ከማህበረሰቡ በአስተሳሰብም ሆነ በአኗኗራቸው ወጣ ያሉ ሰዎች ይመቹኛል፡፡ እነዛ…ብቻቸውን በሀሳብ ጭልጥ ብለው የሚያሰላስሉት፣ በመንገድ ላይ ከሰዎች ራቅ ብለው ወክ የሚያደርጉት፣ ድምፅ ማዳመጫቸውን ጆሮዎቻቸው ላይ ሰክተው ለብቻቸው - የብቻቸውን ድምፅ የሚያዳምጡት፣ በሀይማኖት ስፍራዎች ተገኝተው ብቻቸውን ከሰው አይን ተለይተው የሚፀልዩት፣ በትምህር ቤት ውስጥ የጓደኛ ጥማታቸውን ገድለው የመፅሐፍ ገፆች ውስጥ ዘመናቸውን የሚተመትሙት፣ መታየት የማይፈልጉ፣ በየመንገዱ ሰላምታ የሰለቻቸው፣ ስልክ ሲደወልላቸው የሚያንገሸግሻቸው፣ ብዙ የሚያዳምጡና ምንም የማይናገሩ….ብዙ ያነበቡና ያነበቡትን የማያወሩ፣ እውነት ምን ያህል ከምድር የራቀች እንደሆነች አምነው ብቻቸውን መሆን የመረጡ…ፍፁም የሆኑ ራስ ወዳዶች፡፡
አዎ ገና ከርቀት ሳያቸው አውቃቸዋለሁ…በጣም ይመቹኛል፡፡
እነዚህ ሰዎች ይህ ፈጣን አለም በላያቸው ላይ እየተተራመሰባቸው፣ ብቻቸውን ቁጭ ብለው፣ ፀጥ ያሉ እና የሚያስቡት አይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ድምፅ በላይ የሚያደምጡት የላቸውም፡፡ ከገቡበትም ጠመዝማዛ የሀሳብ መንገድ ሲመለሱም፣ ማንም ሊጠይቀው የማይደፍረውን ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ ጥያቄዎቻቸው አዲስና ሰው ሰው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች አርቲስቶች ናቸው….ከካንቫስ ውጭ የሚያስቡና በአየር ላይ ማስመር የሚችሉ ሰዓሊዎች፣ በግል እውቀት ከፍታቸው ላይ የግል እምነታቸው አማራጭ ህልውናን እንደሚሰጣቸው ያመኑ ህልመኞች፣ አለም ማን እንደሆኑ እንዲነግራቸው እድል የማይሰጡ ሀሳቢያን…እነዚህ እና ብዙ ህይወቶች ናቸው፡፡
ነፍሳቸው በጀማው ድምፅ አይንቀጠቀጥም፤ ዝምታቸው ከድምፅ በላይ ነው፤ ነገር ግን ለራሳቸውም ቢሆን አይሰማም፣ በውስጠ ልባቸው ለማንም የማይነግሩትን ቢናገሩትም ማንም የማይረዳቸውን ታሪክ ተሸክመዋል…የሚያደምጣቸው የፈጠራቸው ብቻ ነው፡፡ ያ ህይወት ይናፍቀኛል፡፡
……………..
