Monday, 10 March 2025 10:03

መስታወቱ

Written by  ደራሲ፡- አንቶን ቼኾቭ
Rate this item
(2 votes)

አንድ እለት አመሻሽ ገደማ ከሚስቴ ጋር ቅድም አያቶቼ ይኖሩበት ወደነበረውና ለረጅም ዘመናት ተዘግቶ ወደ ቆየው አሮጌ ቤት ለጉብኝት ሄድን፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ እርጅናና የግድግዳው ውርዛት ያበቀላቸው እጽዋት ድምር የወለደው የሚያጥወለውል እምክ እምክ የሚል ጠረን ተቀበለን፡፡ ለዘመናት ቅንጣት ብርሀን አርፎበት በማያውቀው የጨለማ ወለል ላይ ያበራነው ሻማ ብርሀን ውጋጋን ሲያርፍበት፣ እልፍ የአይጥ መንጋ በድንጋጤ እየተርመሰመሰ ወደየስርቻው ተሸጎጠ፡፡ ድንገት ከፍተን የተውነውን በር ንፋስ በሀይል ወርውሮ ከጀርባችን ሲዘጋው የተፈጠረው መለስተኛ የአየር ሞገድ፣ በየጥጉ የተከመሩ እድሜ ጠገብ ወረቀቶችን እንደ ገለባ በመጠኑ አንቀሳቀሳቸው፡፡ የሻማው ብርሀንም በላያቸው የሰፈሩትን ጥንታዊ ጽሁፎችና የመካከለኛው ዘመን ስእል ንድፎች ፍንትው አድርጎ አሳየን፡፡ በግድግዳዎች ላይ ተሰቅለው የሚታዩት የቅድም አያቶቼ ስእሎች በእርጅናና በቆሻሻ ወይበው አረንጓዴ ሻጋታ ቀለም በስሱ ቢሸፍናቸውም፣ ኮስታራ ግንባራቸውንና ክብርና ሞገሳቸውን አልደበቀውም፡፡
እርምጃችንና ኮቴያችን ፍጹም ጸጥታ በሰፈነበት ቤት የእንጨት ወለል ላይ ሲያርፍ፣ የመድፍ ጩኸት ያህል ተጋኖ ይሰማል፡፡ ለክፍለ ዘመናት የቅድመ አያቶቼን ድምጽ ሲያስተጋባ የኖረው ቤተኛ ማሚቶ፣ አልፎ አልፎ ከጉሮሮዬ የሚያፈተልከውን ሳል እንደ ልማዱ ተቀብሎ ያስተጋባል፡፡
ከቤቱ ጣሪያ ቁልቁል በሰፊው ጭስ ማውጫ የሚወረወረው ነፋስ የሚያሰማው ሰቅጣጭ የፉጨት ድምጽ፣ እሳት ማንደጃው ውስጥ ተደብቆ በተስፋ መቁረጥ ከሚያነባ የተጨነቀ ሰው መቃተት የሚመነጭ ይመስላል፡፡ ከውጭ ጽልመት በዋጣቸው የመስኮት መስታወቶች ላይ የሚያርፈው የዝናብ ካፊያ ስልታዊ ምት ስቃይን ያውጃል፡፡
ድንገት ከውስጤ የመነጨ አንዳች ስሜት ፈንቅሎኝ፤ “ አይ ክቡራን አያት ቅድምአያቶቼ!! ዘርማንዘሮቼ!! “ ስል ተናገርኩ፡፡ ቀጠልኩናም፤ “የስነጽሁፍ ችሎታ ቢኖረኝ ስለ እያንዳንዳቸው የህይወት ገድሎች በተለይም ልክ እንደኛ ብርቱ በነበሩበት የወጣትነት- እድሜያቸው ያሳለፉትን ውብና ጣፋጭ የፍቅር ህይወት አንድ ሳላስቀር ጽፌ አሳትመው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያቺ እዛ ጥግ ላይ ፎቶዋ የተሰቀለው ሴት ቅድመ አያቴ ናት፡፡ እንደምታይው መልከ ጥፉ ብትሆንም እጅግ አስገራሚ ታሪክ አላት!! እዛ ማዶ ጥግ ላይ የተሰቀለው የመልክ መስታወት ይታይሻል?” በጥቁር የነሀስ ፍሬም ያጌጠና በሴት ቅድመ አያቴ ፎቶ አቅራቢያ ወደተሰቀለ ትልቅ የመልክ መስታወት በእጆቼ እያመላከትኩ ለሚስቴ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡
