Monday, 10 March 2025 08:32

የገበያ ማረጋጋትና ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል ሚና ምንድን ነው?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ጥራቱ የወረደ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ በጭራሽ አንፈቅድም”


በመዲናችን አዲስ አበባ ህገ-ወጥነትን በዘላቂነት ለመቆጣጠር ስለተቋቋመው የገበያ ማረጋጋትና ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል የከተማዋ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ሲያስረዱ፤ ግብረ ሀይሉ ሰፋ ያሉ ተቋማትን ያቀፈ ነው ይላሉ - እነዚህም የገበያ ማረጋጋት፣ የገቢ አሰባሰብና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
ግብረ ሃይሉ በውስጡ የንግድን፣ የከተማ ገቢን፣ የማህበራትን፣ የሰላምና ፀጥታን፣ የፖሊስን፣ የኢንዱስትሪን እንዲሁም የኮሙኒኬሽንን ተግባራት አቅፎ እንደሚገኝ የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ ግብረ ሃይሉ በየጊዜው ያደረጃጀት ለውጥ ቢያደርግም፣ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መዝለቁን ጠቁመዋል፡፡
ግብረ ሃይሉ የተቋቋመው ተቋማቱ የሚሰሩትን ሥራ ለመተካት አለመሆኑን ሲያስረዱም፣ ይልቁንም ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታትና ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ግብረ ሃይሉ በዋናነት ገበያ ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ም/ከንቲባ ጃንጥራር፤ ለዚህም ምርት የሚያቀርቡት እነማናቸው፣ እንዴት ይቀርባል የሚሉትን በማጣራትና በማጥናት ሥራ ላይ ማተኮሩን ተናግረዋል፡፡
“በአንድ በኩል የሰብል ምርት በማህበራት በኩል እንዲቀርቡ ማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ ያቋቋመው የንግድ ስራዎች ድርጅት ምርት በቀላሉ ከአርሶ አደሩ ገዝቶ እንዲያቀርብ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር፣ በግሉ ዘርፍ የሚቀርብ ምርት ህጋዊ የሆነ የግብይት ስርዓት ማምጣቱን እያረጋገጡ መምራት” ግብረ ሃይሉ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ መንግሥት ባቋቋማቸው የግብይት ማዕከላት ውስጥ አርሶ አደሩ በቀጥታ መጥቶ ምርቱን የሚሸጥበት ሁኔታ መመቻቸቱን የማየት፣ የመቆጣጠርና ድጋፍ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም ም/ከንቲባው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የእሁድ ገበያዎች በትክክል እየተተገበሩ ነው ወይ፣ ግብይቱ ላይ በቂ ምርት አለ ወይ፣ ማነው ምርቱን የሚያቀርበው፣ የሚሸጡበት ዋጋ ትክክል ነው ወይ፣ የሚሉትን ጉዳዮች የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ እነዚህን ከማረጋገጥ አንፃር ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡
“በከተማችን ብዙ ዳቦ አምራች ፋብሪካዎች ተቋቁመዋል፤ ትልልቆቹን የሸገር ዳቦና የብርሃን ዳቦዎች ጨምሮ ሰፋ ያለ ቁጥር ያላቸው ከግል ተቋማት ጋር በትስስር ያቋቋምናቸው ዳቦ ቤቶች አሉ፡፡ በግልም የተቋቋሙ ዳቦ ቤቶች አሉ፡፡” ያሉት ም/ከንቲባው፤ “የዳቦ ምርት በተገቢው በገበያው ላይ እንዲቀርብ ለማድረግ ማህበራት ምርት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ አምጥተው ዱቄት ለሚያመርቱ በማቅረብ የዳቦ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡
በመዲናዋ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ለእኒህ የልማት ሥራዎች ደግሞ ከተማዋ ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ያስፈልጋታል፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፉት 6 ወራት አስተዳደሩ 111 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የተሻለ ውጤት ማሳየቱን ያስታወሱት ም/ከንቲባ ጃንጥራር፤ ይህም ሊሆን የቻለው የገቢ ግብር መሰረቱን በማስፋት በተከናወነ ስራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከግብረ ሃይሉ አንድ ንዑስ ኮሚቴ በማቋቋም ደረሰኝ የማይቆርጡ አካላትን መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ም/ከንቲባው፤ በተለይ መርካቶ አካባቢ የብሎኪንግ ሥራ በመጀመር ከደረሰኝ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ከንግድ ቢሮ፣ ከገቢዎች፣ ከሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር በቅንጅት በተከናወኑ ስራዎች የተሻለ ውጤት መምጣቱን ይገልጻሉ - ሆኖም በቂ ነው የሚባል አይደለም፤ ብለዋል፡፡
