(“የደጋ ሰው” በተሰኘው አልበም ውስጥ ባለው “ፖስተኛው” ዘፈን መነሻነት የተጻፈ ምናባዊ የግል እይታ)
ፖስተኛ ነኝ!
ዕድሜ ዘመኔን ከቆላ ደጋ፣ ከደጋ ቆላ እያልኩኝ ከናፋቂ ለተናፋቂ፣ ከአፍቃሪ ለተፈቃሪ፣ ከዘመድ ለዘመድ፣ ከወዳጅ ለወዳጅ፤ ጦማር ሳመላልስ ዕድሜዬን የፈጀሁ።
በዚህም ውለታና ሙገሳን ከሰዎች፣ የጽድቅ ቦታንም ከእግዜሩ የማልሻ። ከላኪ ለተቀባይ በማደርሰው ጦማር የሰዎች የናፍቆት “ጥም ሲረካ”፣ ደስታ ሲከባቸው በማየት ብቻ እኔም ደስታን የማገኝ ፖስተኛ ነኝ።
ዛሬ ግን እንግዳ ነገር ገጠመኝ...
ጦማር በማመላለስ በፈጀሁት ዘመኔ እንደዛሬው ያለ እንግዳ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። ከጅምሩ ሁሉም ጥሩ ነበር። ከሩቅ ሀገር ከደጋ፤ ቁልቁል ሌት ከማዕልት ስከንፍና ስገሰግስ “ለቆለኛዋ ናፋቂ” ጦማሬን ይዤ እንደደረስሁ ሀገሬው በልዩ ሁኔታ፣ በደስታ፣ ጦማሩ በተላከላት ሴት አንደበት፤ ሙገሳ አዘል ዜማ ከሽኖ ነበር የጠበቀኝ።
ፖስተኛው መጣ ለናፍቆታችን ጥም የሚያረካ
አልኩልህ ውዴ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ ባንተ ብመካ፤
የናፋቂን ልብ ስብራት የምጠግን፣ ለጉጉቱ እፎይታን የምቸር እኔ ፖስተኛው፤ እንዲህ ባለ ዜማ ስሞጋገስ አለልማዴ ልቤን ሞቆት፣ ደስታው አቅሜን ፈትኖት ልሞት ነበር።
ምን ዋጋ አለው!
ውዳሴው አፍታ ሳይቆይ የሞቀ ልቤን የሚያቀዘቅዝ፣ ግለቱን በረዶ የሚያደርግ የተቀባይ ብሶት ሰማሁ እንጂ።
ቢያስደስተኝም ማሸጊያው ፖስታው፤ ጌጡ ማማሩ
እጅግ ጓጉቼ ከፍቼ ባየው፤ የለም ጦማሩ።
በእርግጥ እኔም አይቼው በወደድኩት ውብ የጦማሩ ማሸግያ ፊቷ በደስታ ፍካት ከብርሃን ሲስተካከል አስተውዬዋለሁ። በፖስተኛነቴ የሰዎችን ደስታ ማየት ነው ዋናው ዳረጎቴ አላልኩም? በዛም ደስታን ሸመትሁ። ያ ፊቷን ያፈካው፣ ልቧን በደስታ የሞላውና በውብ የታሸገ ጦማር ግን ውስጡ ሲከፈት ይህችን ምስኪን አፍቃሪና ናፋቂ ተቀባይ በከባድ ሀዘን የመታ ባዶ ጦማር ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን እኔን አቀባዩን፣ ፖስተኛውንም ለግራ መጋባት ሰጥቶ ወደ ባዶነት የቀየረኝ ባዶ ፖስታ። የዚህኔ ነው ከዚህች ሴት ሀዘን በላይ የኔ ገዝፎ፤ ሰቀቀን የወረረኝ።
የተቀበልኩት የአንተን እንግዳ
ደግሼ ነበር ጥዬ ፍሪዳ
ደስታዬ ቢታይ ላ’ምባው በሙሉ
አወይ እድሏ ጻፈላት አሉ።
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ጦማር ይዤ ካ’ምባው መድረሴ ነበር። ሀገሬው ፖስተኛነቴን ያውቃል። ይድረሱ ለማን፤ ላኪውም ማን እንደሆነ አላጣውም። የእኔን መድረስ አይታ ደስታ የፈነቀላት ቆለኛዋ ናፋቂ “ፊሪዳ ጥላ” በዜማ ተቀበለችኝ። እኔ ምክንያት ሆኜለት ከድግሱ የተቋደሰው ሀገሬውም “አወይ ዕድሏ” በማለት በሞቅታ አዳንቆ ነበር።
በኋላ ጉድ ሊመጣ...
