በአገራችን አዲስ አበባ የተገነባው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን እና የኮንቬንሽን ማዕከል ከቱሪዝም ገቢ በተጨማሪም፣ የኤግዚቢሽንና የጉባኤ ማዕከል በርካታ ጥቅሞችን ያበረክታል። በዙሪያው የቢዝነስና የስራ ዕድሎችን የሚያስፋፋ፣ የእድገትና የብልጽግና ግንኙነቶችን የሚፈጥር የኢኮኖሚ መነሃሪያ (Hub) በመሆን ያገለግላል። ባሕላዊ፣ ጥበባዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎችን የሚያበራክትም ነው - የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዓይነታቸው ብዙ ናቸው።
የኢንዱስትሪ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምርትና የአገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ፣ የዕውቀት ሽግግርን ያቀላጥፋል። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችን ይከፍታል። የንግድና የገበያ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፣ ውል ለመፈራረም፣ ሽያጭና ግዢ ለመጀመር መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል።
ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ዝግጅቶችን የሚያስተናግድ አገር፣ በዓለማቀፍ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መድረክ ተሰሚነቱ ይጨምራል። የኢኮኖሚ ድርሻው እያደገ ይሄዳል።
አዲስ አበባ የኤግዚቢሽንና የኮንቬንሽን ማዕከል ያስፈልጋታል። ለዚያውም፣ በዓለማቀፍ ደረጃ መወዳደርና ተመራጭነትን ማግኘት የሚችል፣ በላቀ የጥራት ደረጃ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ማዕከል እንደሆነ ከንቲባ አዳነች አበቤ ይናገራሉ።
አዲስ ዓለማ ዓቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል፤ 5ሺ እና 2ሺ ተሳታፊዎችን የሚያስተናግዱ ትልልቅ አዳራሾች ፣ ለኤግዚቢሽኖች እንዲሁም ለጉባኤዎች በስምንት ንዑስ አዳራሽ በርካታ ስብሰባዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ነው። በዓለም የኤግዚቢሽንና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ካርታ ላይ የኢትዮጵያ ስምና ድርሻ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ሰፊ ፕሮጀክት። ከተጓዳኝ ግንባታዎች ጋር 15 ሄክታር ይሸፍናል። በዓለም ደረጃ የመወዳደርና ተመራጭነትን የማግኘት ብቃት እንዲኖረው ታስቦ የተገነባ።
መዲናችን አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችን፣ ጉባኤዎችንና ስብሰባዎችን በአንድ ማዕከል የማስተናገድ አቅም አልነበራትም፤ ይህን የአገራችንን ጉድለት የሚያሟላ ማዕከል ተገንብቶ ለምርቃት የደረሰ ፕሮጀክት፤ ለከተማችንና ለአገራችን ተጨማሪ የስበት ማዕከል ይሆንልናል።
በመሀል ከተማ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ፣ ከአኩሪ ታሪካችን ጋር የተያያ ጥሩ ነገር ፈጥሮልናል።
የትልቅ ታሪክ መዘክር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በግንባታው ጥራትና ውበት፣ በጠቅላላ ይዘቱና በተሟላ አገልግሎቱ ምን ያህል ተመራጭነትን እንዳገኘ በተግባር አይተናል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ስበት ለመሆን ችሏል። አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችና ጉባኤዎች መነሃሪያነቷን የምናረጋግጥበት፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በኩራት የምንመሰክርበት ይሆናል።
አገራችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሥራችም ናት። የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚገኘው በአዲስ አበባ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ የተመድ ተቋማት በአዲስ አበባ ከትመዋል። ይሄ ሌሎች አገራት የማያገኙት ዕድል ነው። የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከላት ተብለው የሚጠቀሱ የዓለማችን አገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ከእነዚህ መካከል አንዷ ናት።
በታሪካዊ ሀብቶችና በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለች ቢሆንም ግን፣ በዓለም ዓቀፍ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ተገቢውን ጥቅምና ድርሻ እያገኘች አይደለችም። በተመድና በአፍሪካ ሕብረት ስር የተካተቱ ብዙ ተቋማት በከተማችን አሉ። ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችንና ጉባኤዎችን ማካሄድ ይፈልጋሉ። እዚሁ አገራችን ውስጥ ቢሆንላቸው ይመርጣሉ - ብዙዎቹ። ነገር ግን፣ ተስማሚ ማዕከላትና አማራጮች ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት ያማትራሉ።
ትልልቅ ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችን በብቃት ለማስተናገድ የምንችልበት፣ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ማዕከል በብቃት ሳናሰናዳ ስለቆየን በየዓመቱ ብዙ ዕድሎችን ያስቀርብናል። የአገራችንን ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ የሚችሉ የሥራና የገበያ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዕድሎች ዓይናችን እያየ ያመልጡን ነበር። አሁን ግን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ተገንብቷል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ እንደሚሉት፣ የግንባታውን ጥራትና ውበት በርካታ ባለ ሙያዎች አይተው መስክረውለታል።
ትልቁ ሁለገብ አዳራሽ - ለስብሰባም ለኤግዚቢሽን ማሰናጃም የሚሆንና 5 ሺ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የሚችል ነው፡፡
ዲዛይኑ የሕንጻውን ንድፍ በግላጭ የሚያሳይ “ስቲል ስትራክቸር” እንደሆነ ጠቅሰው፣ በባለ ሙያዎችም ሆነ በተመልካቾች ዐይን ሲታይ ያምራል ብለዋል። ለእያንዳንዱ የስብሰባ ወይም የኤግዚቢሽን ይዘት በሚስማማ መንገድ አዳራሹን ለማስጌጥ እንዲያመች ታስቦበት የተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
በርካታ ሺ ሰዎችን በአንዴ የሚያስተናግድ ሰፊ አዳራሽ ቢሆንም፣ አየር እንደ ልብ ስለሚያንሸራሽር፣ የጣሪያው ከፍታም 28 ሜትር ስለሆነ የሙቀት መቆጣጠሪያ አያስፈልገውም። በተፈጥሯዊ ብርሃን አዳራሹን የሚያጥለቀልቁ ረዣዥምና ሰፋፊ መስኮቶች አሉት። የፊልም ምስሎችን ለማየት ወይም የኤሌክትሪክ መብራት መጠቀም ካስፈለገም፣ መስኮቶቹን ሙሉ ለሙሉ መጋረድ ይቻላል።
ሁለት የምግብ አቅርቦት ማስተናገጃ ስፍራ፣ እንዲሁም የእረፍት ሰዓት የሻይ የቡና መስተናገጃ ሰፊ ቦታ አለው። ከአዳራሹ ሥር በታችኛው ፎቅ ወደ ተዘጋጁት በርካታ የመጸዳጃ ቤቶች የሚያደርስ መተላለፊያ የሚገኘውም በዚሁ አቅጣጫ ነው። በአዳራሹ ሌላኛው ጎን የክብር እንግዶች መቆያ ቦታና ተጨማሪ የመጸዳጃ አገልግሎት ስፍራዎች ተሰርተውለታል።
የኤግዚቢሽን አዳራሽ - በ5 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት የተገነባ፣ ከሁለገብ አዳራሽ ቀጥሎ ከላይ የምናገኘው ትልቅ አዳራሽ ዋና አገልግሎቱ ለኤግዚቢሽን ነው።
መካከለኛ አዳራሽ - አንድ ሺ ሰዎችን ያስተናግዳል። ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖረው፣ አየር በደንብ እንዲንሸራሸር፣ የተፈጥሮ ብርሃን በሰፊው እንዲያስገባ ታስቦበት የተሰራው አዳራሽ፣ ጣሪያው 28 ሜትር ቁመት አለው።
