Tuesday, 04 March 2025 20:59

ሚጣ (ትንሽዋ ፈላስፋ!)

Written by  ሙ.ቢ
Rate this item
(0 votes)

ንሸጣ (inspired) by Jana Mohr Lone. “…Children are natural philosophers.”

 

ዕለተ ቅዳሜ፡፡
ጥዋት፡፡
ወደ ቤተ ስኪያን ሲሔዱ…
ለወትሮው ታክሲ ይሳፈሩ ነበር፡፡ ዛሬ የእናት መቀነት ስለደነገጠ እግራቸውን ተማምነው ያዘግማሉ፡፡ መንገዱ ከእንቅስቃሴ ስለማይቦዝን ቅርብ ይመስላል እንጂ ወደ ሁለት ኪሎ ሜትር ይጠጋል፡፡
ይጓዛሉ፣ይጓዛሉ፣… ይጓዛሉ…፡፡
እናትና ልጅ (ሚጣ)፡፡
እናት የለበሰችው ነጠላና ቀሚስ በጥቁር ቀለም ስለቀለመ አዳፋነቱን ለመናገር አይቻልም፡፡ የዛሬን አያርገውና ሦስት ኾነው በታክሲ ሲጓዙ የሷን ጥያቄ የሚመልሰው አባቷ ነበር፡፡ ያኔ የሚጣ ጥያቄ አጭር ነበር፡፡ በታክሲ ስለሚሔዱ መንገዱ ስለሚያጥር ይኾን?
ከማዶ በመስኮት አሻግራ ከእናቱ ጀርባ ላይ ኾኖ የሚያለቅሰውን ሕፃን ስትመለከት “አባ አባ አባዬ…ያ ልጅ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?”
“የልቡ ባይሞላ፡፡”
“የፈለገው ነገር አልተገዛለትም ማለት ነው?”
“እእእ…አዎ… የኔ ልጅ እኮ የልጅ ዐዋቂ ናት!” እሙዋዋዋ… ጉንጯን ይስማታል፣ጸጉሯን ይስማታል፣ጆሮዋን ይስማታል፣ዐይኗን ይስማታል…
ይስማታል፣ይስማታል፣ይስማታል…
ዛሬ ከቁጥር ስለጎደሉ ሁለቱ ብቻቸውን፣ ለሚጣ የሀገር ቂጥ የኾነውን፣ ለእናት ግን በጎበዝ ርምጃ ተኩል ሰዓት የሚፈጀውን መንገድ ተያይዘውታል፡፡
ይጓዛሉ፣ይጓዛሉ፣… ይጓዛሉ…፡፡
ድካሙን እንዳታስብ በእንቆቅልሽ ታጠምዳታለች፡፡…
“ሚጣ ስሔድ አገኘኋት ስመለስ አጣኋት፡፡”
“እ... ቆይ እንዳትነግሪኝ… ዐውቀዋለሁ እ…ጤዛ”
“ጎበዝ የኔ ልጅ!...”
እናት እንቆቅልሽ ማምረት በተሳናት ቅጽበት የሚጣ ጥያቄ ሾልኮ ጆሮዋ ደረሰ፡፡
“እማ ለምን ታክሲ አንሳፈርም?” እራሷን እያከከች፡፡
“አሁንማ ደረስን እኮ፡፡ ለኛም በረከቱ ይበልጥብናል፡፡ ”
በረከትን ለማግኘት ያለመው የእግር ጉዞ እስኪጠናቀቅ ግን እናት የሚጣን ጥያቄ መመለስ ግዴታዋ ነው፡፡
አንድ ቀን ሰምታው አይደለም፣ አስባው የማታውቀውን ጥያቄ ስትጠይቃት “ዋ አንቺ ልጅ ቀስ ብለሽ እደጊ! እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ለድግመኛ እንዳትጠይቂኝ” ብላ ብትቆጣት “አባ ግን አይቆጣኝም ነበር” ብላ ከነፈረቀች ወዲህ እሷን መገሰጽ ትታለች፡፡ እምባዋን ለመዘርገፍ ጥቂት ሰበብ ተግታ ለምታድነው ሕፃን “ማጭድ ለምን አውሳለሁ?” በሚል፤ ጥያቄ የመጠየቅ መብት ያለገደብ ተሸልማለች፡፡ (ነፃነት በነፃ አይገኝ)፡፡
ሚጣ ገና የዐሥር ዓመት ሕፃን ብትኾን ነው፡፡ እናቷ ይሄን ስል ብትሰማኝ “ሕፃ…ን?...ሆሆሆ…የዛሬ ጊዜ ልጆች በሆድ ውስጥ በስለው ነው የሚወጡት፡፡ ወይ ሕፃን እቴ !” ማለቷ አይቀርም፡፡
እናቷ ከሚጣ የሚተኮስን የጥያቄ ሚሳይል የምታልፈው የቻለችውን መክታ፣ያልቻለችውን አረሳስታና አስረስታ ወይም ዋሽታ ነው፡፡
ጥያቄ የማያልቅባት ልጅ እናቷን ትጠይቃለች፡፡ እንዲህ…..
