Monday, 10 March 2025 09:14

ማንነቴን ሳሰላስለው---

Written by  ደሳለኝ የኔአካል - ጠበቃና የሕግ አማካሪ
Rate this item
(1 Vote)

“--ግላዊ ማንነታችንን ትተን ማኅበረሰቡ እንድንሆን የሚጠብቅብንን ማንነት ስናሳድድና እሱኑ ስንተውን ከእውነተኛው
እኛነታችን ጋር እንተላለፋለን። አስቀድሞ ከተሰራው ቅርጽ ጋር እንድንገጥም ሲባል ራሳችንን በራሳችን ከርክመን ከርክመን ሌላ
ሆነን እናርፈዋለን። ለመመሳሰል ስንል ልዩነታችንን በህዝብ ቀለም እንደልዛለን።--”


ፍልስፍና ከሚመረምራቸው ዋነኛ ጉዳዮቹ መካከል የሰው ልጅ መነሻ ከየት ነው? መድረሻውስ (መጨረሻው (መጨረሻ ካለው)) ምንድነው? ዕጣ-ፋንታው ተወስኗል ወይስ አልተወሰነም? (ነፃ ፈቃድ አለው ወይስ የለውም?) ሰው ‘በልቡ እንዳሰበው’ ይኖራል ወይስ ሕይወቱን የሚዘውርለት ሌላ ‘አካል’ አለ? የልቡ ሃሳብስ ቢሆን የራሱ ነው ወይስ የሌላ? የሚሉት ጥያቄዎች የታላላቆቹ ፈላስፎች ጠረጴዛ ላይ ሲነሱና ሲወድቁ የኖሩ የመሟገቻ ሃሳቦች ነበሩ። አርስቶትል (Nicomachean ethics, book III)፣ ቅዱስ ኦገስቲን (City of God, book V, and On free choice of the will)፣ ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ (Summa theologica First Part Question 19, anf Question 83)፣ ሙሴ ማይሞኒደስ (the guide for the perplexed)፣ ስፒኖዛ (the ethics)፣ ሳርትር (being and nothingness)፣ ኒቼ (beyond good and evil)… ሌሎችም በርካቶች በእጃቸው ላይ የሚገኙትን ጠጠሮች በተለይ በነጻ ፈቃድ ጉዳይ ላይ ወርውረው አልፈዋል። ጉዳዩ ስለ ሰው ልጅ ነውና በአማኝም በኢ-አማኝም ዓይን ተመርምሯል። ከፈላስፋ ጀምሮ ከመነኩሴ እስከ ሳይንቲስት የምለው አለኝ ብለው በደረሱበት ልክ ሃሳባቸውን ገልጸዋል። የሰው ልጅ ነፃ ፈቃድ አለው፤ ዕጣ-ፋንታው አልተወሰነም የሚሉ፣ ዕጣ-ፋንታው ተወስኗል የሚሉ፣ ሁለቱ ሃሳቦች የሚታረቁ ናቸው የሚሉ እና እግዚአብሔር ነገሮች ከመሆናቸው በፊት ማወቁ ከነፃ ፈቃድ ጋር አይጋጭም የሚሉ ወዘተ አስተሳሰቦች ተነስተዋል። ያም ሆኖ የሰው ልጅ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ጉዳዩ በየጊዜው እየተነሳ የሚመረመር እንጅ መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት የሚመለስ አይደለም። በሀገራችንም ቢሆን የተለያዩ ሰዎች ነገሩ አሳስቧቸው አመለካከታቸውን በየስራዎቻቸው ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም አስቀምጠው አልፈዋል።

