Tuesday, 04 March 2025 21:09

ሰውየው

Written by  ደራሲ፡- አንቶኒ ግሮኖዊች ተርጓሚ፡- ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(2 votes)

ሜይችስላውዝ ቦልኮዊዝ፤ የትውልድ መንደሬን አልለቅም ብሎ፣ ከልጁ ከጃንና ከልጅ ልጆቹ ጋር ወደ ምሥራቅ ከመሄድ አምልጦ ከጦርነቱ እንደምንም ተርፏል። ለብዙ ዘመናት የትውልድ ስፍራቸውንና ነዋሪዎቹን በፍቅር የሙጥኝ ብለው እንደኖሩት ዘር ማንዘሮቹ ሁሉ፣ እርሱም ሰማንያ ዓመት ሙሉ የኖረው፣ በዚያችው ጃዋሪ በተባለች መንደር ውስጥ ነው። አሁን ድዶቹ ጥርስ አልባ ሆነዋል፡፡ የህፃንነት ባህርይ ይታይበታል፣ የፍርሃቱ መጠን በጥቂቱ ጨምሯል።
ሰኔ 1 ቀን 1944 ዓ.ም፣ ሞቃትና ጭጋጋማ ማለዳ ላይ ወደ መንደሩ አደባባይ እንዲመጣ ሲታዘዝ፣ ይህ ምስኪን ሽማግሌ ምን ሊገጥመው እንደሚችል እርግጠኛ አልነበረም። ሆኖም ግን አደጋ ላይ መሆኑን መገንዘብ አላቃተውም፡፡ ሞትም ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ አልቀረም። እናም ናዚዎች እጃቸውን ቢያሳርፉበት ለመቋቋም ራሱን አዘጋጅቷል፡፡
ሽማግሌው እግሩን እየጎተተ ወደአደባባዩ ሄደና፣ በፍርሃትና በድንጋጤ ድባብ ውስጥ ተሰብስበው ከቆሙት ሰዎች መካከል ተደባለቀ። ጆሮው የመስማት ጉጉት እምብዛም ባይኖረውም፣ ሰዎቹ ያወሩትን ግን መስማቱ አልቀረም፡፡ የመንደሩ ሰዎች የታዘዙትን ያህል እህል ባለማምረታቸው ናዚዎች ሊቀጧቸው እንደመጡ አውቋል። ሽማግሌው በዚህ ጉዳይ ሃሳብና ትካዜ ውስጥ ገባ፡፡ “ግን ታዲያ” አለ ሽማግሌው ለራሱ፤ “መሬቷ ለነዚህ ወራሪዎች የሚፈልጉትን አልሰጥም ካለች ምን ማድረግ ይችላሉ? ምድሪቷን እንደሆነ ማዘዝ አይችሉም። ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።”
ገና ከማለዳ ጀምሮ በመንደሩ አደባባይ ተገትሮ የዋለው ሜይችስላውዝ፤ የእግሩ እብጠትና ቁርጥማት ተነሳበት። እድሜውን ሙሉ የተሸከመው ቀንበርያጎበጠው የትከሻው ህመም አሰቃየው። ከሁሉም ደግሞ ጭንቅላቱ። ያ ምስኪን የድሮ ጭንቅላቱ ህመም አየለበት- እስከአሁን መልስ ባላገኘላቸው ጥያቄዎች ከልክ በላይ ያደከመው ጭንቅላቱ።
የመንደሩ ሰዎች ከተሰበሰቡበት ዞር ሳይሉ ማለዳው አልፎ ቀትር ሆነ። ሽማግሌው በዙሪያው ሴቶች ሲንሰቀሰቁ፣ ወንዶቹ ሲራገሙና፣ ህፃናቱ በናዚ ወታደሮች ጩኸትና ግፍትሪያ በፍርሃት ሲላቀሱ ሰምቷል።
“ከህፃናቱ የሚፈልጉት ምንድነው?” ጠየቀ ሽማግሌው፤ ወደጎረቤቱ ዞር ብሎ።
“አያዩም እንዴ?” አለ ሌላኛው በሹክሹክታ፤ “ህፃናቱ እየተመረጡ ነው፣ ጠንካራዎቹና ብሩህ አእምሮ ያላቸው ወደጀርመን ይላካሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከእኛ ጋር ወደ እስረኞች ማከማቻ ይገባሉ፡፡”
“ከእኛ ጋር?!”
