Saturday, 08 March 2025 21:12

የቤተሰብ ዕቅድ ጉዳይ እንደፖለቲካ አጀንዳ እየተቆጠረ መሆኑ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የቤተሰብ ዕቅድ ጉዳይ እንደ ፖለቲካ አጀንዳ እየተቆጠረ ነው የተባለ ሲሆን፤ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የሰላም ዕጦትና የአቅም ውስንነት ዋነኛ ፈተናዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል።
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማሕበር ከትላንት በስቲያ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው አምስተኛ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የውጭ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች የተገኙ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ ስለሚስተዋሉ ችግሮች በስፋት ተነስቷል፡፡ በጉባዔው ላይ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የአውሮጳ አገሮች ለአዳጊ አገራት በጤና ዘርፉ በኩል የሚያደርጓቸውን ድጋፎች መቀነሳቸው ተመልክቷል።
በተጨማሪም፣ የፖሊሲ ለውጦች መከሰታቸውን ተከትሎ፣ በስነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የጉባዔው ተሳታፊዎች አስረድተዋል። በተለይ በጽንስ ማቋረጥ፣ በኤችአይቪ ምርመራና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ የደረሰው ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን በመጠቆም፣ “ኢትዮጵያ በስነ ተዋልዶ ሕክምና ላይ ጠንካራ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ዕምቅ አቅሞች ያሏት አገር ብትሆንም፣ እንደ ሰላም ዕጦት፣ ድህነትና የበጀት ዕጥረት ያሉ ውስብስብና ተያያዥ ተግዳሮቶች እየፈተኗት ያለች አገር ናት” ተብሏል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አካል ጉዳተኛና በግጭት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ከስነ ተዋልዶ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ማግኘት አለመቻላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ በስነ ተዋልዶ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ማቋረጣቸው የብዙዎችን የተዋልዶ ጤንነት አደጋ ውስጥ የሚከት እንደሆነ ተመላክቷል። ይህን ተከትሎ፣ ያልታቀደ ዕርግዝና እና ጥንቃቄ የጎደለው የጽንስ ማቋረጥ ባልታሰበ ፍጥነት እንዲጨምር የራሱ የሆነ ጫና እንደሚያስከትል ነው በጉባኤተኞቹ የተነገረው፡፡
ችግሮችን ለይቶ ትክክለኛውን የመፍትሔ አቅጣጫ መከተል ከተቻለ፣ የሚደርሰውን ጉዳት መቆጣጠር እንደሚቻል የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤ መንግሥት ከአሜሪካ ተቋማት በሚደረጉ ድጋፎች ብቻ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ማሰብ የለበትም፤ ብለዋል። "የአገር ውስጥ ተቋማትን ማገዝና ማሳደግ፣ በእነርሱ ላይ መንተራስ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል።” ሲሉም መክረዋል፡፡
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማሕበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ ዓመታዊው የተዋልዶ ጤና ጉባዔ መካሄድ የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ2017 አንስቶ መሆኑን አስታውሰው፤ የስነ ተዋልዶ ጤና በየጊዜው አዳዲስ ዕውቀቶችንና ልምዶችን እንደሚፈልግ ጠቅሰዋል። አክለውም፣ በጤናው ዘርፍ የአሜሪካ መንግሥት ለስነ ተዋልዶ ጤና ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ድጋፍ እንደማይቀጥል ይፋ ማድረጉን አውስተዋል።
የተዋልዶ ጤና ስራዎች በውጭ እርዳታ ላይ መንጠልጠላቸውን የጠቁሙት አቶ አበበ፤ “ከመንግሥት ጋር ተጋግዘን የተሻለ ስራ ለመስራት እነዚህን ተግዳሮቶች መቋቋም ያስፈልጋል። ከዚህ ቀደም የአገር ውስጥ ሃብት ከማሰባሰብ ይልቅ ውጭው ላይ በብዛት ትኩረት ይደረግ ነበር። አሁን ግን የአገር ውስጥ ሃብትን ለማሰባሰብና ስራዎችን ለማስቀጠል ከዚህ ቀደም በነጻ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በተወሰነ መጠን ክፍያ ማስከፈል በሚያስፈልግበት ወይም እንዲሁ በነበሩበት በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሂዷል” ብለዋል።
አያይዘውም፤ “በመንግሥት በኩል በትምባሆና የአልኮል መጠጦች ላይ ተጥሎ የሚሰበሰበውን ታክስ ለጤናው ዘርፍ ገቢ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች አየተደረጉ ነው። ነገር ግን ገቢ የማድረጉ ሂደት ወደ ስራ አልገባም” ሲሉ አስረድተዋል።
የአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥ በዘርፉ የሚያስከትለውን ክፍተት ለመቅረፍ ተጨማሪ በጀት ከመንግሥት መመደብ ይኖርበታል የሚሉት አቶ አበበ፣ “ለስነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ ሲቀንስ፣ የእናቶችና ሕጻናት ሞት በከፍተኛ ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል” ብለዋል። ዋና ዳይሬክተሩ መንግስት ያለውን አቅም በመፈተሽና በማስተባበር ከሲቪል ድርጅቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በግጭት ምክንያትም ሆነ በሌሎች አደጋዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በሚገኙባቸው መጠለያዎች የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስጠት ቢያስፈልግም፣ ፈታኝ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተው፣ “አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሞያዎች ስነ ልቦናቸው የተጎዳ ነው። በመሆኑም የስነ ልቦና ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።” ሲሉ ተናግረዋል።
“የቤተሰብ ዕቅድ ጉዳይ እንደ ፖለቲካ አጀንዳ እየተቆጠረ ነው።” ያሉት አቶ አበበ፤ የአንድን አካባቢ የህዝብ ቁጥር ከሚገባው በላይ ጨምሮ ማቅረብና የበለጠ ድጋፍ ማግኘት በክልሎች መካከል ፉክክር መፍጠሩን ገልጸዋል።
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማሕበር፣ በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚሰሩ ከ85 በላይ የአገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈ ድርጅት ነው።

Read 669 times