ከመደበኛ የኤሌክትሪክ መስመሮች በተጨማሪ ወለል ሥር የተቀበሩ መስመሮችም ተዘርግተውለታል። ኤግዚቢሽን የሚያቀርቡ ተሳታፊዎች፣ ከአዳራሹ ወለል ላይ ከዳር እስከ ዳር የኤሌክትሪክ ሶኬቶችን በአጠገባቸው ስለሚያገኙ፣ ግራ ቀኝ የሚዝረከረኩ ገመዶች አይኖሩም።
ከአንድ አቅጣጫ በኩል፣ ከአዳራሹ አጠገብ የመጋዘን ክፍሎች አሉት። በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ቢሮዎችን ይዟል። በአጠቃላይ ከኤግዚቢሽን ዝግጅት ጋር የተዛመዱ አገልግሎቶችን ሁሉ እንዲያሟላ ተድርጎ ነው የተሠራው።
ሰፊ የትዕይንት አዳራሽ - በተገጣጣሚ ግድግዳም ሲከፋፍሉት ደግሞ ሰባት ንዑስ አዳራሾች ያሉት ሲሆን አራተኛ ፎቅ ላይ የምናገኘው ሰፊ አዳራሽ፣ 2 ሺ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል። ለትልቅ ጉባኤ ሊያገለግል ይችላል።
ስዕሎችን ለማሳየት ወይም ሌላ ለእይታ የሚቀርቡ ድግሶችን ለማዘጋጀትም የአዳራሹ ቅርጽ ይመቻል። ተመልካቾች በአንዱ ጫፍ ገብተው፣ በእይታ ድግሶች ተስተናግደው ዓይናቸውን ረክቶ በሌላኛው ጥግ ይወጣሉ። ካስፈለገ ደግሞ ረዥሙ አዳራሽ ውስጥ ተገጣጣሚ ግድግዳዎች ተዘርግተው፣ ለንዑስ ስብሰባዎች የሚያገለግሉ 7 መካከለኛና አነስተኛ አዳራሾች ይወጣዋል።
ግድግዳዎቹ ተጣጣፊ ተገጣጣሚ ቢሆኑም፣ ከመደበኛ ግድግዳ አይተናነሱም። ድምጽ አያሳልፉም፤ ሲታዩም ያምራሉ ብለዋል - የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ።
አዳራሹ አራተኛ ፎቅ ላይ ቢሆንም፣ ከበቂ በላይ መተላለፊያዎች አሉት። በየአቅጣጫው በተሠሩ በርካታ ሰፋፊ ደረጃዎች አማካኝነት መግባትና መውጣት ይቻላል። ከደረጃዎች ጎን “ስካሌተሮች” አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪም አሳንሰሮች (ሊፍቶችን) መጠቀም ይቻላል። መጨናነቅም ሆነ መጣበብ አይኖርም።
የአዳራሾቹን አገልግሎት በትክክል ለማከናወንና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ክፍሎችን ጨምሮ፣ የጥበቃና የክትትል ስራውም በሚገባ እንደታሰበበት ስራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ። ለዚህም የጥበቃ ካሜራዎችና መከታተያ ቴክኖሎጂዎችን አሟልተናል ይላሉ - አቶ ሲሳይ። የጥበቃ ባለሙያዎች የተሰብሳቢዎችን ትኩረት በማይረብሽ ሁኔታ ስራቸውን ያከናውናሉ።
የኤግዚቢሽንና የጉባኤ አዳራሾች በተጨማሪ፣ ማዕከሉ ሌሎች በርካታ ግንባታዎችንንና አገልግሎቶችን ያካትታል።
ባለ 5 ኮከብ ሆቴል - 980 የእንግዶች ማረፊያ ያለው።
በሆቴል አገልግሎት በከተማችን በትልቅነቱ ቀዳሚነትን የያዘ ሆቴል እንደሚሆን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ 980 የእንግዳ ማረፊያዎችን መያዝ ይችላል ብለዋል።
እዚህ አካባቢ ምንም ሆቴል አልነበረም ይላሉ - ከንቲባ አዳነች። አሁን ሦስት ሆቴሎች ተሰርተዋል። አራተኛው ከማዶ በኩል አለ። ተደማምረው 1400 የእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት የማቅረብ ዓቅም አላቸው።
ምርጥ ምርጥ አፓርትመንቶች በአካባቢው ተሰርተዋል። ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት የሚሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎችና ተቋማትም ተዘጋጅተዋል።
ፊት ለፊት ለሚ ፓርክ አለ። ሰፊ ነው። ከመስቀል አደባባይ በመቀጠል የሚጠቀስ የከተማችን ትልቅ አደባባይ ነው። ከኤግዚቢሽንና ከጉባኤ ማዕከሉ ጋር ተያይዞ ነው ስራው የሚከናወነው።
ይህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ግዙፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ “አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል” ትላልቅ አህጉር አቀፍ እና ዓለምአቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ ለምረቃ መብቃቱ ለከተማዋ ተጨማሪ ግርማ ሞገስን ያጎናፀፈ ነው፡፡