ሽማግሌውንም ከትውልድ መንደሩ ከጃዎሪ ሊወስዱት ነው ማለት ነው? ግን ለምን? ይሄ የማይታሰብ ነው። የማይቻል ነው። ለምን-ለምን-ለምን? ሰማንያ አመት ሙሉ ሲኖር ከቦልኮው ከተማ እልፍ ብሎ አያውቅም። ሲቃ፣ ጥልቅ ስቃይ፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መንሰቅሰቅ---ከደካማ ሰውነቱ ውስጥ ተላቅቀው ወጡ።
ይኸው የሽማግሌው ሲቃ የጌስታፖውን ሰው ትኩረት ሳበ። የ80 አመቱ ሽማግሌ ሜይችስላውዝ ተያዘና የአካባቢው የጌስታፖ ሃላፊ ዘንድ ተወሰደ። እዚያ ሲደርስ ለምርመራ ከመጡ የመንደሩ ሰዎች ጋር ገፍትረው ቀላቀሉት። ብዙ ቆየና ተራው ደረሰ። ወደ ቢሮው ጠረጴዛ ሲያመራ ራሱን እንደምንም ደግፎ ነበር። ጉልበቱ በጣም ዝሏል፡፡ ጭንቅላቱ ይዋልላል።
“ምንድነው ይኼ--አንድ ሐሙስ የቀረው ሽማግሌ!” ናዚው አንባረቀ። “ምን ቀረው ሞቷል እኮ! እንኳ መሳሪያ ሊደብቅ በቅጡ መቆም አይችልም። ወዲያ ውሰዱት!”
ወዲያው ወደሌላ ክፍል ገፈታትረው ወሰዱት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የናዚ ሃላፊዎች ወደተሰባሰቡበት ቢሮ አቀረቡት። ሁሉም ምስኪኑን ሽማግሌ አንድ ጊዜ ቀና ብለው ተመለከቱና ትንሽ የቃላት ጂምናስቲክ ሊጫወቱ አሰቡ።
“ወጣቱ፤ ስምህ ማነው?” ሃላፊው ጠየቀ።
ሽማግሌው መልስ አልሰጠም።
“መልስ እንጂ አንተ ጅል ሽማግሌ!” ከጎኑ ያለው ወታደር በጆሮው ሹክ አለው።
“እኔን ነው? እሱ ግን ወጣቱን… ነው ያለው…”
ረዥም ሳቅ በክፍሉ ተሰማ።
“አንተን ማለቱ ነው፤ ስምህ ማነው?” አለ ሃላፊው።
“ሜይችስላውዝ ቦልኮዊዝ”
“የት ነው የምትኖረው?”
“መንታው መንገድ ላይ ከዋናው መንገድ ወጣ ብሎ”
ይኼን ጊዜ ሃላፊው ነቃ አለ። ማስታወሻ ደብተር ከጠረጴዛው ላይ አነሳና ለጥቂት ጊዜ ካማተረ በኋላ በቁጣ፣
“ሜይችስላውዝ ቦልኮዊዝ የፖላንድ ስም ነው፤ እንዴት ልትጠቀምበት ደፈርክ?”