“ይሄ በሌሎችም የገበያ ቦታዎች ሁሉ መቀጠል ያለበት ነው፤ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ መንግሥት ገቢውን ካልሰበሰበ ልማትን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ ስለዚህ ህገወጦችን ወደ ህግ ስርዓቱ በማስገባት ህጋዊ ንግድን ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ግብረ ሃይሉ የምርት አቅርቦት እጥረት በገበያ እንዳይኖር እንዲሁም በግብይት መካከል ያለውን የደላላ ሰንሰለት ለመበጣጠስ ትኩረት አድርጎ በመሥራቱ ሰፊ ቁጥር ያላቸው በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ወደ ህጋዊነት መምጣታቸውን ም/ከንቲባው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ከ14 ሺ በላይ የሚሆኑ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ይሄ ደግሞ የገቢ ግብር መሰረቱን በማስፋት ከፍተኛ ገቢን ለመሰብሰብ አስችሎናል፤ብለዋል፡፡
ግብረ ሃይሉ በህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ አይደለም አተኩሮ የሚሰራው፡፡ በተለይ በበዓላት ወቅት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ማህበረሰቦች ገበያ ወጥተው በቅናሽ ዋጋ የተለያዩ ምርቶች የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ያረጋግጣል፡፡
“ለምሳሌ የማህበራት ሱቆች ጤፍ መሸጥ ብቻ ሳይሆን እሴት በመጨመር ዱቄትና እንጀራ ያቀርባሉ፤ በተመሳሳይም ዳቦ የሚያቀርቡ ማህበራትም አሉ፤ በበዓላት ወቅት ለበዓላት የሚሆኑ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ ማህበራትን እንጠቀማለን፡፡” ይላሉ ም/ከንቲባው፤ በማህበራቱ አማካኝነት የእርድ እንስሳት ሳይቀር ለበዓላት እንደሚቀርቡ በመግለጽ፡፡
በመዲናዋ ለዋጋ መናርና ለገበያ አለመረጋጋት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ምርት የሚደብቁ ህገ ወጥ አካላት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ይህን ህገ ወጥ ተግባር ለማስቀረት ግብረ ሃይሉ ምን እየሰራ እንደሚገኝ ም/ከንቲባው ሲያብራሩ፤ “የግብረ- ሃይል አደረጃጀቱ በክፍለ ከተማም አለ፤ ይህ ግብረ ሃይል በንዑስ አደረጃጀት በሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሰብሳቢነት፣ የንግድንና ገቢን የንዑስ ኮሚቴው አባል በማድረግ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ ቁጥጥር የሚያደርገው በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን ወሰን ዘለል ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ከሸገር ሲቲና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በትብብር ይሰራል፡፡” ብለዋል፡፡
ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “የምርት መጋዘናቸው ቡራዩ ወይም ገላን አሊያም ዱከም ወይም ለገጣፎ ይሆንና ምርታቸውን እዚህና ሌላ ቦታ ይሸጣሉ፤ እነዚህን የመሳሰሉ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በቅንጅት በመሥራት እየተከላከልን እንገኛለን፡፡” ይላሉ፡፡
ቁጥጥሩ በዚህ መንገድ እየተሰራ ቢሆንም፣ ከሁሉም አስቀድሞ ከነጋዴው ማህበረሰብ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር መካሄዱን ይናገራሉ፡፡
“ህብረተሰባችን ለኑሮ ጫና መጋለጥ የለበትም፤ እናንተም ድርሻ አላችሁ፤ ህጋዊ ንግድን ማንቀሳቀስ ትችላላችሁ፤ደረሰኝ መቁረጥ አለባችሁ፤ምርት በመደበቅ ሸማቹ ላልተፈለገ የዋጋ ጭማሪ መጋለጥ የለበትም፤ በሚሉት ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በክፍለ ከተማ፣ በየደረጃው ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ወደ ህጋዊ እርምጃ የማስገባት ሥራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡” ብለዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ እንደ መርህ አድርገን የወሰድነው ምርትን ወደ ገበያ ማቅረብ እንጂ መከታተል፣መቆጣጠርና ማሸግን አይደለም፤ ይላሉ ም/ከንቲባው፡፡
