Wednesday, 05 March 2025 20:47

ኡፋሌ (የአጭር አጭር ልብወለድ)

Written by  ውብአረገ አድምጥ
Rate this item
(4 votes)

ሰፈሩን ማን ነው የሚያንቀጠቅጠው? ኡፋሌ፡፡ መንደሩን ማን ነው የሚያምሰው? ኡፋሌ፡፡ ማን ደፍሮ በኡፋሌ ፊት ይቆማል? ማን ነው ሊገዳደረው የሚችል? ማንም፡፡ ብቻውን አንድ ባታሊዮን ጦር ነው፡፡ የታላቅ ወንድሙን የሥጋ ቤት ቢላ እንደ ሰይፍ መዝዞ ሲንጎማለል ማን ነው የማይንቀጠቀጥ? ኡፋሌ አብዮት ነው፡፡
ከሻውልደማ ት/ቤት ፊትለፊት ባለው ቅያስ ውስጥ ይገኛል ኡፋሌ፡፡ ሰፈሩን ሰጥ ለጥ አድርጎ በስሩ ያስተዳድራል፤ ግዛቱ ነው፡፡ ‹‹ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት›› ብሎ ሠራዊቱን ያሰማራል፤ መንደሩን በአንድ እግሩ ያቆመዋል፡፡ በተለይ ሌላ ሰፈር ሄዶ የተጠቃ ልጅ ካለ ወደዚያ ሰፈር ወዲያውኑ ታጣቂዎቹን ያዘምታል፡፡ ወዮላት ያቺ መንደር፤ ወዮላት ያቺ ሰፈር፡፡ በቅፅበታዊ ወረራ የነፃ አውጪ ጦር መአት አውርዶባት ይመለሳል፡፡ ኡፋሌ የሚለው ስም ብቻውን ያርበደብዳል ያንበረክካል፡፡ እንግዳ የሆነ ሰው የኡፋሌን ሰፈር ደፍሮ አያቋርጥም፡፡ በተለይ ሴቶች እንኳን በእውናቸው በህልማቸውም በዚያ በኩል አያልፉም፡፡ ኡፋሌ በእርግጥ በሴት አይታማም፡፡ ተከታዮቹ ግን ‹ወንድ የምንሆነው በሴት ነው› ያሉ ይመስል የትኛዋም ሴት የአንዱ ጎረምሳ ክንድ ሳያርፍባት በሠላም አታልፍም፡፡ እንግዲህ ፍቅረኛዬ ‹‹ይህን ጦር ሰብሬ እመጣለሁ›› ነው የምትለኝ፡፡ ‹‹ውዴ አሁን እየተሻለኝ ነው፤ ሰሞኑን ድኜ እነሳለሁ› ብላትም ቁጣና ሳግ በተናነቀው ድምፅ፤ ‹‹አንተ ታመህ እኔ ጤነኛ የምሆን ይመስልሀል? አካሌ እኮ ነህ፤ እኔ ያለ አንተ ሙት መሆኔን እያወቅህ እንዴት አትምጪ ትለኛለህ? ከፈለጉ ለምን አይገድሉኝም፤ እመጣለሁ ብያለሁ እመጣለሁ›› ብላ በንዴት ስልኳን ዘጋችብኝ፡፡
ታምሜ ብተኛም ፍቅረኛዬ መጥቼ እጠይቅሀለሁ ማለቷ የበለጠ በሽታ ሆኖብኛል፡፡ ‹‹አትሞክሪው ጎረምሶቹ አናሳልፍም ብለው ስለሚያስቸግሩሽ ይቅር አትምጪ›› ብላትም አሻፈረኝ አለች፡፡ የፈራሁት አልቀረም ገና የመጀመሪያውን ቅያስ ሳታልፍ ኡፋሌ እጅ ላይ ወደቀች፡፡ ኮስተር ብላ ‹‹ስማ ብትለቀኝ ይሻልሀል፤ የኡፋሌ ፍቅረኛ ነኝ›› አለችው፡፡ ኡፋሌ ከት ብሎ ስቆ ‹‹መለኛ ነሽ፤ ለማንኛውም ኡፋሌ ማለት እኔ ነኝ›› ብሏት ቤቴ ድረስ ሸኝቷት ተመለሰ፡፡
ድንጋጤው እንዳለቀቃት ፊቷ ራሱ ይመሰክራል፡፡ ‹‹አንተ ሲያስፈራ! እኔ እኮ ሌላ ሰው መስሎኝ ‹የኡፋሌ ነኝ› ስለው እኮ ነው እየሳቀ እዚህ ድረስ የሸኘኝ›› ብላ ባለማመን ስሜት አስር ጊዜ ወደ በሩ ታያለች፡፡ ‹‹አይዞሽ አሁን አምልጠሻል፤ እግዚአብሔር ከአንበሳ መንጋጋ ፈልቅቆ እንዳወጣሽ ቁጠሪው›› እያልኩ አረጋጋኋት፡፡ በቃ ከዚያን ቀን በኋላ ሰፈሩን ለመደችው፤ ኡፋሌም ቤቴ ድረስ እየሸኛት ይመለሳል፡፡ እኔም ‹‹እፎይ›› ብዬ ፍቅሬን ማጣጣም ቀጠልኩ፡፡ በመሀል ግን ስደውልላት ስልኬን ማንሳት አቆመች፡፡ በተደጋጋሚ ብደውልም አታነሳም፡፡ በመጨረሻ እያመመኝም ቢሆን እንደምንም ብዬ ቤቷ ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ ከቤት ወጥቼ ልክ ኡፋሌ ቤት ጋር ስደርስ ከኡፋሌ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው እየተሳሳቁ ከቤት ሲወጡ ተገናኘን፡፡ አዞረኝ፡፡ ከመውደቄ በፊት አጠገቤ ያገኘሁት ድንጋይ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ኡፋሌ ደረቱን ገልብጦ ቀጥታ ወደ እኔ መጥቶ ‹‹ምነው አመመህ እንዴ? አይዞህ›› አለኝና ‹‹መጣሁ ቤት ጠብቂኝ›› ብሏት እኔንም ቤቴ ድረስ ከሸኘኝ በኋላ ‹‹ሴት አትመን እሺ›› ብሎኝ ተሰናብቶኝ ሄደ፡፡
ዛሬ ይኸው አባት እሆናለሁ ያልኩት ሰውዬ፤ የክርስትና አባት ሆኜ አረፍኩት፤ በኡፋሌ ቀጭን ትዕዛዝ፡፡

 

 

Read 148 times