ድምጻዊ ይርጋ ዱባለ በአንድ ሙዚቃው ላይ፤
የሚሆን ይሆናል የማይሆን አይሆንም
ለቁጥቋጦ ያለው መቼም ዛፍ አይሆንም ይላል።
በዕውቀቱ ስዩምም ከይርጋ ጋር በሃሳብ እንደሚስማማ የሚያሳዩ ግጥሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል ብቻ በስብስብ ግጥሞች መድበሉ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ቁመተ-ዶሮ (አጭሬ ግጥም ቁመተ-ዶሮ እንዲሉ ሊቁ ኪዳነወልድ ክፍሌ) ግጥሙን እንጥቀስ።
እግዜርና ዳዊት በአንድ ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል እንኳንስ በጠጠር። ይላል።
ይህን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተሳሰብ በኤፍሬም ስዩም ስራ ውስጥም እናገኛለን።
…በተጻፈ ተውኔት
ባለቀ ዝግጅት
አሜን ማለት ከላይ መብረር
ለምን ማለት ክንፍን መስበር…
እያለ የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ፅዋ ተርታ፣ የተጻፈውን ተውኔት በስክሪፕቱ መሰረት መተወን ብቻ እንደሆነ አስረግጦ ይከራከራል። በርከት ያለው ሕዝባችንም ቢሆን (ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ) አስተሳሰቡ የሰው ልጅ ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል ወደ ሚለው ያደላል። ከፈጣሪው ጋር የሚጣላ ስለሚመስለው ነፃ ፈቃድ አለኝ እያለ ይሽኮረመማል እንጅ አኗኗሩ፣ ስነ-ቃሉም፣ ስነ-ግጥሙም ሲመረመር ግን ‘ለቁጥቋጦ ያለው መቼም ዛፍ አይሆንም’ የሚለውን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ነው።
ዕድሌ ነው እንጅ ከሰው ያሳነሰኝ
ብርቱካን ሲታደል ሎሚ የደረሰኝ -- እያለ ከእሱ ቁጥጥርና ፈቃድ ውጭ የሆነ ኃይል ሕይወቱ ላይ እንደሚወስን ይመሰክራል። ‘ይታደሉታል እንጅ አይታገሉትም’ ብሎ አጉል መፈራገጥ ትርፉ መላላጥ እንደሆነ ይናገራል። ‘የአርባ ቀን ዕድሌ ነው’ የሚለው አገላለጽም ቢሆን በሀገራችን የተለመደ መሆኑ እርግጥ ነው። ከእነዚህ የ’ተወስኗል’ አስተሳሰቦች በተቃራኒ የምናገኛቸው አሳቢዎች በአንጻሩ ጥቂት የሚባሉ ናቸው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ለደህነታችን ዋነኛው መንስኤ ይህ አስተሳሰባችን እንደሆነና ሊቀየርም እንደሚገባው ‘ኢትዮጵያዊነት ከየት ወዴት?’ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ በስፋት ያብራራሉ። ይስማዕከ ወርቁ ደግሞ በአንድ ግጥሙ ላይ ጉዳዩን በጨረፍታ ነክቶት ያልፋል።
የተኛ በቆሎ ጎርፍ የደፈጠጠው
ተኝቶም ያፈራል ትል እያላመጠው
ድንጋዩን ሳይጫን አፈሩን ሳይለብሰው
መፈርጠጡስ ይቅር መዳህ ያቅተዋል ሰው?
ሰው አፈር እስካልለበሰ፡ ክንዱን እስካልተንተራሰ ድረስ ሕይወቱን በትግሉ የመለወጥ ኃላፊነት እጁ ላይ እንደሆነና ይህን ለማድረግም ነጻ ፈቃድ እንዳለው በተዘዋዋሪም ቢሆን ይጠቁማል።
የነጻ ፈቃድ ጉዳይ እንግዲህ ማንነታችንን ስናሰላስል አስቀድመው ከሚመጡልን ግዙፍ ጥያቄዎች አንዱ ሲሆን፤ ከዚህ ግዝፈት በታች የሆኑ ሌሎች ንዑስ ጥያቄዎች ደግሞ አሉ። (ንዑስ የተባሉት ከዕጣ-ፋንታ ጥያቄ ግዝፈት አንፃር ሲታዩ እንጅ ራሳቸውን አስችለን ነጥለን ስንመለከታቸው ግን በየራሳቸው እጅግ ግዙፍና ውስብስብ ናቸው) ከእነዚህ ‘ንዑስ’ ጥያቄዎች አንፃር የነጻ ፈቃድ መኖር አለመኖር ላይ መከራከር ቅብጠት ነው። ለጊዜው ዕጣ-ፋንታችን ተወስኗል የሚለውን ጥለን፤ ነጻ ፈቃድ አለን የሚለውን አንጠልጥለን ብንቀጥል እንኳ አሁን ‘እኔ’ የምንለው ማንነታችን በእርግጥም በነጻ ፈቃዳችን የመረጥነው እውነተኛው ‘እኔነት’ ነው ወይስ በሌሎች ሰዎችና በማኅበረሰባችን ተጽዕኖ የተፈጠረ ሀሰተኛ ማንነት ነው? የሚለው ከእያንዳንዳችን ፊት የቆመ ጥያቄ ነው። መነሻው የትም ይሁን ሕይወት መንገድ ነው። ከእናታችን