ምን ይዘን ተሰለፍን? ብለን ስንጠይቅ ጋሻ፣ ጦር፣ በጣም ጥቂት ‘ቁመህ ጠብቀኝ’ ጠበንጃዎች (እነ ወጨፎ) እና በባዶ እጅም ቢሆን የሚተናነቁ ጀግና ተዋጊዎችን። በጀግኖቻችን ሞት አይፈሬነት ምክንያት አሸነፍን። በ41 ዓመቱ ጉዞ ምን ገነባን ስንል ግን መልሱ ነፍስ የሚያሸማቅቅ ሆኖ ብቅ ይላል። እነሱ እንዴት ሰለጠኑ? እንዴት ኋላ ቀረን? ትንሳኤያችን ከትንሳኤያቸው ስድስት ዓመት ቀድሞ እያለ እንዴት ቆመን አሳለፍናቸው? ከእኛ በኋላ ተወልደው ምን ቢንቁን አጥራችንን ነቀነቁ? አያያዛችን እንዴት ሆኖ ቢታያቸው ስንቃችንን ለመቀማት ተራኮቱ? ከአድዋ በኋላም ሳንነቃ ቀረን። የዳግማዊ ምኒልክን ሽፍን ጫማ መልበስ ስናሽሟጥጥ፣ ከውጭ ያስመጣነውን መኪና እንኳ መልመድ አቅቶን የሰይጣን ፈረስ እያልን በየግብር አዳራሹ አፍ ገጥመን ስናንሾካሹክ፣ የድንጋይ ወፎጯችንን መጅ ወርውረን ወደ ዘመን አመጣሹ ወፍጮ ለመራመድ እንደ እግረ-ተከል ህፃን ስንከነበል ጣልያን ግን ከአርባ ዓመት በኋላ አውሮፕላንና መድፍ ሰርታ ድጋሜ መጣችብን። እነሱ ስልጡን እኛ ኋላቀር የሚለውን ሀረግ ክፉኛ ከመላመዳችን የተነሳ ስንናገረውም የምንኮራበት ይመስለኛል።
ዶጋሊ ላይ እነሱ ስልጡን እኛ ኋላ ቀር
አድዋ ላይ እነሱ ስልጡን እኛ ኋላ ቀር
ማይጨው ላይ እነሱ ስልጡን እኛ ኋላ ቀር
ካራማራ ላይ ሶማሌ ስልጡን እኛ ኋላ ቀር
መቼ ይሆን ግልባጩን ታሪክ ሰርተን ‘እኛ ስልጡን እነሱ ኋላቀር’ የሚል ትርክት ገልብጠን የምንፅፈው? መቼ ይሆን ሀገራችን እኩል ለእኩል፣ ስልጣኔ ለስልጣኔ፣ ቴክኖሎጅ ለቴክኖሎጂ የምትገዳደረው? መቼ ይሆን ከጦር ሜዳ መልስም ሀገር እንዳለችን የምንረዳው? መቼ?