Saturday, 08 March 2025 00:00

3ኛው የአፍሪካን ሮቦቲክስ ሻምፒየንሺፕ ውድድር ከሐሙስ ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አሸናፊዎች በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለማቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ


3ኛው ዙር የአፍሪካን ሮቦቲክስ ሻምፒየንሺፕ ውድድር ከመጋቢት 4 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድ ኢትዮ ሮቦቲክስ አስታወቀ፡፡ ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር የመጀመሪያ ደረጃ፤ የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚወዳደሩ የተገለጸ ሲሆን፤ውድድሩ በዲዛይኒንግ፤ በኢንጅነሪንግና በአውቶነመስ ኮዲንግ ላይ እንደሚያተኩር ታውቋል፡፡
በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ ተማሪዎች የዋንጫ ሽልማቶችን የሚያገኙ ሲሆን፤ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተፈረመ ሰርተፊኬትም ይበረከትላቸዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ውድድር በአዲስ አበባ የሚኖሩ አፍሪካውያንም የሚካፈሉ ሲሆን፤ ለፍጻሜ የሚበቁ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለማቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ የኢትዮ ሮቦቲክስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይክረም መኮንን ገልጸዋል።
ላለፉት 15 ዓመታት የነገዎቹን ኢንጂነሮችና ፕሮግራመሮች የመፍጠር ራዕይ ሰንቆ ሲሰራ የቆየው ማዕከሉ፤ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በዓለማቀፍ የሮቦቲክስ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉና ዓለማቀፍ ልምድና ተሞክሮ እንዲቀምሱ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት በቻይና ሻንጋይ በተካሄደው ኢንጆይ ኤአይ ዓለማቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ 21 ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ሀገራቸውን ወክለው የተወዳደሩ ሲሆን፤ በውድድሩ ከተሳተፉ 27 የዓለም አገራት 3ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ፣ ዓምና በአሜሪካ በተካሄደ የዓለም ሮቦቲክስ ሻምፒዮን የተሳተፉ ታዳጊዎች አስደማሚ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር “ታዳጊዎቹ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት ጀምረዋል” ሲል ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዕውቅናና አድናቆት በመስጠት ብቻ ግን አልተወሰነም፡፡ ኢትዮ ሮቦቲክስ የጀመረውን ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ የማሰልጠንና የማብቃት ሥራን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሙሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮ ሮቦቲክስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰናይክረም መኮንን እንደሚሉት፤ ማዕከላቸው ታዳጊዎችን ከማሰልጠንና በዓለማቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ ዕድሎችን ከማመቻቸት የሚዘልቅ ራዕይን ሰንቋል፡፡ እንደ ቻይናና ሌሎች ያደጉ አገራት ሮቦቲክስ በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ለዚያም በትጋት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

 

Read 241 times