ኑሮ በጥረት በግረት ነው። ፈተና አያጣውም። መጠኑና ድግግሞሽ ቢለያይም፣ ችግር የማይገጥመው ሰው የለም። ዛሬ ባይሆን ነገ፣ ዘንድሮ ባይሆን ለከርሞ ፈተና ይጠብቀዋል። ችግሮችን ተቋቁሞ፣ ፈተናዎችን አሸንፎ ካላለፈ፣ የዕድሜ ልክ ሕይወት ይበላሻል።
ሸክም ቢበዛበትም፣ ትዕግሥቱ ቢሟጠጥም፣ ተንበርክኮ እጅ ላለመስጠት፣ ወድቆ ላለመቅረት ይጣጣራል። ምናልባት ኑሮን የማቃናት ዕድል ያገኝ እንደሆነ ያስባል፤ ያልማል። ግን ዛሬን ካለፈ ነው። ዘንድሮን ከተሻገረ ነው። ከድካሙ ጋር ይታገላል። ከራሱ ጋር ይሟገታል። መታገል ቢሰለቸውም መንገዱን ላለመሳት ይንገታገታል።
የሚያዘናጋና የሚያሳስት ሞልቷል። "ሸውጄ ማለፍ ብችል ችግሮች ይቃለላሉ" ብሎ ያስባል፡፡ ያኛውን መዋሸት፣ ይኸኛውን መሸንገል፣ ያኛውን መሸፈጥ፣ ይኸኛውን መደለል፣ አለ ልክ ክቦ አሸርግዶ፣ አለ ኀጢአቱ ወንጅሎ አዋርዶ… በአቋራጭ መንገድ ከፈተና ማምለጥ፣ ግራ ቀኝ አምታትቶ የሚመኘውን ማግኘት ቢችልስ?
ይህ ባይሆን እንኳ፣ ለጊዜው እፎይ ማለት፣ ዕዳውን ለነገ ማሳደር፣ ተስፋ ቆርጦ መቀመጥ ይችላል፡፡ “ለየትኛው ሕይወት ነው? የነገን ሳላውቅ በከንቱ መጨነቅ ሞኝነት ነው” ብሎ ራሱን ለማታለልና “ለማጽናናት” መሞከር አያቅተውም። ቀላል የማምለጫ ቀዳዳዎችን ለማግኘት ይጓጓል - የተቸገረ የተጨነቀ ሰው። ወደ ምኞቱ የሚያደርሱ ፈጣን መንገዶችን ቢያጣ እንኳ፣ ከኀላፊነት ስሜት ለማምለጥ ብዙ ምክንያቶች ይታዩታል። ከአሰልቺ ጥረት የሚገላግሉ ሰበቦች በምናብ ይመጡለታል፤ ወይም ይመጡበታል። አይፈረድበትም፡፡ በኑሮ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች አካልና መንፈስን ይፈታተናሉ።
እንዲያም ሆኖ፣ ሌላ አማራጭ የለውም። የዛሉ እግሮቹን ለእርምጃ ቢያነቃንቅ ነው የሚያዋጣው። ማንቀላፋት የናፈቀው የረገበ መንፈሱንም ቀስቅሶ ቢያነቃቃ ነው የሚበጀው። ሳይረፍድበት ቢነሣ ነው የሚሻለው።
ተስፋው ሳይጨልም፣ ስንፍና ሳይወርሰው፣ ወደ መጥፎ ተግባር ሳይንሸራተት፣ ማንነቱ ሳይቆሽሽ፣ መንፈሱ ሳይረክስ… ራሱን ተቆጣጥሮ፣ መሰናክሎችን እየተሻገረ መጓዝ አለበት። ለዚህም ብርታትና ጽናት ያስፈልገዋል።
አንዳንዴ እህል ውኃ ሳይቀምስ ቢውልም ሥራውን ከእልባት ማድረስ፣ ሰውነቱ በድካም ዝሎ ዕረፍት እያማረውም ሳይጨልምበት ጫካውን አቋርጦ ጉዞውን መቀጠልና ካሰበው ቦታ ማደር ይኖርበታል። አለበለዚያ ሥራውና ጉዞው በከንቱ የአውሬ ሲሳይ ሆኖ ይቀራል።
ደግነቱ፣ የዘወትር ሕይወታችን ሁልጊዜ በአጣዳፊ ችግሮች የተጨናነቀች በአስፈሪ አደጋዎች የተከበበች ላትሆን ትችላለች። ከተለመዱ ችግሮች ጋር በተለመው የሥራ ውሎ የዘወትሩን ኑሮ እናስኬደዋለን። ወደ ተስፋ ጭላንጭል የሚያስጠጋ መቆናጠጫና መወጣጫ፣ ወደ ተሻለ ኑሮ የሚያመራ የደረጃና የእርካብ መረማመጃ ማግኘታችንም አይቀርም። በእመርታ ወደ ከፍታ የምንሸጋገርበት ዕድል ለመፍጠር መጣጣርም እንችላለን። በመደበኛ የኑሮ ዑደት ውስጥ ይሄ ሁሉ ይቻላል። በተለይ ደግሞ አመቺ ጊዜ ሲገጥመን። ነገር ግን፣ በአመቺ ጊዜ ላይ ብቻ ወይም በተለመዱ ችግሮች ላይ ብቻ የሚያገለግል ዓቅም በቂ አይደለም።