አንዳንዴ ያበድኩ ይመስለኛል፡፡ ሰው የመሆን ስሜት የማይሰማኝ ብዙ ቀናቶች አሉ፡፡ ሰዎች በአዕምሮ ስለመግባባት ያወራሉ፡፡ ስለማይታይ እና በሰዎች መካከል ስላለ ስውር የመሳሳብ ሀይል እንዳለ አድርገው አምነው ይናገሩታል፡፡ እኔ ግን የሚሉት ነገር የማይገባኝ ሰዓት አለ፡፡ በህይወት ውስጥ ስመላለስ በህይወት ያለው ሆኜ ሳይሆን የሚሰማኝ፤ ከርቀት ሆኜ በትካዜ የምመለከተው ቲያትር ይመስለኛል… በአይን ቅርበት የሚታይና በስሜት ውስጥ የማይሰርፅ ቲያትር፡፡
አንዳንዴ እያንዳንዱን የህይወት ውሳኔዎቼንና የአመለካከት ቅርፄን ገርቤ ለማሰላሰል እሞክራለሁ…ምናልባት የሆነ ቦታ ከሳትኩኝ ብዬ…ምናልባት እነሱ እንደሚሉት አይኖቼና ጆሮዎቼ አስተውኝ ከሆነ እነሱን ክጄ ሌላ ፍጥረት ፍለጋ ራሴው ህሊና ውስጥ ስማስን እገኛለሁ፡፡ መላ እፈልጋለሁ….ያለ ምንም ስሜት መሳቅ የምችልበትን መላ፣ ሳይደክመኝ ሳላዝን የማለቅስበትን ዘዴ፣ እያንዳንዱን የህይወቴን ቅፅበቶች ያለምንም ፍልስፍናዊም ሆነ ሀይማኖታዊ ጥያቄ የምኖርበት ጥበብ…..
እንዴት አድርጌ ነው ጤነኛ መሆን የሚቻለኝ፣ ከመጀመሪያውም ጤነኝነት ምን እንደሆነ ማወቅ ሳልችል? ምናልባት ግን ሰው መሆን ማለት ሙሉ መሆን ማለት ወይንም ፍፁም የሆነውን እውነት ማግኘት ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ሰው መሆን ማለት መፈለግ ብቻ ሊሆን ይችላል…መማር፣ በራስ ሀሳብ ውስጥ ተጠፍቶም ቢሆን የሆነ ነገር መፈለግ….ማግኘት አይደለም ….መፈለግ ….መፈለግ ….መፈለግ….
………………
አንዳንዴ ሁሉንም ነገር መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ሁሉንም ነገር፡፡ ሰዎችን መተው…የግል ሀሳብን መተው….ምንም አይነት ማብራሪያ አለመፈለግ…ምንም አይነት ሚስጥር አለመፍታት….ምንም አይነት አምላክ አለማምለክ….ማንም አይነት ተስፋ ከሰው አለመስማት…ምንም ነገር አለመፈለግ….ሰዎች እንዴት እያሰብክ እንደሆነ እንዳያውቁ ማድረግ…ማንም እንዲረዳሽ አለመሻት…
አንዳንዴ ህይወትን አጠገቤ ከሚከናወነው ትርምስ ውጭ አድርጌ ማሰብና መተርጎም እፈልጋለሁ፡፡ የማንም ሰው አፍ ላይ ያልተተረጎመችውን ህይወት እናፍቃታለሁ፡፡ ማንም ያልደረሰባትን፡፡ ማንም ያላገኛትን፡፡ ተደብቄ ብኖራት እላለሁ፡፡ ማንም ሳያየኝ፡፡ ማንም ምን ሆንክ ሳይለኝ፡፡
እኔ እና የፈጠረኝ ብቻ የምናውቀው ህይወት…የምናውቀው እውነት…የገባን ፍቅር ጋር ተደብቄ ማፍቀር ነው የምፈልገው፡፡
አንዳንዴ…..