“ይህ መስታወት ለሴት ቅድመ አያቴ ህይወት መመሰቃቀል ዋነኛ ምክንያት የሆነና አንዳች ምትሀታዊ አዚም ያለበት ነው፡፡ በውድ ዋጋ ገዝታ እዚህ ካመጣችው እለት ጀምሮ እስከ እለተ ሞትዋ ድረስ አንድም ቀን ከአጠገቡ ተለይታ አታውቅም፡፡ በየዕለቱ ፊት ለፊቱ ተቀምጣ ለአፍታ አይኗን ሳትነቅል ስታፈጥበት ትውላለች፡፡ ሌላው ቀርቶ ምግብ ስትበላ እንኳን ማፍጠጧ አይስተጓጎልም፡፡ ይህ አልበቃ ብሏት ማታ ለመተኛት ወደ መኝታ ክፍሏ ስታመራ ይዛው ትገባለች፡፡ በመጨረሻም ከመሞትዋ በፊት አስቀድማ አብሯት እንዲቀበር ተናዛ የነበረ ቢሆንም፣ የመስታወቱ ትልቀነት ከሬሳ ሳጥኑ በመብለጡ ኑዛዜዋን መፈጸም ሳይቻል ቀርቷል፡፡”
“ሴትየዋ መኳኳል ይወዱ ነበር ማለት ነው?” ሚስቴ ጠየቀችኝ፡፡
“እሱስ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ግራ የሚያጋባው ነገር ሌላ መስታወት ለምን አልነበራትም? ይሄን መስታወት ብቻ በልዩ ሁኔታ እንድትወድ ያደረጋት ነገር ምንድነው የሚለው ጥያቄ ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የሆነ ያልደረስንበት ድብቅ ሚስጥራዊ ምክኒያት እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ ወይም በአፈ ታሪክ ሲነገር እንደምንሰማው መስታወቶች ላይ ይኖራሉ የሚባሉት እርኩሳን መናፍስት አደንዝዘዋትም ሊሆን ይችላል፡፤ በእርግጥ መስታወቱ ርካሽ የሚባል አይነት ቢሆንም የሆነ ርኩስ ምትሀታዊ ሀይል ሳይኖረው አይቀርም፡፡”
ይህን ብዬ ወደ መስታወቱ ቀረብኩና የሸፈነውን አቧራ ለአመል ያህል ጠረግ ጠረግ አድርጌ በውስጡ ተመለከትኩና ከትከት ብዬ ሳቅኩ፡፡ የአሮጌው ቤት ማሚቱ ሳቄን ተቀብሎ ከክፍል ክፍል አስተጋባው፡፡ መስታወቱ እንደ ሌሎቹ መስታወቶች ጠፍጣፋ አይነት ሳይሆን ክብ በሆነው ቅርጹ ላይ ልክ እንደ መነጽር መስታወት ከመሀሉ አበጥ ብሎ የተሰራና ምስልን የሚያጎላ ሌንስ ባህሪ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ጠጋ ብዬ መልኬን ስመለከት ፊቴን ልክ እንደተበታተነ ሁሉ አዘበራርቆ አሳየኝ፡፡ አፍንጫዬን በግራ ጉንጬ ቦታ፣ ጉንጮቼን ደግሞ በስተቀኝ በኩል አንድ ቦታ ላይ የተከመሩ አስመሰላቸው፡፡
“በእውነቱ ቅድመ አያቴ ከሰዎች ሁሉ ለየት ያለ ምርጫ ነበራት ማለት ነው!” ስል ተናገርኩ፡፡
