Saturday, 08 March 2025 21:28

እማማ ዝናሽ ፤ ከማሳቅ በሻገር! (እሴት እና ተረክ)

Written by  በዙፋን ክፍሌ
Rate this item
(1 Vote)

"እድሜ የሰጠው አያየው የለም! " ይባላል። እንዲህ መባሉ በሁለትና ከዚያ በላይ ጊዜዎች[ ዘመናት ፣ ወቅቶች ፣ ሁኔታዎች ፣ አጋጣሚዎችና ክስተቶች... ወዘተ] ተገኝቶ ፣ ለውጡን ፣ ዕድገቱን ፣ ልማቱን ጥፋቱን አይቶ፣ "ድሮ በእኛ ጊዜ... " እያለ ለሚተዝት ፣ አላፊውን ወይም የደረሰበትን ጊዜ ለሚረግም [ወይም/እና ] ለሚያመስግን ሽማግሌ ይመስለኛል። በተቀረ ሁሉም ትውልድ የየደረሰበትን ጊዜ በረከትም ሆነ መርገምት ተቋድሶ ያልፋል።
አሁን የእኛው ጊዜ ፥ ይኸ ዘበናዩ!
ዘበናይ ጊዜ ነው መቼም! ኮምብጦር የሚሉት ዕቃ ሲወጠን ግዙፍ ነበር። እያደር አነሰ። ቤት ከሚያህል አንስቶ ' እጠረጴዛ ዋል ' (Desktop) እሚሉት ላይ ደረሰ። በበነጋው ' እጭን ዋል' (Laptop) ወደሚሉት ተለወጠ። ውላጤው ለጥቆ እየጉያችን እንደ ዳዊት እምትሻጥ ' እመዳፍ ዋይ' (Palmtop) የሆነች ፣ 'ቅብዝብዚት' (mobile) እምትባል ኮምቡጦር ላይ እንገኛለን።
አዲያ ዛሬ ፣ በየደቂቃው ' እጭን ዋሉን' (Laptop) እና 'ቅብዝብዚቱን' (mobile) ከፍቶ "ዓለም አማን? ገበያው ደህና? ማርካቶ ናጉማ? ማን ፈሳ ማን ገማ? ንጉሥ ደኻንዱ? ሳይል የሚያድር የሚውል የለም። አዲያ የደረሰ ፥ የደረሰ ዜና ትኩሱን ከነአተላው በሚላፍበት በይህ ዘበናይ ጊዜ፣ "አካም ኦልታኒ? አካም ቡልታኒ?" ከሚባሉት ርዕሶችና ገጸ ሰብኦች (Character ) መካከል በተውኔት (Entertainment) ረገድ እማማ ዝናሽ ዝነኛዋ ናቸዉ።
እማማ ዝናሽ ፤
እድሜ ናቸዉ። ዕርግና (እርጅና ) ናቸዉ። ታሪክ ናቸዉ እኚህ እማማ። ቅርስ ናቸዉ። የተረክና የእሴት ቅርስ። ሙዳይ ናቸው። በገርነት(Authenticity) እና የዕርግና ንጽሕና ፣ በድፍረት እና በትሕትና ፣ በጽርፈት (ስድብ ) እና በቁልምጫ ፣ በባለ አገርነት እና በሃይማኖተኝነት ከሚናገሯቸው ንግግሮች ውስጥ ከማሳቅ በላይ የሆነ ነገር አለ። እኔን ያዝ ያደረጉኝን ደጋግመው ከሚሏቸው ብሂሎቻቸውና እዚያ ዉስጥ የተሰገሰጉ እሴቶቻቸው ጥቂት ብቻ ነጥቦች ላውጋችሁ።
ሀ) "አባቴ ቄስ ናቸው ፥ ታቦት ተሸካሚ.."
