መጻሕፍት በዘመናት ሁሉ የሰውን ልጅ ህይወት ለመለወጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ አብርሃም ሊንከን፣ አይዛክ ኒውተንና ሄለን ኬለርን ብቻ እንኳን ብንወስድና በህይወታቸው መፅሐፍ ያስከተለውን ለውጥት ብንመረምር ብዙ እንረዳለን፡፡
ቤንጂሚን ፍራንክሊን በ17 ዓመቱ በፈላዴልፌያ ዋና ዋና መንገዶች የሚንከላወስ ቤሳቤስቲን የሌለው ምስኪን ወጣት ነበር፡፡ ወደፊት ሚስቱ የምትሆነውን ዴቦራን ያገኘው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡ በመጨረሻ ሳንቲሙ የገዛውን ዳቦ እየበላ በደጇ ያልፍ ነበር፡፡ የኮሌጅ ትምህርቱን ከመከታተል ይልቅ የምርጥ ምርጥ ደራሲያን ስራ ውጤት የሆኑ መፃህፍትን ማንበብና አእምሮውን ማበልፀግን መርጧል፡፡ ለቤንጃሚን ፍራንክሊን መፃሕፍት የማይለዩት ባልንጀሮቹ ነበሩ፡፡ መፅሐፍ ተውሶ ሌሊት ሲያነብ አድሮ በነጋታው ይመልስ ነበር፡፡ መጻሕፍቱ እጅግ አመርቂና መሰረት የያዘ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ እውቀትን ያጎናፀፉት ሲሆን፤ በዚህም በዘመኑ የአሜሪካ ዲፕሎማት ሆኖ ነበር፡፡ ታሪክ ፀሀፊው ጊበን አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የእኔን የጠዋት ንባብና ማንም የማይሽረውን የማንበብ ፍቅር ህንድ ባላት ሀብት ሁሉ እንኳን የምለውጠው አይደለም፡፡” ቻርለስ ዲከንስ ደግሞ “ለጥሩ መፃህፍት ያለኝ ፍቅር የተለያዩ ነገሮች እንዳያማልሉኝ እንደመከላከያ የቆመልኝ ጋሻ ጃግሬዬ ነው፡፡” ሲል በይፋ ገልጽዋል፡፡
ጣሊያናዊው ሲሴሮ ያለውን ንብረት ሁሉ ሸጦ መፃሕፍት ለመግዛትና ከመፃህፍት መካከል ለመኖርና ለመሞት የፈቀደ ሰው ነበር፡፡ ሲሴሮ የመጻሕፍትን ባህሪ ተንተርሶ እንደገለፀው፤ “ከመኖሪያ ቤቴ በተጨማሪ መጻሕፍት ቤት ባቋቁም ለቤቱ ነብስ ሰጠሁት እንደ ማለት ነው” ብሏል፡፡
አንድ ፀሀፊ ደግሞ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ማንም እኔን በቤተ-መንግሥት ውስጥ የሚኖር በአትክልትና በጽጌያት የተከበበ፣ በመልካም ግብር ድግስ፣ ጠጅ የተጣለበት፣ ሙክትና ፍሪዳው የሚታረድበት፣ በዘበኞች የተጠበቀ የታላቆች ታላቅ የሆነ፣ እስከዛሬ በዓለም ያልታየ ንጉስ ሊያረገኝ የሚችል ሰው ቢኖርና መፅሐፍ ግን አታነብም የሚለኝ ከሆነ፣ ንጉስነቱ በአፍንጫዬ ይውጣ እለዋለሁ፤ ከቶውንም የመጻሕፍት ፍቅር የሌለው ንጉስ ከምሆን፣ ጉሮኖ ውስጥ ደሃ ሆኜ ከብዙ መጻሕፍት ጋር ብቀመጥ እመርጣለሁ፡፡”
አይዛክ ኒውተን በወጣትነት እድሜው በባቡር ጣቢያ አካባቢ ጋዜጣ አዟሪ ነጋዴ ነበር፡፡ ባቡር እስከሚመጣ ድረስ በአካባቢው ከሚገኘው ቤተ መጻሕፍት አይጠፋም ነበር፡፡ ባቡሩ ሲመጣ ግን ጋዜጣውን ለመሸጥ ወደ ባቡር ጣቢያው ይመለስ ነበር፡፡
ሄለን ኬለር ዓይነ ስውር ነበረች፡፡ ሆኖም በነበራት መንፈሰ - ጠንካራነት በርትታ በመማርና ብዙ መፃሕፍትን በማንበብ የአሜሪካ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባል ለመሆን የቻለች አስደናቂ ሴት ነበረች፡፡
በሀገራችን ያለው የንባብ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በበለፀገው ዓለም እያንዳንዱ ቤተሰብ ሁለት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ክፍሎች አሉት፡፡ አንደኛው ለአካል አስፈላጊ ምግቦችን መመገቢያ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የአእምሮ ምግብ የሚገኝበት የንባብ ክፍል ነው፡፡ በነዚህ ሀገራት የአብዛኛው ቤተሰብ የንባብ ክፍል ስፋት ከመመገቢያ ክፍል ስፋት ይበልጣል፡፡ እርግጥ ነው ጣእም ከሰው ሰው ይለያል፡፡ እነዚህ አገሮች ለመፃሕፍት የሚያወጡት ወጪ ከግሮሰሪ ወጪያቸው የበለጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በነዚህ አገራት የአንባቢው ቁጥር ባለፉት 50 ዓመታት ከፍተኛ እድገት ሲያሳይ፣ በያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ መቶ መጻሕፍት ይገኛል፡፡ በኛስ አገር? የገጠሩን ህዝብ ለጊዜው እንተወውና፣ ዋና ዋና ከተሞችን እንኳን ብንወስድ፣ ልጆቻችን በየቤታችን መጻሕፍት ያገኛሉ?