ሚስቴ በማቅማማትና ብዙም ፍላጎት ሳይኖራት በዝግታ ቀረብ ብላ በመስታወቱ ውስጥ ተመለከተች፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ አንዳች እጅግ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ ገጽታዋ ምንጩ ባልታወቀ ድንጋጤና ሽብር ልውጥውጥ አለና፣ ፊትዋ ዱቄት የተነሰነሰበት ይመስል ነጭ ሆኖ፣ ጆሮ በሚሰነጥቅ ጩኸት እሪታዋን አቀለጠችው፡፡ በእጇ የያዘችው ሻማ ከጭብጧ አምልጦ ወለሉ ላይ ወደቀና ብርሀኑ ጠፋ፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ዋጠን፡፡ ይሄኔ በጭለማው ውስጥ አንዳች ከባድ ነገር ወለሉ ላይ ዱብ ብሎ ሲያርፍ ታወቀኝ፡፡ ሚስቴ ነበረች፡፡ ራስዋን ስታ ወድቃለች፡፡
ነፋሱ በአስፈሪ ዜማ ስልት እየነፈሰ ነው፡፡ አይጦች በወለሉ ላይ መርመስመስና በየጥጉ የተከመሩትን ወረቀቶች ማተራመስና ማንኮሻኮሽ ጀምረዋል፡፡ አንዱን መስኮት ከውጭ የሚሸፍነው የቆርቆሮ መዝጊያ ድንገት ምን እነደነካው ሳይታወቅ መሬት ላይ ወድቆ ከፍተኛ ድምጽ በማሰማቱ የማጅራቴ ጸጉሮች እስኪቆሙ ድረስ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡ በተከፈተው መስኮትም ጨረቃ እስከ ብርሀኗ ብቅ ብላ ታየች፡፡
የወደቀችው ሚስቴን እንደ ምንም ታግዬ በማንሳት ተሸከምኩና ከዚያ አሮጌ የቅድመ አያቶቼ መኖሪያ አወጣኋት፡፡ በዚያ ምሽትና በተከታዩ እለት ቀን ሙሉ ራስዋን እንደሳተች ቆይታ በመጨረሻ ምሽት ላይ ለመንቃት ቻለች፡፡
ብዙም ሳትቆይ “መስታወቱስ? መስታወቱን ስጠኝ!! መስታወቱ የት ነው ያለው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያለእረፍት መጠየቅ ጀመረች፡፡
ለአንድ ሙሉ ሳምንት ያህል እህል ውሃ በአፍዋ ማድረግ አሻፈረኝ ብላ ያለፋታ መስታወቱ እንዲመጣላት ብቻ አብዝታ መወትወትና መጨቅጨቋን ቀጠለች፡፡ ሁኔታዋ ባልተቋረጠ ለቅሶ ጸጉርዋን በመንጨት፣ አልጋ ላይ ያለ እረፍት በመገላበጥና በመቁነጥነጥ የታጀበ መሆኑ ምግብ ከመጥላቷ ጋር ተዳምሮ ሰውነቷ በጣም በመዳከሙ የጤንነቷ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በሀኪሟ ተነገረኝ፡፡ ይሄኔ ፍርሀቴን ዋጥ አድርጌ የመጣው ይምጣ በማለት ወደ ቅድመ አያቶቼ መኖሪያ ቤት ገባሁና፣ ያንን መአተኛ መስታወት አውጥቼ አመጣሁላት፡፡ መስታወቱን እንዳየችውም በደስታ ፈነጠዘች፡፡ ባለማመንና በፍቅር በእጆችዋ እየዳሰሰች ደጋግማ ሳመችውና፣ አይኖችዋን ተክላ ፍዝዝ ብላ ትመለከተው ጀመረች፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ አስር አመታት ተቆጠሩ፡፡ ሚስቴ አሁን ድረስ መስታወቱ ላይ ማፍጠጥዋን አላቆመችም፡፡ ለአፍታ እንኳን ከአጠገቡ መራቅ አትፈልግም፡፡