ውዳሴና ድግስ አጣምሮ የተቀበለኝ ሀገር፤ የጠቆረ ፊቱን አዙሮ በትዝብት ያየኝ የጀመረው ከዳሱ የሚናኘውን፤ መነሻው አምሮ፣ ነገር ግን በብሶት የታጀበውን ዜማ እንደሰማ ነው። እኔን በአይኑ ቂጥ በመገርመም እና በመታዘብ ሲቀባበለኝ፤ ይህቺን በባዶ ጦማር ልቧ የተሰበረን ሀዘንተኛ ሴት አይዞሽ ለማለት እንኳን ጊዜ ሳያባክን ነበር።
ብቻ ዳስ ሙሉ ዐይን እኔን ይገረምመኝ ያዘ። የዚህኔ ሰቀቀን የፖስተኛ ነፍሴን ይበሳሳት ጀመር። በዚህ የሀገሬው የጠቆረ ገላማጭ ፊትና አሽሟጣጭ ምላስ፤ በዚህ ደግሞ የዚህች ናፋቂ ሴት ሀዘን ብርክ አስያዘኝ። እኔ የሆንኩትን፣ የደረሰብኝን ግን ማንም አልተረዳልኝም። የእኔን ሰቀቀን፣ የእኔን ሰቆቃ ያየልኝ የለም።
በሽቶህ ልርካ ደብዳቤም ባላይ
ጠረንህ አለ እማሸግያው ላይ
እስኪ ንገረኝ ማን እንደከፋ
ምን ብትጽፍልኝ መልዕክትህ ጠፋ።
ተስፋ በመቁረጥ፣ ሀዘን እየበላት፣ በእንባ ያመጣውትን ባዶ ፖስታ ወደ አፍንጫዋ ሰዳ እየማገች “በሽቶህ ልርካ ደብዳቤም ባላይ” ስትል ዜማዋ ከሙሾ አውራጅ ተመሳስሎብኝ ሆዴን አንሰፍስፋዋለች። “ምን ብትጽፍልኝ ነው መልዕክትህ የጠፋው?” እያለች ምላሽ የሚሰጣት ያለ ይመስል ትጠይቃለች።
በፖስታ አመላላሽነት የብዙ ዓመታት ልምዴ፣ ጦማር ምንም ቢጻፍበት እንደማይጠፋ አውቃለሁ። “በቃል ያለ ይጠፋል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል” ነው ብሂሉም። ፍቅርንም፣ ናፍቆትንም፣ ሀዘንንም፣ ትዝብትንም፣ ጥላቻንም ሁሉን ቋጥሮ ከላኪ ወደ ተቀባይ ይደርሳል። እሷም ይሄን መጠየቋ እውነቱ ጠፍቷት ሳይሆን ግራ መጋባት የምትለውን ቢያሳጣት ነው። በዚህ ሁሉ መሐል እኔ እምነት በልቼ ጦማሩን ከፖስታው እንዳላጎደልኩ እሷ የተረዳችኝ ሲመስለኝ፣ ልጽናና ቢቃጣኝም ሰቆቃዬን ለማራገፍ ግን አቅም አልሆነኝም።
ከግራ መጋባቷ ጋር የተዋሃዱ፣ ብስጭት የተሸከማቸው፣ ከቆረጠ ልቧ የሚንጠባጠቡ የብሶት ቃላቷ ውስጥ ሳይቀር መሰበሯን ሳደምጥ ይበልጥ ሰቆቃዬ ከበደ። እንዲህ አለች ይህቺ ምስኪን።
አያ ሾንኮራ ልቤ ጠብቆ
የአጨዳው ሰዓት ቢታይ ሸንበቆ