[አናታቸውን እየተመተሙ]
እማማ ዝናሽ ፤ ከሚኮሩበትና በደስታ ከሚያነሱት አገረ ሙላዳቸው(Place of birth) ቡልጋነት እኩል[ ምናልባት በላይ] ለአያሌ ጊዜ ፣ ላገኙት ሰዉ ሁሉ "አባቴ ቄስ ናቸው ፥ ታቦት ተሸካሚ.." ይላሉ።[አናታቸውን እየተመተሙ።] ይኼ ሃይማኖት ነው፡፡ ይኼ ታሪክ ነው። ይኼ ኩራት ነው። " እኔ የእገሌ ልጅ ነኝ" ማለት ኩራት ነው። "ዘየኀብእ ሃይማኖቶ ኢይከውኖ ሞገስ" ይላል ሊቁ። እምነቱን የሚደብቅና የማይኮራበት ሞገስ የለውም። ጥላ ቢስ ነው። ትከሻው አይከብድም። ቃሉ አይታመንም። ዓይኑ ውስጥ ኩራት ፣ ልቡ ዉስጥ ድፍረት ፣ ግንባሩ ላይ ወዝ የለውም። ሃይማኖትህ ምንም ይሁን፥ ቢሻህ ልጅህ ፣ ሚስትህ ፣ ብትል አገርህ ፣ እናትህ ፣ ሳይንስ ፣ ኦዳው ( ዋርካው ) ፣ መልካው ፣ አባይ ወንዙ ፣ ዳሸን ተራራው ፣ አድዋ አምባው ይሁን ሃይማኖትህ ፣ ኤርታሌ ገሞራው ፣ ንሥር አሞራው ይሁን የሚያሳምንህ - ግን እምነት እምነት ነው፡፡ አውቀህ የምትገባበት ፣ አምነህ የምትቀበለውና እብለት ፣ ብልጠት ፣ ዘዴ(tactic ) የሌለበት 'የማትሰወረው አንተ' ማለት ነው ሃይማኖት። ታዲያ የማትሰውረው ሃይማኖት ሲኖርህ ከተርታነት ትሻገራለህ። ከፍ ትላለህ። መንፈሳዊ ትሆናለህ። አገርህን ጉልበተኛ ጣልያን ይወርብሃል። ንጉሥህ በማርያም ምሎ ዝመት ይልሃል። ትዘምታለህ። ጊዜው ረመዳን ነው። ጊዜው ሁዳዴ ጦም ነው፡፡ ቦታው አድዋ አምባ ነው። በማርያም ምሎ ክተት ያሉህ ጃንሆይ ኲይናት( ጦርነት) ላይ ነህና እህል እየቀመስክ ተዋጋ ይሉሃል። እግዜር ቸር ነው፤ ደጉን ጊዜ ሲያመጣው ትጦመዋለህ ብላ ይሉሃል። አንተ ገበሬው የአባ ቢላዋ ልጅ ወይ ፍንክች! በጦም አንጀትህ ፣ በሃይማኖተኛ ልብህና የሞራል ከፍታህ ጥልያን እንዴት ትቻልህ?! አቃተቻ! ይኼ ነው ይኸውልህ "አባቴ ቄስ ናቸው ፥ ታቦት ተሸካሚ.." ብሎ ማለት። ጌታዬ ፣ መስቀል ሁሉ ማዕተብ ይሆናልን? የለም! ሃይማኖት መንፈሳዊ ከፍታ ላይ መድረስ ነው። ፍቅርን መዋኘት ፣ ሰብአዊነትን መላበስ ነው። ተአምኖ እና ትውክልት ነው፡፡ ተርፎ እሴት ፣ ተርፎ ትርክት(narattive) ተርፎ ተረክ ፣ ተረት ፣ ዘፈን ይሆናል። ግጥም ይሆናል። ይኼ ነው ይኸውልህ "አባቴ ቄስ ናቸው ፥ ታቦት ተሸካሚ.." ብሎ ማለት።
ለ) "የሰዉ ያለህ ፥ የመንግሥት ያለህ"
እማማ ዝናሽ ፣ የመጣባቸው ሰው ቀጣፊ ፣ ሌባ ፣ አደገኛ እና መስመር የለቀቀ ከመሰላቸው "የሰዉ ያለህ ፥ የመንግሥት ያለህ....ኡኡ" ይላሉ።
"የሰዉ ያለህ"
ሰው። አዎና ሰው!!
