መንገድ ዓይንህ አፈር አይባልም ደርሶ፣
የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ፡፡
ይወስዳል መንገድ፣
ያመጣል መንገድ
አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ….
ስለ መንገድ የተቋጠሩ ስንኞች፣ የተነገሩ ምሣሌያዊ አነጋገሮች፣ የተንቆረቆሩ ዘፈኖች በርከት ያሉ ናቸው፡፡ መንገድ ከአገር ልጅ…ም ይባላል፡፡ ስለ መንገድ የተነገረው፣ የተቀነቀነውና የተዘፈነውን ለመስኩ ባለሙያዎች ትተን ወደ ዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን እናምራ፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን ግየታ ወረዳ ተጉዘን ነበር፡፡ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም.፡፡ ቶቶት የወጣቶች ማኅበር÷ በዘቢደር ቴሌግራም ገጽ ላይ ለ6ኛ ጊዜ ወደ ጉራጌ ዞን ግየታ ወረዳ ዛራ ባህላዊና ታሪካዊ ቦታ “ጉዞ ፊታውራሪ ሳፎ” በሚል ጉዞ እንደሚያደርግ ማስታወቂያ ለጥፎ አይቼ ለመጓዝ ወሰንኩ፡፡ ለጉዞ የሚጠየቁትን መስፈርቶች አሟልቼ ከማኅበሩ አባላት ጋር ሰባተኛ ላይ ከጧቱ አንድ ሰዓት ግድም ተቀላቀልኩ፡፡ ሰባተኛ ላይ ያገኘኋቸው የማኅበሩ አባላት፣ ለእኔ ሁሉም አዳዲስ ፊቶች ነበሩ፡፡ በኋላ መንገድ ላይ የተቀላቀሉን ግን የማውቃቸውና የሚያውቁኝ አልጠፉም፡፡ ከአዲስ አበባ (ሰባተኛ) አውቶቡሳችን ጓዛችንን ሸክፎ ለጉዞ ዝግጁ ሆነ፡፡ “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ ጉዞው አዝናኝ እንደሚሆን ከወዲሁ ምልክቶች ይታዩ ጀመር፡፡ የተመረጡ የጉራግኛ ዘፈኖች ተንቆረቆሩ፡፡ ጭፈራውና እልልታው… ከጣራ በላይ ሆነ፡፡ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ስለሆኑ ለጉዟችን ውበትና ጣዕም ሰጡት፡፡ ወጣት የነብር ጣት እንዲሉ፡፡
“ዛራ”፣ የተፈጥሮ ዛፎች ስብስብ ብቻ አይደለም፡፡ ዛራ ውበት ነው፡፡ ዛራ ታሪክ ነው፤ ዛራ የተፈጥሮ ሚዛን አስጠባቂ ደን ነው፡፡ ዛራ ቅርስ ነው፡፡ ዛራ ባህል ነው…፡፡ በዛራ ደን ውስጥ ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ተገጥግጠዋል፡፡ 30.69 ሔክታር ያህል እንደሚሸፍን ከግየታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከ300 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረ በውስጡ የጥድ፣ ዝግባ፣ ሾላ፣ ወይራ፣ ግራር፣ ኮሶና ሌሎች አገር በቀል ዛፎች እንደሚገኙበት ከተደረገልን ገለዳ ለመረዳት ችለናል፡፡ የደኑ መፈጠር ምክንያቱ የግየታ ዋቅ “ማንድወ” እንደሆነ የዕድሜ አንጋፎች ይናገራሉ፡፡ የማንድወ ዓመታዊ በዓል “ጭሽት”፣ በየዓመቱ በታኅሣሥ ወር አጋማሽ በዕለተ ሐሙስ ዛራ ውስጥ በሚገኘው የዋቅ ዘገር ይከበራል፡፡
የዋቅ መልዓክ በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ (በጉራጌ ምድር) የጦርነት ዳመና ሲያንዣብብ፣ የዝናብ እጥረት ሊከሰት ሲሆን ማኅበረሰቡ ወደ ዋቅ መቀመጫ ይጓዛል፡፡ ፈጣሪ ምህረቱንና ይቅርታውን እንዲሰጥ ዋቅ ተልዕኮውን ይወስዳል፡፡ ፈጣሪም ሳይዘገይ ምላሹን ይሰጣል፡፡ ዝናቡም ይዘንባል፤ ጦርነት ቀርቶ ሰላምም ይሆናል፡፡
ለማንድው ክብር በየዓመቱ የጭሽት በዓል ይከበርለታል፡፡ በበዓሉ ላይ ምዕመናን የተመኙት ከተሳካ እንደ አቅማቸው ግምጃ፣ ማር፣ የወርቅ ጃንጥላ፣ ብር …ይሰጣሉ፡፡