ቤታችን ሙሉ ሲሆን ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም የሚያዋጣ፣ ተጨማሪ አዳዲስ ችግሮችንም መጋፈጥ የሚችል ዓቅም ከሌለን፣ የኑሯችን የሕይወት ስሜት ይደበዝዛል። ዛሬ አለ ሲሉት ነገ ድንገተኛ ነፋስ መጥቶ እንደሚወስደው ገለባ ይሆንብናል። ዛሬ ቆሞ የታየ፣ ነገ እንዳይወድቅ መተማመኛ አይኖረውም።
በምቹ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በፈተና ጊዜም ቢሆን፣ በትክክለኛ መንገድ ለመጓዝ የሚታገል እንጂ ለአቋራጭ መንገድ እጁን የማይሰጥ፣ በስንፍና ወደ ስህተትና ወደ ጥፋት የማይንሸራተት የመንፈስ ብርታት ብቻ ነው የሰው ልጅ መተማመኛ። በስኬት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በከባድ ጊዜም ቢሆን፣ ባለ በሌለ ዓቅሙ ሥራውን አሳምሮ በጥበብ የማከናወን ትጋት፣ መልካሙን ጎዳና ይዞ የመጓዝ ጽናት ያስፈልገዋል።
አንዳንዴ ስንቁን እየቆጠበ ለበርካታ ሳምንታት መሥራትና መጓዝ ሊኖርበት ይችላል - በቀን አንዴ ብቻ እየበላ። አንዳንዴ፣ “አይዞኝ” እያለ ራሱን ከማበረታታት ውጭ ሌላ ድጋፍና ሌላ አማራጭ ላያገኝ ይችላል። ፈተናዎችን የመሻገርና ችግሮችን የማሸነፍ ብርታት፣ ነው ዋስትናው፡፡ ዓላማውን በጥረት ግረት ለፍሬ የማብቃት ጽናት ብቻ ነው አለኝታው።
ካልሆነ ግን፣ በጅምር ከመንገድ ይቀራል። የዛሬ ቡቃያው ነገ ይደርቃል። ትንሽ ሲደናቀፍ ለመልካም ተግባር ወኔ ያጣል። በትንሽ በትልቁ እየተሰናከለ ለመራመድ ይሰንፋ።
ይህም ብቻ አይደለም። መልካም የመንፈስ ብርታት ይርቀዋል። ጊዜያዊ ስሜት ያታልለዋል። ራሱን መቆጣጠር ይሳነዋል። “ለዛሬ ብቻ ብሳሳት፣ ለዛሬ ብቻ ባጠፋ”… በማለት ራሱን እያታለለ ራሱን ወደ ስህተት ይገፋፋል። የጥፋት መንገድን ወደ ራሱ ይጠራል። ለክፉ መንፈስ እጁን ይሰጣል።
በችግር ጊዜም ቢሆን መልካም መንፈስን በጽናት የሚይዝ ጠንካራ ሰብዕና፣ ነው መዳኛው፡፡ በፈተና ጊዜም ቢሆን ለመጥፎ መንፈስ መግቢያ መንገድ የማይሰጥ ጠንካራ ባሕርይ ነው ጋሻው። አዎ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም። ቀላል ቢሆንማ ባላስቸገረን፤ ፈተና ባልሆነብን። ቀላል ስላልሆነ ነው ፈተናነቱና አስቸጋሪነቱ። ግን ውጤቱም የዚያኑ ያህል ነው። ከፈተና ጋር መታገል ለከንቱ አይደለም።
ውድ ነገር ዋጋው ውድ ነው። ሕይወት ደግሞ ከሁሉም የላቀ ውድ ነገር ነው። አእምሮ፣ አካልና መንፈስ የተሰናኙበት ሕይወት፣ እጅግ በጣም ውድ ነው። ዋጋውን የመክፈል ዓቅምና ፈቃደኝነት ያስፈልጋል።
አስገራሚው ነገር፣ የሕይወትን ትርጉም የምናጣጥመበት የሰመረ ሕይወት ውስጥ መሟላት ካለባቸው ነገሮች መካከል፣ “ዋጋውን የመክፈል ዓቅም፣ ፈቃደኝነትና የተግባር ጥረት” አንዱ ነው። ፍሬና ውጤቱም ያስፈልጋሉ። ነገር ግን፣ ፍሬና ውጤት እየዘገነ እንደልብ የሚሰጥ አንዳች ተአምረኛ ኀይል ብናገኝ፣ የሰመረ ሕይወት አይኖረንም። የሕይወትን ትርጉም ማጣጣም አንችልም።
