Wednesday, 05 March 2025 00:00

ምዕራፍ 7

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እስካርሌት በሁለት ሳምንቶች ውስጥ ሚስት ሆነች፡፡ ከዚያ በቀጠሉት ሁለት ወራት ውስጥ ደግሞ የሙት ሚስት ሆነች፡፡ በእርግጥ ምንም ሳታስብበትና በጥድፊያ ባለትዳር ብትሆንም ወዲያው ከዚህ ከትዳር ሰንሰለት እፎይ ብላ ለመገላል ችላለች፡፡ ዳሩ ግን እነዚያን ከትዳር በፊት የነበሩ የመዝናናትና እንደልብ የመጨፈር የምንግዴ ሕይወት መብትና ነፃነቷን፤ መልሳ ለማግኘት አልቻለችም፡፡ ከሰርጓ ማግስት ቀጥሎ በነበሩት ወራት የባሏ መሞት ሐዘን ተከተለባት፡፡ በልቧ እፎይ አለች እንጂ በሌላ ወገን የከፋት ነገር ተፈጥሯል- የልጅ እናት መሆን ተክሎባታል፡፡ ባንድ ጀምበር ሚስት፣ በሌላ ጀምበር የሙት ሚስት፣ ደሞ በሌላ ጀምበር እናት፡፡


ዓመታት ካለፉ በኋላ እስካርሌት የእነዚያን 1861 የሚያዚያ ቀናት ከነዝርዝር ውሎ- አመሻሻቸው ለማስታወስ በጭራሽ አትችልም፡፡ ጊዜና ክንውኖቹ ሁሉ እንደህልም፣ እንደቅዠት እየተደራረቡ ያላንዳች እውንነት ወይም ተጨባጭ ምክንያት ብዥ እንዳለ ፊልም አልፈዋል፡፡ መቼም እስክትሞት ድረስ እነዚያ ቀናት በትዝታዋ መዝገብ ውስጥ ባዶ ገጽ ሆነው ይቀራሉ፡፡ በተለይ ቻርለስ ለጋብቻ ሲጠይቃት እሺ ባለችበት ቀንና በሠርጋቸው ቀን ማህል ያለው ትውስታ ጭራሽ ጭልምልም ያለ ነው፡፡ ሁለት ሳምንት፣ መቼም በሰላሙ ጊዜ እንኳን ጋብቻ ፍጥምጥም የማይደረግበት ጊዜ ነው፡፡ ከፍጥምጥም ወዲያ ደግሞ የአንድ ዓመት ወይም ቢያንስ ቢያንስ የስድስት ወር ሞቅ ያሉ ቀናት ተጠብቆ ነበር ጋብቻ የሚፈጸም፡፡ ዳሩ ግን ደቡብ በእሳት በተያያዘበት ጊዜ በመሆኑ ድርጊቶቹ ሁሉ ንፋስ ተሸክሟቸው እንደሚነጉድ ሁሉ በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚበሩ የጥንቶቹ ቀናት የእርጋታ ጉዞ ውበት፤ ለዛው ሙጥጥ ብሎ ጠፍቷል፡፡ ያኔ፣ ኤለን እጆቿን አጣጥፋ የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል እያለች እስካርሌትን በመምከር፣ ደግማ ደጋግማ ነገሯን ሁሉ እንድታስብበት ሞክራ ነበር፡፡ ሆኖም እስካርሌት የእናቷን ልመና ሁሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ ሜዳ አፈሰሰችው፡፡ ማግባቱን አገባች፡፡ ያውም ባንዳፍታ- በሁለት ሳምንት ውስጥ፡፡