የግየታ ዋቅ - ማንድወ መቀመጫና የበዓሉ ማክበሪያ የሆነው ዛራ ኅልውናውን ለማጥፋት የሚፈታተኑት ወገኖች አልጠፉም፡፡ ደንብና ሥርአትን፣ ባህልና ሥነምግባርን ጥሰው ዛራን የሚደፍሩ እንዳሉ ሁሉ እምነትን (ኃይማኖትን) ተገን አድርገው ባህላዊውን ሥርአት በነበር ለማስቀረት ቀንና ሌሊት የሚባዝኑ፣ የሚያሴሩና የሚያበላሹ እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ለባህሉ በተከለለ ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ካላቋቋሙ እንቅልፍ የማይወስዳቸው የባህል ጸሮች እዚህም ሌላም ቦታ አጋጥመዋል፡፡ ባልጠፋ ቦታ ባህላዊ ተቋሞች ያሉበትን ቦታ እየመረጡ ለምን ሁከት እንደሚፈጥሩ ግልጽ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው የያዘውን እምነት የማራመድ መብቱ የተጠበቀና የተከበረ ቢሆንም፤ ይህንን ሃቅ መቀበል አይፈልጉም፡፡ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ” የሚል አቋም ስለሚያራምዱ የሌሎችን መብትና ነፃነት ይጋፋሉ፡፡ ለዘመናት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ባህላዊ ሥርአት እከተላለሁ ለሚለው ወገን ዕድል ለመስጠት ፍቃደኞች አይደሉም፡፡ እነርሱ እከተለዋለሁ የሚሉትን እምነት እንኳ በወጉ ሳያውቁ የሌላውን የሚያውቁ የሚመስላቸው ነገር ግን የማያውቁ ሞልተዋል፡፡
በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ የክርስትናም ሆነ የእስልምና ኃይማኖቶች ሳይስፋፉ ወይም ከነአካቴው ሳይኖሩ ነው ባህላዊ እምነቶች የነበሩት፡፡ አንዳንድ ወገኖች መረጃና ማስረጃ ሳይዙ እንደሚያወሩት አይደለም፡፡ ከእነዚህ ባህላዊ እምነቶች ቦዠ፣ ደሟሚትና ዋቅ በፊት በጉራጌ ምድር ኃይማኖት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ “የዋቅ አምልኮ በሚካሄድበት ቦታ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነበር” ብለው የበሬ ወለደ ትርክታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ፍጹም ውሸት ነው፡፡ በሰነድ ወይም በማስረጃ የተደገፈ መረጃ ማቅረብም አይቻልም፡፡ እንዲሁ ስሜታዊ ተኩኖ የሚነገር ተራ ኩሸት ነው፡፡
የጉራጌ ሕዝብ ለፍትህ፣ ርትዕና ንብረት ጥበቃ ጉዳይ ”ቦዠ”ን፣ ለድርቅና ለጦርነት መፍትሔ (ጦርነትን ድል ለማድረግና ዝናብ ለማግኘት) ዋቅን፣ ከልምላሜና ከዘር ማስቀጠል (ከማሕጸን ልምላሜ) ጋር በተያያዘ ደሟሚትን፣ ወደ እግዚያብሔር (እግዘር) ዘንድ መልዕክት የሚያደርሱ ወይም ማኅበረሰቡ መልዕክት ያደርሱልኛል ብሎ እምነት የሚጥልባቸው ናቸው፡፡
አንዳንድ ዳተኞች እንደሚሉት፤ ባህላዊ አምልኮዎቹ ባዕድ አምልኮ አይደሉም፡፡ ባዕድ አምልኮ ማለት ከእግዚአብሔር መስመር የወጣና ከጊዜ በኋላ ከባዕድ አገር የመጣ ማለት ነው፡፡ ባህሎቹ ከፈጣሪ እግዚያብሔር ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከሚከተለው የዋቅ በድራና የደሟሚት ዋይወቶ መመልከት ይቻላል፡፡
ከዋቅ በድራ
… አጎ ተሰቀረም - ይውሪ ባነ በሽንጥር፣
ጨኹወ ገፓም ቾናም ይውሪ ባነ በሽምበረር
ማጉራ በቅየረቅየር ሸተረም
ጉ ባሁም የጎረ
አባኸ እግዘረ
በድራኸ ይብረ …
ከደሟሚት ዋይወቶ
ብሻና ደምወቶ፣
የአብ እግዘር ገረዶ
ተሰሜ ትትወርዶ
ምር አውያም ወረቶ? …
አቶ ገብረየሱስ ኃይለማርያም፣ “The Gurague and Their Culture” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ገጽ 140፣ “Many Gurague believed Demamwit to be one of the three children of God the Father.”