በቆሎ አጭጄ ተክዬ አገዳ
እንዴት ለፋለሁ ለቆሮቆንዳ።
ምንስ ብትል አልፈርድም። እኔም እሷ በቆመችበት ቆሜ እንዲህ ያለው መከራ ቢደርስብኝ ከዚህ የገዘፉ ዘለፋዎችን ለማለት ምላሴ አትሰንፍም ነበር። ግን ላኪውን ምን ነካው? እላለሁ ደጋግሜ። ምን ነካው? እንዲህ ያለ ረብ የለሽ ጨዋታ በመጫወት የአፍቃሪውን ልብ ከመስበር፣ እኔ መልዕክተኛውን ከማሳቀቅ የሚያገኘው ትርፍ በእውነቱ ምንድነው? አንድነቱን ጥላቻ ያዘለ፣ አጥንት የሚሰብሩ ቃላት ጽፎ ቁርጥን መንገር ዓለም አልነበር? እያልኩ ከራሴ እሟገታለሁ።
ታጥፎ በፖስታ እንዴት ይላካል
እምባ አበባ አይደል በምን ይደርቃል
ላኩት ባዶ እጁን መሰናበቻ
አይነግርህም ወይ ሀዘኔን ብቻ?
በሀዘን ያፈሰሰችውን እምባዋን ተአብ ፈጥሬ፣ ልክ እንዳበባ አድርቄ፣ ውብ ፖስታ ውስጥ አሽጌላት ባደርስና ያ ደገኛ የሰራውን ግፍ ባሳየው፣ እኔም ከሰቆቃዬ ብድን ተመኘው። ይህ ምኞቴ እውን ይሆን ዘንድ የመለኮትን ተራዳኢነት ሽቼም ነበር።
ጉድለቴ ገሃድ ይውጣ አደባባይ
ቃላት አልጽፍም በጦማሬ ላይ
የጠቆረ ፊት መንገር ካልካደ
ማዘኔን አይቶ በቃኝ ከሄደ።
“በምላሹ ምን አለች?” ብሎ መልስ ለሚጠብቅ ላኪ ጋር ባዶ እጄን ሰዳ፤ ያደረጋትን፣ የሰራትን፣ የሆነችውን መንገር እንደሚችል አምናለችና እንደ እምነትሽ ይሁንልሽ ብቻ አልሁ።
የዝምታ መልእክቷን ተቀብዬ ከእሷ ሀዘን በላይ የሰበረኝ ሰቆቃ የወፍጮ ድንጋ ከአንገቴ የተንጠለጠለ ያህል አስጎንብሶኝ፤ አያቀረቅሩ አቀርቅሬ ከዳሱ ሹልክ ብዬ አመለጥሁ። በሩጫ ያህል እርምጃ ከመንደሩ ሳመልጥ፤ ያቺ ምስኪን በቀደመ ሙሾ አውራጅ ለዛዋ የስነ-ቃል ጦር መዛ ከኋላዬ ወረወረች። ስነ-ቃላዊ ጦሩ እንዲህ ይሰኛል...
የጠሪ አክባሪ ጋብዞ መከራ
ሰርጉ አማረለት ያለሙሽራ።
ከነበረኝ ፍጥነት በላይ ጨምሬ የደጋውን መንገድ ስያያዝ የማስበው፤ ያንን ደገኛ ለምን እንዲህ እንዳደረገ አጥብቄ መጠየቅን ነበር። ነገር ግን መልሱ ምንም ቢሆን ምን የዚህችን ምስኪን አፍቃሪ የደቀቀ ልብ እንዳይጠግን፤ የእኔን በሰቆቃ የሳሳች ነፍስ ከቦታዋ እንዳይመልስ አውቃለሁ።
በተለይ የእኔ ሰቆቃ አይድንም...