አሽሌይ ከሰራዊቱ ጋር በተጠራ ጊዜ ለመሄድ እንዲያመቸው የሠርጉን ቀን ከበጋው መጀመሪያ ወደ ግንቦት መግቢያ ሲያዟዙረው እስካርሌት የሠርጓን ቀን ከሱ ሰርግ በፊት አደረገችወ፡፡ ኤለን እምቢ ብላ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዋድ ሐምፕተን ሻለቃ ጦር ጋር ወደ ደቡብ ካሮላይና ለመሄድ ቻርለስ በጣም በመጣደፉ፣ በአዲስ ፍቅሩም ግፊት በመወትወቱ፣ ጄራልድም ሁለቱን ወጣቶች በመደገፉ፣ የተባለው ሠርግ እሷ በፈለገችው ቀን ለመሠረግ በቃ፡፡ ጄራልድ፣ አንድም በጦርነቱ ትኩሳት ምክንያት፤ አንድም እስካርሌት ጥሩ አቻ፣ አልፋም እኩያ ለመምረጥ በመቻሏ ተደስቶ የሠርጉን መፋጠን ይሁን አለ፡፡ ለዛውስ ጦርነቱ መጣሁ መጣሁ እያለ በሚፎክርበት ሰዓት በሁለት ፍቅረኛሞች ማህል ጣልቃ ገብቶ-አርጉ አታርጉ የሚለው፤ እሱ ማን ነውና ነው? ኤለን ሌሎች የደቡብ ሴቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ ተሟግታ ተሟግታ በመጨረሻው እጇን ሰጠች፡፡ በእርጋታና በትርፍ ጊዜ የመዝናናት ወግ የተሞላው ዓላማቸው፤ ግርግር በበዛበት ዝባዝንኬ ሕይወት በመተካቱ፤ ልመናቸው፣ ፀሎታቸውና ምክራቸው ሁሉ ከንቱ ቀርቶ፤ እንደ ጎርፍ እየጠራረገ ከሚወስዳቸው ጠንካራ ንፋስ ጋር አብረው እንዲነፍሱ ተገደዱ፡፡
ደቡብ በጉጉትና በጦርነት ስሜት ተሳክሯል፡፡ መቼም ጦርነቱን በአንድ ውጊያ ከፍፃሜ እንደሚያደርሱት ማንም ያውቃል፡፡ በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ ወጣት በጥድፊያ ለጦርነቱ ይመዘገባል፡፡ ስለዚህ ለፍቅረኛው በጥድፊያ ቀለበት ያስራል፡፡ ቀለበት ያሰረው ደግሞ በአጭር ጊዜ ሠርጉን ይደግሳል፡፡ እንዲህ በቶሎ አቀለጣጥፎ ጋብቻውን ውል እያስያዘ ወደ ቨርጂኒያ ሄዶ ያንኪዎችን ድባቅ ለመምታት ልቡ ተነሳስቷል፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ከጦርነቱ በፊት የሚፈጸሙ የጋብቻ ሥነ-ስርዓቶች ስላሉ፣ ሰው ሁሉ ለመለያያ ለቅሶና ለሀዘን ምንም ጊዜ የለውም፡፡ ሴት ሴቶቹ ዩኒፎርም ይሰፋሉ፣ ካልሲዎች ይጠልፋሉ፣ የሚጠቀለሉ ፋሻዎችን ያዘጋጃሉ፡፡ ወንድ ወንዱ የሰልፍ ልምምዱንና ተኩሱን ተያይዞታል፡፡ ከአትላንታ በስተሰሜን ወደምትገኘው ወደ ቨርጂኒያ የሚሄዱ በሠራዊት የተሞሉ ባቡሮች በጆንስቦሮ እያቋረጡ እንደጉድ ይግተለተላሉ፡፡ ለሚሊሺያው ዩኒፎርም ለማዘጋጀት በተመረጡ ሕዝባዊ ኩባንያዎች የተሰፉትን፤ ደማቅ ቀይ፣ ውሃ ሰማያዊና አረንጓዴ ዩኒፎርሞች የለበሱ የተለያዩ ክፍሎች በደስታ ይተምማሉ፡፡ አንዳንድ ትናንሽ ቡድኖች ደግሞ እቤት የተሰፉ ባርኔጣዎችን አድርገዋል፡፡ ሌሎች ከናካቴው ዩኒፎርም ያልለበሱም አሉባቸው፡፡ ሁሉም ቢሆኑ በግማሽ ሥልጠናና በግማሽ ትጥቅ የሚጓዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በስሜት ተሞልተው ሊፈነዱ ከመድረሳቸው የተነሳ እየጮኹ ወደ ሽርሽር የሚሄዱ ይመስላሉ፡፡ እነዚህን ዘማቾች የሚመለከቱት ገና በዝግጅት ላይ ያሉት ወጣቶች ልምምዱን አገባደው ቨርጂኒያ ከመድረሳቸው በፊት ጦርነቱ አልቆ ጉድ እንዳይሆኑ ሰግተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሠራዊቱን ቶሎ የማዝመት ተግባር በጣም በጥድፊያ እየተሠራ ነው፡፡