ከላይ በጉራግኛ የተቀመጡት ስንኞች፣ ዋቅም ሆነ ደሟሚት ተልዕኳቸውም ሆነ አመጣጣቸው ፈጣሪን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ የባህሉ አጋፋሪዎች ተብለው የተሾሙት የሚያጠፉትና ባህሉ በራሱ የሚያዝዘውን በውል ለይተው ሳይረዱ እንዲሁ በጥላቻ በባህልና እሴቶች ላይ የዘመቱት አላዋቂዎች ወይም ለጉዳዩ ማይም የሆኑት ብቻ አይደሉም፡፡ ተማርን፣ ሰለጠንን ወይም ውጭ አገር ሄደን ተማርን የሚሉ አንዳንድ ወገኖችንም ያካትታል፡፡ የተጻፈውን ሳያነቡ፣ ሳይጠይቁና የተጠናውን ሳያጠናቅሩ ለዘመናት የኖረን ባህልና እሴት ለማውደም ይጣደፋሉ፡፡ ሳይመረምሩ በስሜት በመነዳት ይበይናሉ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ስለ መብት መከበር፣ ስለ ኃይማኖት (የእምነት) ነጻነት መታጣት ሌሎችን ሲከስሱ ዳር ድንበር የላቸውም፡፡ እነርሱ ራሳቸው ግን የሰውን የእምነት ነጻነት አያከብሩም፡፡
እኔ ወድጄና ፈቅጄ የተቀበልኩትን እምነቴን - ባህሌን ማነው የሚነጥቀኝ? ማንኛውም ወገን እምነቱንና ኃይማኖቱን እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እርሱ እንዲነካበት እንደማይፈልገው ሁሉ የሌላውንም መንካት የለበትም፡፡ ለመንካት ወይም ለማጥፋት መብትም ሆነ ነጻነት የለውም፡፡ በስሜትና በስማ በለው ባህልን መጻረር፣ አልፎ ተርፎ ባህላዊ ቦታዎች ላይ እሳት መለኮስ ድንቁርና ነው፡፡ ጀብደኝነትና አምባገነንነት ነው፡፡ ያለማወቅ አዙሪት ነው፡፡
በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ የሚገኙ የቦዠ፣ የደሟሚትና የዋቅ ባህላዊ ሥፍራዎች በአገር በቀል ዛፎች የተሸፈኑና የተከለሉ ናቸው፡፡ አባቶችም ሆን ብለው ቦታውን ጠብቀው ነው ያስተላለፉት፡፡ ዛፎቹ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ፣ ዝናብ በወቅቱ እንዲመጣ እንዲሁም የአካባቢው የአየር ሁኔታ ለሰው ልጅ ምቹ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ የተፈጥሮን ሚዛን ከመጠበቁ ጎን ለጎን ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዛፎችና ዕጽዋት እንዲበቅሉ፣ ምንጭ እንዲፈልቅ ያመቻቻሉ፡፡ ዕፅዋት፣ የዱር እንስሳት እንዳይጠፉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ የቦዠ - ጉዌታኩየ መቀመጫ ይናንጋራ፣ የደሟሚት - የዌደማም መቀመጫ ሞክየረርና የቢጣራ፣ የቸሃ ዋቅ - ደማም መቀመጫ ወገፐቻ፣ የግየታ ዋቅ - ደማም መቀመጫ ዛራ ባህላዊ ቦታዎች … ለዚህ አባባሌ ምስክሮቼ ናቸው፡፡
በዛራ ደን÷ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ጥንቸል፣ ጅብ፣ ቀበሮ፣ ጃርትና የተለያዩ የአዕዋፋት ዝርያዎች በብዛት እንደሚገኙ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ካሰራጨው መረጃ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በተያያዘም በዚሁ ደን ውስጥ በቀደሙት ጊዜያት የተለያዩ የጎሣ መሪዎች ሹመታቸው ወይም ንግሥናቸው የሚጸድቅበት የ”ኧርጉሥ እምር” የሚባሉ ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡
ዋቅም ሆነ ሌሎች ባህላዊ እምነቶች በዓላት መቀዛቀዛቸውን የተረዱት የዛራ ደማም ደላ አቅነዳ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን ባህል ጥላሸት እየቀቡ እንዲጠፋ እያደረጉ ያሉ ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው፣ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸው እንዲያብብ፣ ለሕዝብ እንዲደርስ የሚያደርጉትን በመመልከት፣ ባህሎችንና ባህላዊ ቦታዎችን እንዲንከባከቡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
እኛም በግየታ ሕዝብ መስተንግዶና አቀባባል ተደምመን፣ መርቀንና ተመራርቀን ወደ መጣንበት በሰላም ተመልሰናል፡፡ ሰላም ለምድራችን ይሁን፡፡ ለአላዋቂዎች አንድዬ ልቦና እንዲሰጠን በመመኘት እሰናበታለሁ፡፡ ሰላም!