“እውነት ይህ ምስል እኔው ራሴው ነኝ?” ስትል አጉተመተመች፡፡ ከንግግሯ ጋር አብሮ ፊትዋ በታላቅ የደስታና የተድላ ብርሀን ተጥለቀለቀ፡፡ ቀጥላም፤
“አዎ!! ራሴው ነኝ፡፡ ከዚህ መስታወት በስተቀር ሁሉም ውሸት ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ ባሌን ጨምሮ ውሸታሞች ናቸው፡፡ ወይኔ!! ገና በአፍላነቴ እንዲህ ውብ መሆኔን አውቄ ቢሆን ኖሮ በጭራሽ ይህን ባሌን አላገባውም ነበር፡፡ እጣፈንታዬም ከእንደሱ አይነቱ ለእኔ ደረጃ ከማይመጥን ሰው ጋር መተሳሰር ሳይሆን ከፍተኛ ክብርና ማእረግ ያላቸው መልከመልካም መሳፍንት ጫማዬን ስመው እንዲያገቡኝ ማድረግ ይሆን ነበር!!” በማለት ተናገረች፡፤
አንድ እለት ከሚስቴ ኋላ ቆምኩና መስታወቱን እንደዋዛ በጨረፍታ አየት ባደርገው የማይታመን ምስጢር ተገለጠልኝ፡፡ በህይወቴ ዘመን ፍጹም አይቼው የማላውቀው አይነት መግነጢሳዊ ውበት የፈሰሰባት ሴት ተመለከትኩ፡፡
በአጭሩ የተፈጥሮ ግርማ፣ ፍቅርና ቁንጅና በሙሉ የፈሰሰባት ተአምር ናት ማለት ይቀላል፡፡ “ግን ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምንድነው የተፈጠረው? ለንቋሳና መልከጥፉ የሆነችው ሚስቴ በመስታወቱ እንዲህ ውብ ሆና ለመታየት የቻለችው በምን አይነት ተአምር ነው? እን-ዴ-ዴ-ትትት??”
መልሱ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ የአጉሊ መነጽር አይነት ስሪት ያለው መስታወት የሚስቴን አስቀያሚ መልክ አመሰቃቀለው፡፡ የተበታተኑት የፊትዋ ገጽታዎችም መስታወቱ በወሰዳቸው አዲስ ቦታ ሲቀመጡ ድንገተኛ አዲስ ቁንጅናን ፈጠሩ፡፡ መቀነስ በመቀነስ ተባዝቶ የፈጠረው መደመር እንደ ማለት ነው፡፡
እነሆ ከዛ እለት አንስቶ እኔና ሚስቴ ጎን ለጎን መስታወቱ ፊት ተቀምጠን ለአፍታ እንኳ አይናችንን ሳንነቅል ስናፈጥበት እንውላለን፡፡ አፍንጫዬ ወደ ግራ ጉንጬ በጣም ተጠግቷል፡፡ አገጬ ለሁለት ተከፍሎ ወደ ተቃራኒ ጎን ተጣሟል፡፡ የሚስቴ ገጽታ ግን አሁንም እንደፈካና እንደተዋበ ነው፡፡ ውስጤ ሊገለጽ በማይችል ብርቱ የብቸኝነት ስቃይ ሲወቀር ይታወቀኛል፡፡
ድንገት ከ-ት-ት-ት-ት ብዬ ከጣሪያ በላይ በማስካካት ሳቅሁ፡፡
የሚስቴ የሹክሹክታ ንግግር ተሰማኝ፡፡
“ውይይይ እንዴት ውብ ነኝ!!”

ተርጓሚ፡- ሳሙኤል እንግዳ

Read 103 times