"የሰው ያለህ" ማለት በጎረቤት ፣ በእድር ፣ በወገን መመካት ነው፡፡ በአገር የመመካት ሩብ ነው፡፡ አረቦን ነው፡፡ "የሰው ያለህ" ሲባል የሰማ ወደ አፉ የሰደደውን ጉርሻ እንኳን ይመልሳል። እጁ የገባውን ሽመልም አንካሴም አንስቶ መሮጥ ነው። እሳትም እንደሆን ፣ አውሬም እንደሆን ፣ ጠብም እንደሆን ማጥፋት ፣ መገላገል ፣ አለሁ ደረስኹ ማለት ነው፡፡
ልብ ብለሃል? "የሰው ያለህ" ሲባል ሃይማኖት ፣ ነገድ ፣ አገረ ሙላድ ፣ ፍልስምናህን አይመለከትም! አታደንቅም ይኼን? "ሰው ሆይ " ስትባል "እነሆኝ" ማለት። አሁን ፍራ "የሰው ያለህ" ብትል ቀድሞ ደራሹ በራሪ ካሜራ እየሆነ መጥቷል።
"የመንግሥት ያለህ.."
መንግሥት ማለት አገር ማለት ነው። አገር ያለው ነው " በሕግ አምላክ" የሚለው። "የመንግሥት ያለህ.." ማለት በአገር ተስፋ ማድረግ መመካት ነው፡፡ በአገረ መንግሥት (State) ተሥፋ የቆረጠ ፣ " በሕግ አምላክ" እያለ የተደፈረ ፣ "የመንግሥት ያለህ.." ብሎ መንግሥት አልደርስ ያለው ትውልድ ነው ወደ ኩርፊያ የሚኼደው። ይሰውረነ። የአገረ መንግሥትን መታፈር አይንሳን። "በሕግ አምላክ" ክብሯን አትጣብን። አሜን።
ሐ) "ወታደሮች አሉ ፥ እጠራለሁ"
እማማ ዝናሽ ፣ "የሰዉ ያለህ ፥ የመንግሥት ያለህ....ኡኡ" ብለው አያበቁም። "ወታደር አለ! ወታደር ይመጣልሃል! መንግሥት ይቀፈድድሃል! '' ይላሉ። ይህን ሲሉ ልበ ሙሉነታቸውና ኩራታቸው አባቱ ከሩቅ ሲመጣ አይቶ እንደሚኮራና እንደሚቅበጠበጥ ልጅ ነው። ወታደር ማለት መመኪያ ነው፤ በእማማ ዝናሽ ተረክ ውስጥ። ወታደር አስፈሪነቱ ለግፈኛ ጠላት እንጂ ለአገር ልጅ ትምክህት ነው። ከላይ ካነሳነው በአገረ መንግሥት (State) ማመን ፣ መመካትና ተሥፋ ማድረግ ጋር የሚያያዝ ነው "ወታደሮች አሉ ፥ እጠራለሁ" ማለት። ያንን ክብር ለአገረ መንግሥታችን እና ሕዝባችን ያድልልን። አሜን በል አንተ ከአሜን ይቀራል!
ጌታዬ ፣ ከሆነልኝ በሌላ ክፍል እመለሳለሁ እንጂ ዘርዝሬም አልዘልቀው። ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ ነውና ወጋችንን ጋብ አድርገን ፣ አፋችንን በማር ይዘን ከመሰናበታችን በፊት ስለ እማማ ዝናሽ እንድናወጋ ምክንያት የሆነንን ዘካርያስ ኪሮስን ከመቀመጫችን ብድግ ብለን እናመሰግናለን። ዕድሜ ይስጥልን!

Read 556 times