“ስሜ ነዋ” ሽማግሌው የተናገረው እርግጠኝነት በጎደለው ድምፀት ነበር።
“ታዲያ ለምን የአይሁዶቹ ቤተ አምልኮ ትሄዳለህ?” ሃላፊው በቁጣ ተናገረ።
“የአይሁዶቹ ቤተ አምልኮ” ሽማግሌው ሳያውቀው ሃላፊው የተናገረውን ደገመው።
“ኦህ! እኔ እኮ ካቶሊክ ነኝ። ወደ አይሁዶቹ ቤተአምልኮ አልሄድም”
በዚህ ሰአት ሃላፊው እንደተመኘው ሽማግሌው ተወነባብዷል። ሃላፊው ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠው ዶሴ ላይ ከመንደሩ ባሻገር በአንዲት ጎጆ ውስጥ ስለሚኖር ጥርስ አልባ ሰውዬ የተመዘገበ ነገር አለ። ምናልባት ይሄ ሽማግሌ እሱ ሊሆን ይችላል።
ሃላፊው የተባለው ሰው በትክክል ሽማግሌው ስለመሆኑ መርምሮ ለማወቅና የእለቱን ስኬታቸውን ለተሰበሰቡት ሠራኞች ለማሳወቅ የተለያዩ ማሰቃያ መንገዶችን ለመጠቀም ወስኗል።
“የት ነው የምትኖረው ሚ/ር ሜይችስላውዝ? አሁን ልብ አድርግ! መዋሸት የለም፤ ያልገባህ መምሰል የለም” ሃላፊው አስጠነቀቀው።
“ነገርኩህ እኮ ቅድም፤ ጎጆዬ ውስጥ” ሽማግሌው አጉተመተመ።
ሽማግሌው በጣም ደክሞታል። እነዚህ የናዚ ጓዶች እንዲቀመጥ ቢፈቅዱለት በወደደ ነበር።
“አንተ ብቻዬን ነው የምኖረው ብለሃል፤ ይህ ደሞ ውሸት መሆኑን እናውቃለን!” አለና የናዚው ሃላፊ ደነፋ፡፡
“አሁን እውነቷን ተናገር! አብሮህ የሚኖረው ማነው?”
ሽማግሌው ለመናገር አቅማማ። ላለፉት ጥቂት ቀናት ብቻውን ነበር። ቀደም ሲል አብረውት ይኖሩ ስለነበሩት የካትዝ ልጆች ምንም የተናገረው የለም። ለምን እንዳልተናገረ ግን ግራ ገብቶታል። የካትዝ ቤተሰብና የሱ ቤተሰብ ጓደኛሞች ነበሩ። በከተማው ነገሮች አስቸጋሪ እየሆኑ ሲመጡ እናታቸው ልጆቿን ወደ ሽማግሌው ቤት ላከች። ደግሞም ትክክል ነበረች። መሆን ያለበትም እንዲያ ነው- አንድ ወዳጅ ሌላውን ወዳጁን መርዳት አለበት።
“አንተ ሽማግሌ ተናገር! በጎጆው አብሮህ የሚኖረው ማነው?” ሃላፊው ትእግስቱ ተሟጠጠ።
“አሁን ማንም የለም። ግን…” ትንሽ ካቅማማ በኋላ፤ “ለጥቂት ሳምንት እንግዶች ነበሩኝ። አሁን ግን ሄደዋል፤ ብቻዬን ነው ያለሁት”
“እንግዶች!” አለና የበታች ሃላፊው በረዥሙ ሳቀ።
“ሰማችሁ! ሽማግሌው የሚኖረው እንግዳ በሚቀበልበት ስፍራ ነው። ለመሆኑ እንግዶቹ እነማን ናቸው?”
ሃላፊው ድንገት ወደ ሽማግሌው ዞር አለና እንደመምታት እጁን ዘረጋ።
“የካትዝ ልጆች ናቸው” ሽማግሌው ፈርጠም ብሎ መለሰ።
“ወደእኔ የመጡት አባታቸው ቦልኮው ውስጥ ከሞተ በኋላ ነው።”
“አይሁዶች! አይሁዶች አብረውህ እንዲኖሩ ትፈቅዳለህ!” ናዚዎቹ አንድ ላይ ገነፈሉ፡፡
“የጥሩ ሥነምግባር ስሜት የለህም፤ አንተ ቆሻሻ ዓሳማ!”