በዚህ የጦርነት ጥድፊያ ማህል የእስካርሌት ሠርግ ድግስ ደግሞ እየተጧጧፈ ነው፡፡ በዚህ ተብሎ በዚያ እሷ ራሷ እንኳ መቼ ተገባደደ ብላ ባላሰበችበት ሰዓት የኤለንን የሙሽራ ልብስ ከነቩዋሉ ለብሳ፣ የአባቷን ክንድ ይዛ፣ የታራን ደረጃ በከፍተኛ አጀብ ወርዳ በእንግዶች ጢም ብሎ ወደተሞላው አዳራሽ ገባች፡፡ ሁሉ ነገር ካለፈ በኋላ እንደህልም ውል ውል የሚላት- ግድግዳው ላይ የተሰቀሉት በመቶ የሚቆጠሩ የሚንቦገቦጉ ሻማዎች፣ የእናቷ በፍቅር የተሞላ ፊትና በመጠኑ ደንገጥ ያለ አኳኋን፣ እንዲሁም ጋብቻዋ የአብርሃም የሣራ እንዲሆን ስትጸልይላት በዝግታ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከንፈሮቿ፣ ጄራልድ በብራንዲና በኩራት ፊቱ በላብ ቸፍ ብሎ፣ ሴት ልጁ ገንዘብም፣ መልካም ስምም፣ ደህና ዘርም ያገባች መሆኗ ሲያስፈነድቀው፣ አሽሌይ ደግሞ ከደረጃዎቹ ግርጌ ክንዱን ከሜላኒ ክንድ ጋር እንዳቆላለፈ ቆሞ፣ የሚታየው ትርዒት ነው፡፡ በአሸሌይ ፊት ላይ የሚነበበውን ሁኔታ ስታይ የሚከተለው ሀሳብ መጣባት- “ይሄ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ሊሆን አይችልም፡፡ ቅዠት ነው፡፡ ሕልም ነው፡፡ አሁን ባላስበው ይሻላል እንጂ በዚህ ሁሉ ሰው ፊት ጩኸቴን እለቀዋለሁ፡፡ አሁን በጭራሽ ለማሰብ አልችልም፡፡ ሌላ ጊዜ፣ ዓይኖቹን ለማየት በማልችልበት ጊዜ አስብበታለሁ፡፡”
ፈገግ ባሉትና በተሰበሰቡት እንግዶች ማህል ማለፉም ቢሆን ህልም የመሰለ ነገር ነው፡፡ የቻርለስ ሳምባ የመሰለ ፊትና የሚንቀጠቀጥ ድምጽ፣ የሷም ቀዝቃዛና ግራ የተጋባ መልክ ይታያል፡፡ በመጨረሻ እንኳን ደስ ያለሽ የመባሏ፣ የመሳሟ፣ የጥብስ ግብዣው፤ ዳንሱ ሁሉ እንደህልም ያለፈ ነገር ነበር፡፡ አሽሌይ ጉንጯን ሲስማት የተሰማት ስሜት፣ የሜላኒ “አሁን በእርግጥ እውነተኛ እህትማማቾች ሆንን” የሚል ለስላሳ ድምፅ-ይሄ ሁሉ እውን ያልሆነ ቅዠት ነበር፡፡ የቻርለስን አክስት ወይዘሮ ፒቲፓት ሐሚልተንን ከመቀመጫቸው ያስነሳቸው የስሜት ግንፋሎት እንኳን ሳይቀር፤ የሰመመን መንፈስ እንደዋጠው ባለ ሕልም ነው የሚታያት፡፡
ሊነጋጋ ሲል ዳንሱም ግብዣውም ሲገባደድ፤ ታራንና የምስለኔውን ቤት አጨናንቀውት የነበሩት ከአትላንታ የመጡት እንግዶች፤ በየአልጋው፣ በየሶፋውና በየምንጣፉ ላይ ሲተኙ፤የጎረቤቶችም ሰዎች ሁሉ በሚቀጥለው ቀን በ”አሥራ ሁለቱ ዋርካዎች” መናፈሻ ቦታ ለሚደረገው ሰርግ ለመዘጋጀት ወደየቤታቸው ሲሄዱና አካባቢው ሁሉ እርጭ ሲል፤ ያ ሁሉ እንደህልም እንደ ቅዠት የታየ ነገር ከገሃዱ ዓለም ጋር ተጋጨና እንደ መኪና መስታወት እንክትክቱ ወጥቶ ዱቄት ሆነ፡፡ ገሃዱ ዓለም፤ አንገቷ ድረስ አንሶላውን ስባ የማይጥም መልኳን ስታሳየው እንኳ ከምንም ሳይቆጥራት በደስታ የሚፈነድቀውን ቻርለስን አሳያት፡፡
እስካርሌት ባልና ሚስት በአንድ አልጋ ውስጥ እንደሚያድሩ በደንብ ታውቃለች፡፡ ነገር ግን እስከዚህም ከጉዳይ ጽፋ አስባበት አታውቅም፡፡ ከእናቷና ከአባቷ አንፃር ስታየው ነገሩ ትክክል ነው፡፡ በራሷ ላይ ደርሶ ስታየው ግን በጭራሽ አልዋጥ አላት፡፡ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ከዛ ከ”አሥራ ሁለቱ ዋርካዎች” ግብዣ በኋላ በራሷ ላይ ምን ዓይነት መዘዝ እንዳመጣች ተገነዘበች፡፡ ለራሷ በችኮላ የማይሆን ውሳኔ በመወሰኗ የፀፀት ምጥ በሚያሰቃያትና አሽሌይን ለዘለዓለም የማጣቷ ነገር እንደ እግር እሳት በሚለበልባት ሰዓት፤ የዚህ ልታገባው ፈጽሞ እቅድ ያልነበራት ልጅ አብሯት አንድ አልጋ ውስጥ ማደር፤ በጭራሽ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ሆኖባታል፡፡ እሱ እያመነታ ወደ አልጋው ሲጠጋ በጎረነነ ድምጿ አንሾካሾከችለት፡፡
“እንዲች ብለህ ብትጠጋኝ እሪ ብዬ ነው የምጮኸው! ላንቃዬ እስከሚሰነጠቅ አገሩን አደባልቀዋለሁ! በል ካጠገቤ ጥፋ! ጫፌን ንካኝና ወዮልህ!”
ቻርለስ ሐሚልተን በዚህ ዓይነት የሠርጉ ዕለት ማታ በመኝታ ቤቱ ጥግ ባለ፣ ባለመደገፊያ ወንበር ላይ ጉልበቱን ታቅፎ አደረ፡፡ ይህን ያህልም አልከፋውም፡፡ ምክንያቱም የሙሽራይቱን ትህትናና ልስላሴ ስለተረዳው ወይም የተረዳው ስለመሰለው ነው፡፡ ፍራቻዋ ሁሉ ሟሙቶ እስኪጠፋና እሱን ለመቀበል ዝግጁ እስክትሆን ድረስ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ብቻ…ብቻ እየተገላበጠ፣ ለመመቻቸት እየሞከረ በጣም በቅርቡ ወደ ጦርነት እንደሚሄድ አሰበና አንዴ በኃይል ተነፈሰ፡፡