በአንዳች ተአምር የተሰጠንን ፍሬ በብዙ ጥረትና ግረት በእጅጉ እንዲበረክት ከታገልንና ከተሳካልን፣ የሕይወትን ትርጉም ማጣጣም እንችላለን። ከሌላ ሰው ማሳ ውስጥ ገብተን እንዳሰኘን ለመሸምጠጥና ለመብላት ብቻ የምንመኝ ከሆነ ግን፣ ከጨቅላ ሕጻንነት ወይም ደግሞ ከዝንጀሮ ቡረቃ የተለየ የሕይወት ትርጉም አናገኝበትም። የጥረት ውጤት፣ የሥራ ፍሬ… ማለታችንም ውጤት ብቻ ትርጉም ስለማይኖረው ነው። ፍሬ ብቻ… ጣዕም አይኖረውም ባይባልም፣ የሥራ ፍሬ ሲሆን ግን “የሰውን ክብር ከፍ የሚያደርግ የሕይወት ትርጉምና ጣዕም” አለው።
ለዚያም ነው፣ የጣዕሙና የትርጉሙ ያህል ዋጋ መክፈል የግድ የሚሆነው። ውድ ነገር ደግሞ ዋጋው ውድ ነው። አንዳንዴም እጅግ ይከብዳል። በተለይ ደግሞ በችግርና በፈተና ጊዜ። በተለይ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የሚያደክም ሲሆን…
ወይ ያለ ጥረት የሚሸመጠጥ ፍሬ ያምረናል። ወይ… ሁሉም ይቅርብኝ በሚል ስሜት ተስፋ ቆርጠን መቀመጥ ያሰኘናል። ይፈታተነናል።
የጥረታችንና የድካማችን ብዛት ወዲያውኑ ውጤት የማይሰጥ፣ በማግስቱ አብቦ የማያፈራ ሲሆን … ትዕግሥትን የሚያስጨርስ፣ ተስፋችንን የሚያደበዝዝ ሲሆን… ዋና መተማመኛችን ለፈተና እጅ የማይሰጥና ችግር የማይበግረው ጠንካራ ሰብእና ነው - በተግባር ከተመሰከረለት የብቃት ልሕቀት ጋር የተዛመደ የመንፈስ ጽናት።
ጾም የዚህ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ሳንበላ ብንውልም፣ ሳንሠራ አንውልም እንደማለት ዐይነት። ሳንበላ ብንውልም፣ ፊታችንን አጥቁረን ሰው ላይ አንነጫነጭም የሚል መንፈስ ዐይነት። ችግሮችን መቋቋም፣ ስሜታችንን መቆጣጠርና ኑሮን በተገቢው መንገድ መምራት እንችላለን የሚል ትርጉም።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ችግርንና ፈተናን ከፍ ከፍ ለማድረግ አይደለም። የብዙዎቻችን ኑሮ ጾም ሳንጨምርበትም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ደግሞም ጦም ያደረን ማብላት የተጠማን ማጠጣት እንጂ፣ በጾም መቸገር ራሱን የቻለ በጎ ዓላማ ወይም ድንቅ ብቃት አይደለም።
ይልቅስ፣ ፈልገነውና ፈቅደነው ሳይሆን በኑሮ ሂደት የሚጋረጡብን ፈተናዎችና የሚገጥሙን ችግሮችን ተቋቁመን ማለፍ እንዳለብን የሚያሳይ ምልክትና መታሰቢያ ሊሆን ይችላል - ጾም። የሰብዕና ጥንካሬና የመንፈስ ጽናት እንደሚያስፈልግ እንድናስታውስ የሚረዳ ምልክት።
ደግሞም ጾም ለታይታና ለይስሙላ ቢሆን ትርጉም የሚያጣው በዚሁ ምክንያት ነው። የጾምን አስመስለን፣ በጎን ለጉርሻ እየተጣደፍን ከራሳችን ጋር ብንሻማ፣ ትርጉሙን እናጠፋዋለን። ስንቃችንን መቆጠብና በቀን አንዴ ብቻ እየበላን መጓዝ ሲኖርብንስ ምን ልናደርግ ነው? ራሳችንን እያታለልን በአንድ መዳፋችን ዓይናችንን ጨፍነን በሌላ መዳፋችን ስንቃችንን እየበረበርን ልናራቁት ነው? በማግስቱ ባዶ ለመቅረት፣ በሳልስቱም መራመድ አቅቶን መንገድ ለመቅረት?