………………
ልብ በጥልቀት ተሰርስሮ ሲደማ ሰዎች አያለቅሱም፡፡ ዝም ነው የሚሉት፡፡ የሚያስረዱት ነገር የላቸውም፣ ማንም እንዲረዳቸውና እንዲሰማቸው ተስፋ አያደርጉም…ዝም ብለው አንድ ቦታ ላይ ተቀምጠው በሀሳብ ይጠፋሉ፤ በማይሰሙት ንግግር ራሳቸውን ይነቀንቃሉ፤ እውነትን ከመናገር ይቀላል ብለው የውሸታቸውን ፈገግ ይላሉ፡፡
ምክያቱም ጥልቅ የሆነ ሀዘን አይጮህም….ነገር ግን ቀስ እያለ የህሊና ጉድጓድ ውስጥ ይሰምጣል፡፡ የህመሙ ጥልቀት ከዚህ ቀደም ቃላት የሰነበቱበት፣ አሁን ላይ ግን የሌሉበት ባዶ የሀሳብ መንደር ውስጥ ያሰድዳል…በንግግር መሀል ባለ ፀጥታ ውስጥ (ታማኝነት የሚኖርበት ሚስጥራዊ የድምፅ ሞገድ) ህመማችን የልባችንን በር ወዝውዞት ያልፋል፡፡
ያ ፀጥታ በውስጡ ሰላም የለውም፤ ነገር ግን በታላቅ የነፍስ ድካም ምክንያት የተሸከምነውና ልናወራው የማንፈቅደው የውስጥ ሸክም ነው ያለው፡፡ የዚህ ህመም ተሸካሚዎች በህይወት ሳሉ ስሜታቸውን የሚነግሩላቸውን ቃላት በመፈለግ አይደክሙም…ምክንያቱም አንዳንድ ህመም ስም የለውምና ነው … ያለው ልክ እንደ ገደል ማሚቱ የሚያስተጋባ የውስጥ ድምፅ ነው፤ ማንም እንዲረዳቸውም አይፈልጉም…ምክንያቱም ከብዙ የህይወት ግርፊያ በኋላ አንዳንድ ጦርነቶች በግል ጥረት ብቻ ድል እንደሚነሱ ስለደረሱበት ነው፡፡
ስለዚህ ይሸከሙታል…ሀዘናቸውን ተሸክመውት ለብቻቸው በታላቅ የፀጥታ መንኮራኩር ይነጉዳሉ…ከሸክማቸው ጋር ተቧድነው እንዴት እንደሚኖሩ መላውን ብቻቸውን ሆነው ይዘይዱታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከታመሙበት ለመፈወስ ሳይሆን ምን ያህል ሸክማቸውን እንደያዙት በህይወት መድረክ ላይ መቆየት እንደሚችሉ ራሳቸውን በራሳቸው ለመረዳት ሲፈልጉ ብቻ ነው፡፡
ምናልባትም አንድ ቀን ሸክሙ ሙሉውን ባይረግፍም ይቀልላቸው ይሆናል….ፀጥታውም ድምፁን ያለሰልስ ይሆናል…ምናልባት አንድ ቀን በህይወት ቆይቶ ህይወትን ብቻ መተንፈስ ምን አይነት እንደሆነ ሚስጥሩን ይደርሱበት ይሆናል፡፡
……………
ከሰዎች ጋር ስሆን ባዶ እሆናለሁ…ኦና፡፡ ደግሜ ሙሉ ለመሆን ከነሱ መራቅ አለብኝ፡፡ ብቻውን የቀረ ቅርፊት የሆንኩ እስኪመስለኝ ድረስ በህይወቴ ውስጥ ስሰጥ ቆይቻለሁ፡፡ የሌሎች ሰዎችን ችግሮች በተደጋጋሚ ከመስማቴ የተነሳ የራሴ የምለው…የግሌ ሰላም በአዕምሮዬ ውስጥ የቱ ጋ እንዳለ እስክስተው ድረስ እወዛገባለሁ፡፡