“አባ የሞተው ምን ኾኖ ነው?”
“በእግዜር ሕመም”
“ገዳይ ነው ማለት ነው?”
“ም…ን?” ክው ብላ ደንግጣ … “ምን ? ማ አንቺ? ማነው ገዳይ? …”
“እግዛቤር”
“አንቺ ልጅ ተይ እንዳታስቀስፊኝ! ሆሆሆሆ….”
ቀልቧን ለመሰብሰብ፣ንዴቷን ለማረቅ ከራሷ ጋር ታግላ እንደምንም ድምፅዋን ለማለዘብ እየሞከረች “…’ገደለው አይባልም፡፡ ‘ወሰደው ነው’ የሚባለው… ”አለች የሞት ሞቷን፡፡
“ውስድ ውስድ?”
“አዎ ውስድ ውስድ፡፡”
“ወዴት?”
“ሰማይ ቤት…አሁን የምንኖርበት ቤት ደግሞ የምድር ቤት ይባላል፡፡”
“አሃ…የምድር ቤትና የሰማይ ቤት ተብሎ፣ ቤት ለሁለት ይከፈላል ማለት ነው?”
“እ….አ…ዎዎዎ”
“ሀብታም ነን ለካ?”
“አ…ዎዎዎ”
ይሄን ጥያቄ በብቃት የመለሰች ስለመሰላት እናት በፈገግታ ደምቃ በእፎይታ እየተነፈሰች፡፡
“በጣም እንጂ ልጄ...ሀ…ብታም ነን…እንዲህ መልካም ጥያቄ ስትጠይቂ እግዛቤር ይወድሻል፡፡ እንጂ…እንዴው እስቲ ተይኝ…”
“እግዛቤር ጥያቄ አይወድም?”
“አዎ…. የማይኾን ጥያቄ አይወድም፡፡”
“የማይኾን ጥያቄ ምን ማለት ነው?”
እየመጣሽ ተኚ…(ለራሷ ብቻ አልጎመጎመች)፡፡ ወድያው “መልስ የሌለው ጥያቄ ማለት ነው፡፡ ”
አፀዱን አልፈው ወደ ውስጥ እየገቡ ሳለ (ምናለ ዝም ብትል)
“የሁሉ ፈጣሪ የኾነ እግዛቤር መልስ የሌለው ጥያቄ ሲጠይቁት አይወድም፡፡ እሺ ሽታዬ?”
“እእእ…ደሞ የሁሉ ፈጣሪ ከኾነ ጥያቄን ለምን ፈጠረ?”
“እሻሻሻ …እስቲ ዝም በይ! ትምርት እየተሰጠ ነው፡፡ ”
ጸጥ! ጸጥ!
እንደ ማማተብ፣እንደ መሳለም፣ አንደ መማጸን፣ እንደ መጸለይ፣
እንደ…፣እንደ…፣እንደ…
እናት ትምህርት እየተሰጠ ሳለ አካሏን እዚያ ትታ በሐሳብ ነጎደች፤ ከራሷ ጋር ማውጋት ያዘች፡፡ “…ጉድ! ጉድ! ምን ጉድ ናት? ጉድ ኖሯል የወለድኩት? ቁርጥ አባቷን! ‘ዘር ከልጓም ይስባል’ አሉ፡፡”
ጥቂት ዝም ከተባባሉ በኋላ ወድያው “እማ ራበኝ” አለች፡፡ እናት ለራሷ ብቻ በሚሰማ ድምፅ “ይሄ የት/ቤት ምገባ ልጄን ክፉ አስለመደብኝ…” አለች፡፡ ወድያው ‘በስመ አብ’ ብላ አማተበችና “ሽታዬ… ቤት አላደርስሽ አለ? ተአምረ ማርያም ይነበብና መክፈልታችንን ብልት…ከዛ ደሞ ቤት ስንደርስ ሽሯችንን አንተክትከን ብልት… እሺ ሽታዬ?…እሺ? እሺ በይኝ እንጂ?…ደሞ ከኑረዲን ሱቅ ፖፕ እገዛልሽና ጥጥት ..እሺ?”