በእርግጥ እንዲህ ዐይነት ችግር ላይገጥመን ይችላል። ቢሆንም ግን፣ ይብዛም ይነስ ከችግር የሚያመልጥ ሰው የለም። ከወታደሮች ስልጠና ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። በውድቅት ሌሊት መነሳት፣ በቀውጢ ተኩስ ውስጥ መለማመድ፣ ማታና ቀን ያለ ዕረፍት ያለ እንቅልፍ ትጥቅና ስንቅ ተሸክሞ መጓዝ… ሥልጠናው ከባድ ነው። ያታክታል። ያማርራል። ትዕግሥትን ይፈታተናል። ነገር ግን፣ አስቸጋሪው ሥልጠና ለአስቸጋሪ የጦርነት ጊዜ ይጠቅማል።
ሁል ጊዜ ጦርነት ይኖራል ማለት አይደለም። ላያጋጥም ይችላል። ታዲያ፣ በአድካሚ ልምምድና በአስቸጋሪ ስልጠና ራስን ማሰቃየት ለምን ያስፈልጋል? ጥቅም ላይኖረው ነገር በከንቱ መልፋትና ዋጋ መክፈል ምን ይረባል? ጋራ ሸንተረሩን በእግር ለመጓዝ የሚያስገድድ ችግር ላይፈጠር ይችላል።
ግን ደግሞ፣ ችግሮችና ጦርነቶች ያጋጥማሉ። አንዳንዴም በተደጋጋሚ። ቀድሞኑ በሥልጠና አካላቸውንና መንፈሳቸውን ያጠነከሩ ሰዎች ናቸው፣ ከባባድ ፈተናዎችን የማለፍ፣ ጥፋትን የመከላከልና በጎ ተግባር የመፈጸም ብርታት የሚኖራቸው። ለእንዲህ ዐይነት ጊዜ አስቀድሞ የተከፈለ ዋጋ ነው - ሥልጠናው። ለወደፊት ይጠቅማል ተብሎ የተከፈለ መሥዋዕትነት።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ጾም እንደ ሥልጠና መቆጠር የለበትም። ይልቅስ እንደ መታሰቢያ፣ እንደ ማስታወሻ ቢቆጠር የተሻለ ይመስለኛል። ለመንፈስ ጽናትና ለሰብዕና ጥንካሬ ከፍ ያለ ዋጋ እንድንሰጥ፣ በችግርና በፈተና ጊዜ ከመልካሙ ጎዳና ሳይዛነፉና መንገድ ሳይስቱ የመጓዝ ዓቅምን እንድናከብር፣ እንድንመኝና ለዚያም እንድንጥር የሚገፋፋ መታሰቢያ ነው።
ግን፣ ሌሎች ትርጉሞች ሊኖሩት አይችሉም ማለት አይደለም። የጸጸትና የንስሐ ምልክት ተደርጎ ይታያል። ወታደራዊ ግቢና ሥልጠና… ለጥፋተኞች ማረሚያ ቅጣትና ተግሣጽ የሚሰጥ ግቢ ብናደርገው እንደማለት ነው። ጥንካሬንና ጽናትን ለመገንባት የሚያገለግሉ ከባባድና ፈታኝ የአካል እንቅስቃሴዎች፣ ለቅጣትና ለተግሣጽም ሊያገለግሉ ይችላሉ። ጾምም እንደዚያ ዐይነት ትርጉም ይሰጡታል። ዋናው ቁም ነገር ግን፣ በፈተና ጊዜም የመጽናትና ችግርን የማሸነፍ መንፈስን እንድናከብር የሚያገፋፋ ምልክት መሆኑ ላይ ይመስለኛል።
Monday, 10 March 2025 09:04
Published in
ነፃ አስተያየት