ዝምታ በውስጡ መረጋጋትን ብቻ አይሰጥም…ትግልም አለበት፡፡ ያ ዝምታ ብዛት ያለው ራስን የማግኛ ክፍተት ይሰጣል፡፡ ሆኖም እኔ ዝምታዬን ለሰው ልጆች የግል ታሪክ መፈንጫ አድርጌዋለሁ፡፡ እስካሁን የሰማሁትን መልሼ ላፅዳው ብል የቀረኝ ዘመን የሚበቃኝ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ሰምቻለው…የብዙ ሰው ሚስጥራት በጭንቅላቴ ውስጥ ተሰቅስቆ ተቀምጧል፡፡ ምን እንደማደርገው አላውቅም፡፡ በግል ሀሳቤ ውስጥ ቆይቼ የራሴን ሚስጥር መበተን ሲገባኝ በተለያዩ ሰዎች ትረካዎች ውስጥ ራሴን በታትኜው ተቀምጫለሁ፡፡
ሰዎች የሚሉኝን ሳደርግላቸው ከሚደሰቱት ደስታ ጋር ሱስ ይዞኝ….ሙሉ ጊዜዬን በመስጠቴ የአንድን ሰው ጭንቀት ማትረፍ ውስጥ ያለውን እፎይታ በመፍጠሬ… እንባቸውን በዝምታዬ በመጥረጌ…ለሰው በመድረሴ ሁሉም ነገር የሚስተካከል ይመስለኝ ነበር፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ ወደየትም የማይቀየር ፍጥረት መሆኑን ከተረዳሁ በኋላ፣ በፍጥነት ብቻዬን መሆን እንዳለብኝ ገባኝ…መሸሽ፡፡ ያን ጊዜ ትንሽ መተንፈስ እችላለሁ…ማሰብ፡፡ ያን ጊዜ እሞላለሁ፡፡ የምሰጠውም ነገር ይበዛልኛል፡፡
ስለዚህ ምናልባት ለተወሰኑ ጊዜያት ብሰወር ልትረዱት የሚገባው አንድ ነገር ነው….የምጠፋው የገነባሁትን ለማውደም ሳይሆን ለማደስ ነው፡፡ በዝምታ ማድመጥም ቃላትን ከመደርደር በላይ ውስጠ ሚስጥር እንዳለሁ በዝምታ አድጌ ለማሳየትም ነው፡፡
የሰው ልጅ ግን ይቀየራል?….እሱን እንጃ፡፡
………………
መመኘት ግዴታህ ከሆነ ምን ትመኛለህ ብላችሁ ብትጠይቁኝ ይህንን እላለሁ….
ቀላል ህይወት ነው መኖር የምፈልገው፡፡ በህፃናት ፈገግታ ከእንቅልፌ መንቃት፣ ዝናም ሲዘንብ ከመስኮቴ ጥጋት ስር ተቀምጬ የጠብታዎቹን ዜማ ማዳመጥ፣ የማልፈተንበትን መፅሀፍ ይዤ ከተራራ አናት ላይ በንፋስ ውዝዋዜ በቃላት መስከር፣ ማንም እንዲያደንቀኝ ሳይሆን ራሴን ደጋግሜ እንዳይ የሚያደርገኝን ስዕል መሳል እፈልጋለሁ፣ ጨረቃዋ ከነ ጃኖዋ ስትመጣ እሷን እያየሁ መተኛት እፈልጋለሁ፣ ስነቃም የምቅበዘበዝበት ጉዳይ ሳይኖረኝ ተረጋግቼ ነው ከሚጠብቀኝ ቀን ጋር መላመድ የምፈልገው፣ በሰዓታት እና በገንዘብ ቁጥጥር ስር መግባት አልፈልግም፣ ሙሉ እና ፍፁም ነፃ ነው መሆን የምፈልገው….
ለረዥም ጊዜ ከህይወት ውስጥ የሆነ ልዩ ትርጉም ሳስስ ነው የከረምኩት…ሆኖም አሁን ላይ ምንም አይነት የሚፈበረክ ትርጉምም ሆነ ሚስጥር እንደሌለ ደርሼበታለሁ፡፡
ቀሪው ነገር የሚኖር ህይወት ብቻ ነው…መኖር ብቻ፡፡
ምንም አይነት የሚፈፀም ተስፋ የለም፣ ምንም አይነት የተንጠለጠለ አላማ የለም…ያለው በሰፊ ምድር ላይ የሚተነፈስ አየር ብቻ ነው፡፡ እኔም ከዚህ በላይ ለፍለጋ ነፍሴን ወደ የትም የምሰድበት ጉልበቱ የለኝም፡፡
ቀላል ህይወት ነው የምፈልገው…..
