Wednesday, 05 March 2025 20:24

ዘለንስኪ ለትራምፕ እጅ ሰጡ ይሆን ?

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(8 votes)

The Art of the Deal ወይስ እጅ ጥምዘዛ?

የዓለምን የፖለቲካና የንግድ ሥርዓት ባልተለመደ መልኩ እየገለባበጡት ያሉት (disrupt እንዲል ፈረንጅ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ድርድሩን እያጧጧፉት ነው ተብሎላቸዋል፡፡ The Art of the Deal የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት ትራምፕ፤ የተዋጣላቸው ተደራዳሪ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ክፋቱ ግን በቢዝነስ ዓለም የለመዱትን የድርድር ስልት ለፖለቲካው ዓለም መተግበራቸው ነው ሲሉ ይነቅፏቸዋል፤ተቃዋሚዎቻቸው፡፡ ደጋፊዎቻቸው ግን የድርድር ብቃታቸው ለፖለቲካውም ዓለም እየሰራላቸው ነው በማለት ያወድሷቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ድርድር ለማድረግና ከሩሲያ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈጸም በዋሺንግተን የተገኙት ዘለንስኪ፤ ድንገት በተፈጠረ የተጋጋለ ምልልስ ነበር ከዋይት ሃውስ የተባረሩት፡፡ ያኔ ሩሲያ ዳግም ወረራ እንደማትፈጽም ከአሜሪካ ዋስትና እስካላገኙ ድረስ ስምምነት ለመፈራረም እንደማይፈቅዱ ነበር ዘለንስኪ ያሳወቁት፡፡ እነሆ ከቀናት በኋላ ግን እጅ የሰጡ ይመስላሉ፡፡ ፎክስ ኒውስ እንደዘገበው፤ ዘለንስኪ ለትራምፕ በላኩት ደብዳቤ፣ ለስምምነቱ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዘለንስኪ "ለሰላም ስምምነት ዝግጁ አይደለህም" ተብለው ክብር በጎደለው ሁኔታ፣ ከነጩ ቤተ መንግሥት መባረራቸውን ተከትሎ፣ አውሮፓውያኑ ከጎናቸው የቆሙ ቢመስሉም፣ ዘለንስኪ ግን የተማመኑባቸው አይመስሉም፡፡ ለነገሩ ያለ አሜሪካ ተሳታፊነት ዩክሬን በሩሲያ ዳግም እንደማትወረር ዋስትና መስጠት አይቻልም ነው ያሉት፤ የአውሮፓ አገራት መሪዎች፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የዩክሬኑ ዘለንስኪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም - ለትራምፕ እጅ ከመስጠት ውጭ፡፡ የመጣ ይምጣ ብለው በአሻፈረኝነታቸው ከገፉበት የሩሲያ መጫወቻ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምናልባትም የአሜሪካ ጭምር፡፡ ስለዚህ እጅ መስጠታቸው ብዙ አያስገርምም፡፡

ይህንንም ታዲያ The Art of the Deal እንበለው ወይስ እጅ ጥምዘዛ? ጊዜ እውነቱን ይነግረናል፡፡ ለጊዜው ግን ዘለንስኪ እጅ ሰጥተዋል፤ ለሰውየው ትራምፕ፡፡ 

Read 1076 times