“ሥነምግባር! ቆሻሻ ዓሳማ?” ሽማግሌው እንደገደል ማሚቶ የሰማውን አስተጋባ።
የሽማግሌው ምስኪን አእምሮና የተወናበደ ስሜቱ ትግል ገጠሙ። እነዚህ ናዚዎች ሽማግሌውን ለመጥፎ ዓላማ ሊጠቀሙበት ነው። ሆኖም ግን ከድርጊታቸው ሊያቆማቸው አይችል ይሆናል። ስለጭካኔያቸውና ስለአረመኔ ባህርያቸው ግን የሚያስበውን ሊነግራቸው ይችላል።
“አባታቸው ሚስተር ኬዝ ጓደኛዬ ነበር። ለ50 ዓመት በመንደሩ አብረን እንነግድ ነበር” አለ ሽማግሌው ብዙም ሳይጨነቅ። “እናም ልጆቹን እኔጋ ለማስቀመጥ ደስተኛ ነበርኩ።”
“አያችሁ ደስተኛ ነበር!”የሹፈት ሳቅ ተከትሎ መጣ።
“ደስተኛ ነበር!” አለ በድጋሚ፣ ሁኔታው ወጣቱን ናዚ እያሳቀው።
“ከአይሁዶች ጋር በመኖርህ ቆሻሻነት አይሰማህም?” ጠየቀው ሃላፊው።
“የለም፤ አይሰማኝም” አለ ሜችይስላውዝ፤ ጠንከር ብሎ ግን በቀስታ።
“ነገር ግን በእርግጠኝነት ያሳፍርሃል?” ጠየቀው ሃላፊው።
“አንተ የአርያን ዘር! አይሁድ አልጋህ ላይ እንዲተኛ፣ ጠረጴዛህ ላይ ምግብ እንዲበላ፣ ገንዳህ ላይ እንዲታጠብ ፈቅደሃል። ማፈር ይገባህ ነበር!”
“የለም አላፍርም። ልጆቹ በመምጣታቸው በጣም ነበር ደስ ያለኝ”
“እናንተ ፖላንዶች ነውረኛ ናችሁ።” አለ የናዚው ሃላፊ።
“እናም ለሌሎች የአርያን ህዝቦች ደህንነት ሲባል እናንተን ከምድረ-ገፅ መጠራረግ ይገባል።”
ሽማግሌው የናዚዎቹን አካሄድ ሳይገነዘብ አልቀረም። ያሰቡትን በፍጥነት ይተገብሩ ዘንድ ተስፋ አድርጓል። በእሱ በኩል ራሱን ዝግጁ በማድረጉ ደስተኛ ነው።
“አርያን? አርያን ነህ ነው ያላችሁኝ? ደህና-- ሊሆን ይችላል፤ እኔ ግን አላውቅም” ሽማግሌው በዝግታ ነበር የተናገረው።
“ግን የአርያን ዘር መሆኔ አይሁዶችን እንድጠላ ካደረገኝ ፈጽሞ አርያን ባልሆን እመርጣለሁ። እነርሱም እንደኛው ናቸው። ደስ በሚያሰኘን ይደሰታሉ፤ በሚያስከፋን ይከፋሉ። ከኛ የተለዩ አይደሉም።”
ወጣቱ ናዚ ዘሎ ሆዱን በቡጢ ባያቀምሰው ኖሮ፣ ሽማግሌውለረዥም ሰዓት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ በወደደ ነበር፡፡
“አንተ አስቀያሚ አፍቃሪ አይሁድ!” አለና እያምባረቀ ሽማግሌውን በቡጢ ደገመው፡፡
ወዲያው ሃይለኛ ፍንዳታ ተሰማ። ለቅሶ፣ ጩኸትና፣ ሌላ ፍንዳታ! ሽማግሌው ምላሹን ሰጠ። ጀርመኖቹ በተለያዩ ጥያቄዎች በሚያሾፉበት ጊዜ ሁሉ የመጨረሻ ምላሹን ከተቀዳደደው ጃኬቱ ስር ደብቆ ነበር።

 

Read 119 times