……………..
በስተመጨረሻ….
በስተመጨረሻ አንተ እና አንቺ ብቻችሁን በምድር ላይ እንዳላችሁ መረዳት ትጀምራላችሁ፡፡ ሁላችንም ብቻችንን ነን፡፡ ማንም አንተን ሊረዳህ የሚመጣ ሰው የለም፤ ማንም ስላንተ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብልህ የለም፣ ማንም አንተን ሀብታም ሊያደርግ ከእንቅልፉ የሚነቃልህ የለም፣ ማንም አንተ እንዲረዱልህ ብለህ የምትናገረውን ንግግር የሚሰማልህ የለም፣ ማንም ያንተን ፍቅር ሊጠጣ ነፍሱን አፅድቶ የሚከሰትልህ አታገኝም፤ ማንም እንባሽን ለማበስ ፍላጎት የለውም….ብቻሽን ነሽ፤ ብቻህን ነህ፡፡
ከራስህ ውጭ አንተን ቀና የሚያደርግህ ማንም የለም፣ ሁሌ በፈለግሻቸው ቁጥር አጠገብሽ የሚደርሱልሽ ሰዎች የሉሽም፡፡ ተሸክመነው ያለነውን ሸክም መሸከም የሚችል ምድር ላይ ብናስስ አናገኝም፡፡ ሁሌም ቢሆን የነበርከው አንተ ብቻ ነህ፡፡ ብቻህን፡፡ ይህን ሁሉ ነገር ማድረግ የምትችለው….አንተ ብቻ፡፡
ይህ መሆኑ ምናልባት እርግማን ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ልዩ የሆነ የነፃነት አይነትም ሊሆን ይችላል፡፡
ምክንያቱም ብቻችሁን ናችሁና ….ከዚህ በኋላ ውሳኔዎቻችሁ የናንተ ብቻ ነው ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ ያኔ እናንተ ናችሁ በቃ ማለት የምትችሉት፡፡ ያኔ አንተ ብቻ ነህ የገዛ ታሪክህን አፅድተህ እንዳዲስ ድርሰቱን መስራት የምትችለው፡፡ ያኔ ባንቺ ላይ ማንም ስልጣን አይኖረውም፡፡ ያኔ የበፊት ትዝታችሁም ሆነ፣ ህመማችሁ፣ ስቃያችሁ፣ የውስጥ ጩኸታችሁ ከናንተ በታች ይሆናሉ፡፡ ብዙውን ዘመናችሁን የማንነታችሁ ፍፅምና ላይ ስትሰሩ ስለነበራችሁ ውሳኔዎቻችሁ ከውስጥ ጥያቄያችሁ ጋር እኩል ይሆናል፡፡
በዛም እስከዛሬ ድረስ ከህይወት አዘቅት ውስጥ ሆናችሁ ስትማሩት የነበረው ሚስጥር፣ ጀግና መች እንደምትሆኑ የሚነግራችሁን ሰበካ ሳይሆን እስካሁን ድረስ ዋናው የህይወታችሁ ጀግና እናንተ ብቻ እንደሆናችሁ ደጋግሞ የሚነግራችሁን የውስጣችሁን አምላክ ድምፅ ብቻ ነው፡፡
…………………
ከብዙ የትካዜ ቀናት መካከል በአንዱ ቀን ቁጭ ብዬ በተከዝኩበት እነዚህ ቃላት ራሳቸውን ፈጥረው በእኔ ውስጥ እንዲህ እንዲህ እየሆኑ ፈሰሱ…..
መልካም ራስን የመፈለግ ዘመን….