የእስካርሌት ሠርግ እንደሕልም እንደቅዠት እንዳለፈ ሁሉ የአሽሌይ ደግሞ ከሷ በባሰ የሕልም ጭጋግ ውስጥ እንደተሸፈነ አለፈ፡፡ እስካርሌት በ”አሥራ ሁለቱ ዋርካዎች” መናፈሻ እልፍኝ፣ ውሃ አረንጓዴውን “የሠርግ ማግስት ቀሚሷን” እንደለበሰች ከትላንት ማታ ጀምሮ እየበሩ ባሉት በመቶ በሚቆጠሩ ሻማዎች ማህል ቆማ፤ የሜላኒ ሐሚልተን ትንሿ ፊት የውበት ፀዳል ስትጎናፀፍ ተመለከተች፡፡ ወ/ት ሜላኒ ሐሚልተን ወ/ሮ ሜላኒ ዊክስ በምትሆንባት በዚህች ቅፅበት ፊቷ ላይ የሚበራው ቁንጅና እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ እንግዲህ አሽሌይ ለአንዴም ለሁሌም መሄዱ ነው፡፡ ከጭብጧ ተፈልቅቆ ወጥቶ ማምለጡ ነው፡፡ የሷው አሽሌይ፡፡ አዬ! ምኑን የሷው ሆነው፣ አሁንማ የሰው አሽሌይ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ የሷ ሆኖስ ያውቃል እንዴ? እስካርሌት በጭንቅላቷ ውስጥ መዓት ነገሮች እየተርመሰመሱ የምታስብ የምታልመውን ሁሉ አሳጧት፡፡ ጭንቅላቷም ለማሰብ ከሚችለው በላይ ስለበዛበት ደከመው፡፡ ተረባበሸ፡፡ አሽሌይ አፈቅርሻለሁ ሲላት አልነበረም እንዴ? ታዲያ ምን ለያያቸው? ይሄን ለማስታወስ ብትችል በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ቻርለስን በማግባቷ የመንደሩን ሰዎች ሐሜተኛ ምላስ እንዲታጠፍ አድርጋ፣ አፋቸውን አስዘግታ ነበር፡፡ ዳሩ ያ አሁን ለሷ ምን ረባት? በዚያን ጊዜ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን ግን ከቁጥር የሚጣፍ ነገር አይደለም፡፡ ያም ቢሆን ለሷ ትልቁና አስፈላጊው ጉዳይዋ አሽሌይ ብቻ ነበር፡፡ አሁን እሱም አመለጣት፡፡ እሷም ብትሆን፤ አለማፍቀር ብቻ ሳይሆን በጣም ከምትጠላው ሰው ጋር ተጋብታ አርፋለች፡፡
(ከነቢይ መኮንን “ነገም ሌላ ቀን ነው” መጽሐፍ የተቀነጨበ)

 

Read 378 times