“የመጀመሪያውና ዋና አጀንዳችን ምርት ወደ ገበያ ይቅረብ፤ ነጋዴውም ይነግድ አምራቹም ያቅርብ፤ ህብረተሰቡም በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ ይሸምት፤ ይህን ማድረግ የሚያስችል የግብረ-ሃይል እንቅስቃሴ ይኑረን ነው፤በዚህም መሰረት ነው እስካሁን እየተሰራ የዘለቀው፡፡” ብለዋል፡፡
“በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ አልፎ መንገራገጮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤የግለሰብ ፍላጎቶችም ይኖራሉ፤ እነዚህን ጥቆማ በደረሰን ቁጥር እናርማቸዋለን፤ እርምጃም እንወስዳለን፤ ለምሳሌ ገቢ ላይ እነዚህ ችግሮች ሲያጋጥሙ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ሌብነትና ጉቦኝነት በመሳሰሉት ላይ በአመራሩ ውሳኔ እየተሰጠ የማስተካከል ስራ እየተሰራ ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ግብረ ሃይሉ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ም/ከንቲባው ሲያብራሩ፤ ጥራቱ የወረደ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ በጭራሽ አንፈቅድም፤ በጥራት ጉዳይ አንደራደርም ይላሉ፡፡
“ለዚህም እኛ ብቻ ሳንሆን እንደ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ያሉ አካላት የሚመረቱ ምርቶች ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፤ ከስታንዳርድ በታች የሆኑ ምርቶችንም ያስቆማሉ፤ እኛም ይህን እንደግፋለን፡፡” ብለዋል፡፡
ነገር ግን ከዚያ በፊት ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ ድጋፍ እናደርጋለን የሚሉት ም/ከንቲባ ጃንጥራር፤ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ማህበራትን በመደጎም አቅማቸውን እያጠናከረ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ተደርጎ የሚመረተው ምርት ከስታንዳርድ በታች ከሆነ ግን እርምጃ እንደሚወሰድና ተቋማት ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ስለማድረጋቸው በግብረ ሃይሉ እንደሚገመገሙ ጠቁመዋል፡፡
ግብረ ሃይሉ ትኩረት ያደረገባቸው የእሁድ ገበያዎች 210 እንደሚደርሱ የሚናገሩት ም/ከንቲባው፤ ከእነዚህ ውስጥ ስታንዳርዳቸውን ጠብቀው በተሻለ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱት 180 ያህሉ ናቸው ይላሉ - በአንድ ወረዳ በአማካይ ሁለት የእሁድ ገበያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠቆም፡፡
ለመሆኑ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ የገበያ ሥፍራዎች ሲባል ምን ማለት ነው?
“ስታንዳርድ ስንል የገበያ አመቺነት፣ የሚቀርበው የምርት አይነት፣ ምርቱ በወጥነት የሚቀርብ መሆኑ፣ የገበያው ዋጋ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሆኑን መነሻ በማድረግ የተቋቋሙ የግብይት ቦታዎች ናቸው፡፡” በማለት አብራርተዋል፡፡
ዋናው ዓላማችን የሰንበት ገበያዎች የህብረተሰባችንን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንዲሰራባቸው ማድረግ ነው የሚሉት ም/ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ ግባችን በኑሮ ላይ ጫና የሚያሳድሩ የምርት ዋጋዎች ነዋሪዎች በቅናሽ የሚሸምቱበትን እድል መፍጠር ስለሆነ ገበያዎቹ በዚያ ልክ ስታንዳርዳቸውን ጠብቀው እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው፤ ብለዋል፡፡
ም/ከንቲባው የገበያ ማረጋጋትና ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይልን አስመልክቶ ከሰጡት ሰፊ ማብራሪያ ተነስተን ግብረ ሃይሉ በመዲናዋ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ መረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ በዋናነት ከተለያዩ የአስተዳደሩ ተቋማት ጋር ቅንጅትና ትብብር በመፍጠር የገበያ ማረጋጋትና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም፣ በዚህ ብቻ ግን አልተወሰነም፡፡
ግብረ ሃይሉ ህጋዊ የንግድ አሰራርን እያሰፋ ይገኛል፡፡ የገቢ ግብር መሰረትን በማስፋት የአስተዳደሩን ገቢ በማሳደግ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ የከተማዋን ማህበረሰብ የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ በዚህም የከተማዋንና የነዋሪዎቿን ችግር በመቅረፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

Read 272 times