በበለፀጉት አገራት በየ100 ሜትሮቹ ቤተ መጻሕፍት ወይም የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ይገኛሉ፡፡ በኛም ሀገር ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ኪዮስኮች አሉ - የተለያዩ ቁሳቁሶች የሚቸረቸርባቸው፡፡ በሀገሪቱ ባጠቃላይ የአሮጌ መጻሕፍት መሸጫ መደብሮች እንኳን ጨምረን አንድ መቶ እንኳን የሚሞሉ መጻሕፍት መደብሮች የሉም፡፡ በርግጥ ንግዱ በሀገራችን አትራፊ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ለዚህም ይሆናል ሜጋ ከኩራዝ የተረከበውን የመርካቶውንና ከአራዳ ገበያ ፊት ለፊት የሚገኙትን የመጻሕፍት መደብሮች ወደ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መቸርቸሪያነት የለወጠው፡፡ (ልብ በሉ! ጽሁፉ በ1992 ዓ.ም የተጻፈ ነው) አስተያየቴ የሚስቀይማቸው ቢኖሩ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ 10 እንኳን የሚሞሉ መጻሕፍት ሲተዋወቁ አይተናል? ወይስ ሰምተናል?
ባሉትም የመጻህፍት መደብሮች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስና አሮጌ መጻሕፍት ተደርድረው ቢውሉም፣ ሊጎበኙአቸው ወደ መደብሮቹ የሚሄዱት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሚፈልጉትን የመጻሕፍት ዓይነት በትክክል የሚያውቁትን ቁጥራቸውን ባልናገር ወይም ባልገምት ይሻላል፡፡ አሳፋሪ ነውና፡፡ ለመሆኑ ስንቶቻችን በዓመት 5 መጻሕፍት እንገዛለን? ቁጥሩን አበዛሁት እንዴ? (ይቅርታ ትልቅ ይቅርታ!!)
ተዳፈርክ ባልባል በአብዛኛው የሃበሻ ቤት ውስጥ መጻሕፍት ቢሰበሰቡም እንኳን ቤት ማሳመሪያ ተደርገው ነው የሚታዩት፡፡ ያሳዝናል! መጻሕፍት ሊያገለግሉን እንጂ ለትርኢት የሚቀመጡ አልነበሩም፡፡ እውነተኛ አንባቢዎች ወይም የሚፍጨረጨሩ የሚተጉ /ለማንበብ/ የሉም ማለቴ እንዳልሆነ ተረዱኝ፡፡ የአንባቢው ቁጥር በሚያሳዝን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማሳየትና ሁኔታውን ለመለወጥ ከያንዳንዳችን ብዙ እንደሚጠበቅ ለማሳየት ካለኝ ቅን ፍላጎት ነው፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰን አንድ ጊዜ፤ “የማያነቡ ሰዎች የሚያስቡት ነገር አይኖራቸውም፤ የሚናገሩትም እጅግ ጥቂት ነው፡፡” ብለው ነበር፡፡
በሀገራችን ብዙ ተማሪዎች “ትምህርት ጨርስኩ” የሚል አባባል ሊሰነዝሩ ይደመጣሉ፡፡ እኔ ይህን አባባል የምደግፍ አይደለሁም፡፡ የአንድ እንግሊዛዊ ምሩቅ ተማሪና መምህር ምልልስን እንመልከት፡፡ በዩኒቨርሲቲ የምርቃት በዓሉ ላይ በደስታ ተሞልቶ የመጣ አንድ ወጣት ተማሪ ለኮሌጁ ፕሬዚዳንት ትምህርቱን በድል ማጠናቀቁን ጮክ ብሎ ነገረው፡፡ ፕሬዚዳንቱም፤ “እኔ እንኳ ገና መጀመሬ ነው” ሲሉ መልስ ሰጡት፡፡ በሀገራችን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከአንድ ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ መጻሕፍት በዓይናቸው ላለማየት የማሉ ይመስላል፡፡ የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ለአባባሌም ይቅርታ አልጠይቅም፡፡
(አዲስ አድማስ፤ግንቦት 12 ቀን 1992 ዓ.ም)
Published in
ህብረተሰብ