“ ‘ኦሊፖፕ እኮ ነው የሚባለው እማ” ብላ ከፈነደቀች በኋላ አንገቷ ላይ ተጠመጠመች፡፡
“ይሁን እሱን እገዛልሻለሁ… እሰይ የኔ ልጅ! የኔ ልጅ እኮ ጎበዝ ናት” ብላ እቅፍ አድርጋ ሳመቻት፡፡
እናት ነፋሱ ብብቱ ስር ገብቶ እየኮለኮለ በሚያስፏጨው፣ከፍ ዝቅ በሚደርገው የጥድ ዛፍ ላይ ዐይኗን ተክላ በሐሳብ በረረች፡፡ ጎንበስ ቀና የሚለውን ጥድ ለተመለከተ የአዳም ረታን የአበባዋንና የነፋሱን ወግ ያስታውሳል፡፡ ጥዱ አበባዋን ተክቶ ከነፋስ ጋር እንዲህ የሚባባሉ ይመስላሉ፡፡
ነፋስ፡- “ከጓደኞችህ ተለይተህ ቤተ ስኪያን ብትገባ የምታመልጥ መሰለህ?…” እያለ ያን ግብዳ ጥድ ያስጎነብሰዋል፡፡ ጥድም በፈንታው “…እራሱን ዝቅ የሚያደርግ ‘ከፍ ከፍ’ ይላል፣ እንዳጎነበስኩ የምቀር አይምሰልህ ቀና እላለሁ፡፡ ቱቱ.. ቃል ለሰማይ ለምድር! “ ይላል ንዴት ባረገዘ ትሕትና፡፡
ለአንድ ሕፃን እንዲህ ማጠፊያ ካጠረኝ፣ ‘ …ሕፃናትን ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው’ ማለቱ ጥያቄ ቢወድ ነው?! አዎ… ቢወድ ነው እንጂ፡፡ እና ‘መልስ የሌለው ጥያቄ ሲጠይቁት አይወድም’ ብዬ ልጄን አሳሳትኳት ይኾን? ጥቂት አሰብ አደረገችና፡፡ አይ ስታድግ ‘እንዳትቀሰፊ ብዬ ነው’ እላታለሁ… ‘የውኃና የእናት መጥፎ የለውም’፡፡ ከፍ ስትል ነፍስ ስታውቅ ይቅር ትለኛለች…” እያለች በሆዷ እያጉተመተመች ሳለ አንድ ስም ከጀርባዋ ሲጠራ ሰማች፡፡
“ወለተ ኪዳን”
“ፍቅርተ ማርያም”
“ውይ በሞትኩት”
“እረ ጠላትዎ!”
“ልጆቼ በዛችሁና ነው…”
“እረ እንኳን በዛን አባ”
“ደኅና ነሽ ልጄ?”
“ይመስገን ፡፡ ደኅና ነዎት እርስዎ ? እግርዎን ተሻለዎት?”
“መቼም ደኅና ነኝ፡፡ ይመስገን፡፡ አይለቅበት፤ክብሩ ይስፋ፡፡” ወዲያው ዐይናቸውን ወደ ሚጣ ልከው ”እንዴት ናት? አንቺ ነይ እስቲ ወዲህ … እረረረ…ዐድጋ የለም እንዴ? ነይ እስቲ የኔ ልጅ” ከማለታቸው ጉልበታቸውን ልትስም ጎንበስ አለች፡፡ “ተይው ተይው ጠላትሽ ዝቅ ይበል!” ብለው ባንድ እጃቸው ቀና አድርገው በመስቀላቸው ደባበሷት፡፡
በአጭር የተቆረጠውን ጺማቸውን እያሻሹ፡-“ለመኾኑ ስንት ቀን ኾናት?”
“ሁለት ሱባዔ ልትደፍን ጥቂት ቢቀራት ነው፡፡”
“ሳታስታጉል ትጠመቅ፡፡ ለመኾኑ ለውጥ አለ?”
“አይ አባ ምን ለውጥ አለ ብለው፡፡”
“አይዞሽ! እሱ ባለው ጊዜ ይኾናል፡፡ መቸኮል አያስፈልግም፡፡ ለመኾኑ ሌላ ዐመል አለባት?”
“እረ ሌላ ዐመልስ የለባትም፡፡ እንደ ሌሎች አያንፈረፈራት፣ አይጥላት፡፡ ልቤ ውልቅ እስቲል በጥያቄ ታፋጥጠኛለች እንጂ…፡”
ወደ ቤት ሲመለሱ…
እማ “አባባ ንስሐ (የእናቷን የነፍስ አባት አባባ ንስሐ ነው የምትላቸው) ‘በሌሊት የሚበላ እንስሳ ነው’ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?”