ማህፀን ከወጣንባት ቅፅበት ጀምሮ (ምናልባት ከዚያም በፊት ጀምሮ) በዚህ መንገድ ላይ ተገኝተናል። መንገዱ በአሳባሪዎች የተሞላ እንደመሆኑ መጠን (በመረጥነው) አሳባሪ ስንጓዝ፣ አረማመዳችን ራሳችንን ይመስላል ወይ? መስለን የምንታየውና በትክክልም የሆንነው ማንነታችን አንድ አይነት ናቸው ወይስ እንደ ልብሶቻችን የክት እና የአዘቦት ‘ማንነት’ አለን? ፈጣሪ (ወይም ተፈጥሮ) ዕጣ-ፋንታችንን ወስኗል ወይም አልወሰነም ከማለታችን በፊት፣ የእኛ ዕጣ-ፋንታና ነጻ ፈቃድ ማኅበረሰቡ በሰራው ቅርጽ (ሞልድ) ውስጥ ገብቶ አልተጨፈለቀም ወይ? ከላይ ከተብራራው የነጻ ፈቃድ ጉዳይ ይልቅ ይህኛው ጥያቄ ለሰው ልጅ የበለጠ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ይመስላል። ወደ ሰማይ ከማንጋጠጣችን በፊት መጀመሪያ የጎንዮሹ ምን ይመስላል የሚለውን መመርመር አስፈላጊ ነው። ፈጣሪ ነጻ ፈቃድ ሰጥቶን ከሆነ እኛስ በተሰጠን ነጻ ፈቃድ ልክ በነፃ ምርጫችን እየኖርን ነው ወይ? ማኅበረሰባዊ ድጋፍ (Social approval) ለማግኘት ስንል የማንመርጠውን አልመረጥንም? የማንፈልገውን አልሆንም? የምንጠላውን የምንወደው አልመሰልንም? ራሳችንን እየኖርን ነው ወይስ የሆነ ሰውን እየተወንን? የሕይወታችን ደራሲዎች ነን ወይስ ማኅበረሰብ የጻፈልንን የማንነት መነባንብ አነብናቢዎች? ከዋነኛው የዕጣ-ፋንታ ክርክር በፊት ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚያስፈልገው ሞኝ ላለመሆን ነው።
ፈጣሪ በፈቀድነው መንገድ እንድንኖር ቢፈቅድልንም፣ ፈቃዳችንን ካልኖርነው፣ እኛ ላይ ያለው ነጻ ፈቃድ ‘መቃብር ላይ እንደተቀመጠ ጣፋጭ ምግብ’ መሆኑ እርግጥ ነው። መኖሩም አለመኖሩም ትርጉም አይሰጥም። ወደ ውሃው ወይም ወደ እሳቱ እጃችንን የመስደድ ምርጫ ቢሰጠንም እንኳ እጃችንን የምንሰደው ወደፈለግነው ሳይሆን ማህበረሰብ (ወይ ሰዎች) እንድንሰድበት ወደሚፈልጉት ከሆነ፣ የተሰጠንን ነፃ ፈቃድ አክስረናል። በዚህም የተነሳ ሕይወትን አክስረናል፤ አርክሰናልም። ይህ እንግዲህ እንደ አለመታደል ሆኖ የአብዛኞቻችን የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘዬ ነው። ከእውነተኛው ማንነታችን ጋር ተካክደን ለወል ፍላጎት እጅ ሰጥተናል። የግል እውነታችንን ለመንጋው ፍላጎት ባርያ አድርገናታል። ለጥፊ የዘረጋነውን እጅ (በይሉኝታ ወይም በማስመሰል የተነሳ) ሃሳባችንን ቀይረን አጨብጭበንበታል። ሰዎች ሲወዱት አይተን፡ የማንፈልገውን ተምረናል። የሚያስመልሰንን በልተናል። ጥሩ ሰው መሆናችንን ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡን ‘የጥሩ ሰውነት መስፈርት’ ሸምድደን ተውነናል። ኤርቪንግ ጎፍማን የተባለ የማኅበረሰብ አጥኚ እ.ኤ.አ በ1959 the presentation of self in everyday life በሚል ርዕስ ባሳተመው ጥናቱ፤ የእያንዳንዳችን የየዕለት ግንኙነት (daily interaction) ትወና መሆኑን ያስረግጣል። ግላዊ ማንነታችንን ትተን ማኅበረሰቡ እንድንሆን የሚጠብቅብንን ማንነት ስናሳድድና እሱኑ ስንተውን ከእውነተኛው እኛነታችን ጋር እንተላለፋለን። አስቀድሞ ከተሰራው ቅርጽ ጋር እንድንገጥም ሲባል ራሳችንን በራሳችን ከርክመን ከርክመን ሌላ ሆነን እናርፈዋለን።
ለመመሳሰል ስንል ልዩነታችንን በህዝብ ቀለም እንደልዛለን። ባዶ እጁን የቆመ ማኅበረሰብ መሐል ስለተገኘን ብቻ አንዳች ነገር ይዘን መወለዳችን ኃጢአት መስሎ ይታየንና፣ የያዝነውን ደፍተን ከባዶው መሐል ባዷችንን ገብተን እኩል እንሆናለን። ከዚያ በኋላ የሚኖረን እድል (ያውም ከነቃን) “እንዲህ ነበርኩ እንዴ?” ብለን መጠየቅ ነው። ፈጣሪም ገና ሲያየን በሚላን ኩንዴራ አገላለጽ፤ “እሱ ነው፤ ግን እሱን አይመስልም” ብሎን ያልፋል። ሕይወታችን ይህ ከሆነ ነጻ ፈቃድ ኖረ አልኖረ ፋይዳው ምንድነው?

 

 

Read 281 times