“በጾም ሰዓት መብላት ‘ኃጢአት ነው’ ማለታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ትናንት ዓርብ አልነበር? ‘በዓርቡ በጥዋት መብላት ክልክል ነው’ ሲሉ ነው፡፡”
“እ…እ ደሞ አባባ ንስሐ… ትናንት እትየ ትዕግሥት ቤት የኾነ ነገር ሲጠጡ ዐይቻለሁ፡፡”
“ መቼ ?”
“ትናንት”
“ትናንት ትናንት?”
“አይ ሌላ ሰው ዐይተሽ ነው…”
“አንቺ ‘በዐይኔ በብረቱ’ ትይ የለ? እኔም በዐይኔ በብረቱ ዐይቻለሁ፡፡”
እናት አፏን ሸርመም አድርጋ ‘ጠበል ይኾናል…’ አለች፡፡
“በትንጢየዋ መለኪያ?”
“ሆሆ…ምናለበት ‘ደሞ በዚህ፣ በዚያ ይጠጣ’ ተብሎ ተጥፏል?”
የተከናነበችውን ነጠላ አልፎ ፊቷን ለመውረር የጎመጀውን የነፍሳት መንጋ በሚጢጢ መዳፏ ካባረረች በኋላ፡-
“እማ …አባባ ንስሐ ‘ፈጣሪ ሁላችንንም ይወደናል’ ሲሉ እኔንም ይወደኛል ማለት ነው?”
“በጣም እንጂ … በጣም አድርጎ ይወድሻል፡፡ ፍቅሩ መች ያልቅበታል…”
“ከወደደኝ አባቴን ለምን ገደለው?”
(በሆዷ ‘አሁንስ በዛ እቴ’ እያለች) “ ‘ወሰደ’ ነው” የሚባል፡፡ ‘ገደለ’ አይባልም አላልኩሽም?”
ቸኩላ “እሺ ለምን ወሸደው ?”
“ፈቃዱ ቢኾን…”
“እኔ ግን አል…ወ…ደውም፡፡”
“በስመ አብ…!..”እናት አማትባ ስትጨርስ “አንቺ ልጅ! እንደሱ አይባልም!” ለመቆጣት ሞከረች፡፡
“እምብ…የው…..እንድወደው ከፈለገ አባዬን ከወሰደበት ያምጣልኝ፡፡”
እናት ከሞት የተነሣውን አልአዛርን እያሰላሰለች “ለሱ ምን ይሳነዋል” ብላ ትክዝ አለች፤ ድምፅዋን ቀንሳ፡፡
መልስ የቸገራት እናት፣ ከማዶ ሱክ ሱክ የሚሉትን እናትና ልጅ የመሰሉ ሰዎች በአንገቷ እያሳየች “የውልሽ እነዛን እናትና ልጅ ዐየሻቸው? ዝም ብለው ነው የሚሔዱ፡፡ ልጅ አትጠይቅም፤ እናትም አትመልስም፡፡ ዝምምም… ብለው ይሔዳሉ፡፡ ደስ አይሉም?“
ዝም፡፡
“እ…የኔ እናት ደስ አይሉም? ይላሉኮ፣ አይሉም? አዎ እስኪ በደንብ ዕያቸው”
ሚጣ ዝም አለች፡፡
እናት ጨነቃት፡፡
በዝምታዋ መሃል ከራሷ ጋር ታወጋ ጀመር፡፡ “…አሁን እናትና ልጅ ይኹኑ፣ አክስትና የወንድም ልጅ ይኹኑ፣ አክስትና የእኀት ልጅ ይኹኑ፣ አያትና የልጅ ልጅ ይኹኑ፣ መንገዱ ያጎዳኛቸው ምንገደኞች ይኹኑ፣ ጎረቤታሞች ይኹኑ፣ አደራ ተቀባይና አደራ ይኹኑ፣…..
….ማ ነገረኝ? እንዴት ዐወቅሽ ብትለኝ ምን ልል ኖሯል? ሆሆሆ…ይቺ ጉደኛ ልጅ ግም ነገር ልታስተምረኝ ነው መሰል …“ ብላ በስሱ ፈገግ አለች፡፡
ሚጣ ከዝምታዋና ከቁዘማዋ ስትመለስ “አባ ግን ‘መጠየቅ ያረጋል ሊቅ’ ይል” ነበር ብላ እንባዋ ዐይኗ ላይ መታቆር ሲጀምር፣ ‘ፌርሜሎ’ ላይ ተጥዶ ሊገነፍል የሚጣደፈውን ወተት እንደሚታደግ እማወራ “እውነት ነው የኔ ልጅ፡፡ እውነትሽን ነው…” አለች እናት፡፡

Read 144 times