Monday, 10 March 2025 10:10

ከአዲሱ “ሳላዛት” መጽሐፍ የተቀነጨቡ ቅምሻዎች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የእኛና የሌላኛዎቹ አለም ፍጡራን ነገር
…አጠቃላይ ቁመናው በወፍራም ብርሃንና ጨረር ተቀርፆ ይታየኛል እንጂ ዝርዝር መልኩን ማየት አልችልም። ደንግጫለሁ። የእግዚአብሔር ይሁን የሞት መልአክ ባላውቅም ከፊቱ በግንባሬ ወደቅሁ።
“ምን ሆንህ?” የሚል ንግግር ሰማሁ። የድምፁ አይነት ከሰው ልጅ ድምፅ ቃና ይለያል፣ ለጆሮ የሚከነክንና የሚሰቀጥጥ ቃና ነው። ከሆነ የዱር ወፍ፣ ከቆቅ ምናምን ጉሮሮ የሚወጣ ድምፅ ይመስላል፣ የቆቅ ያልሁት ከማውቀው ድምፅ ጋር ላቀራርበው ብዬ እንጂ በትክክል እንደ ቆቅም አይደለም፤ እና ትኩር ብዬ ስሰማው ድምፁ የሚያስፈራ ነገር አለው። ቋንቋው ግን ግልፅ የሆነ አማርኛ ነበር።
“የእግዚአብሔር መልአክ ሆይ በፊትህ እሰግዳለሁ” አልሁት እንደተደፋሁ ፊቴን ብቻ ቀና አድርጌ።
ሳቀ– በጣም አጭር፣ ቀድሞ የሚያቆም ሳቅ የሚመስል ነገር።
“የእግዚአብሔር መልአክ አይደለሁም” አለ።
“ምንድነህ”
“መጀመሪያ ተነስ። ተረጋጋ”
ተነስቼ ቆምሁ።
“ከሌላ ዓለም የመጣሁ ወንድምህ ነኝ” አለኝ።
“ሌላ ዓለም? …ከየት? እ… ምን ወንድም አለኝ…”
“ምን ወንድም አለኝ? ብታውቅበት በሁለንታው ውስጥ ያለው ሁሉ ወንድምህና እህትህ ነው። እኔ የፈጣሪያችሁ መንፈስ በጊዜና ቦታ አራርቆን የቆዬ ወንድምህ ነኝ”
“አልገባኝም እባክህ…”
“እሺ በሚገባህ ሰዋዊና ምድራዊ ዕሳቤ ልንገርህ፡ ከሌላ ፕላኔት ነው የመጣሁት”
“ሌላ ፕላኔት? ከየት?”
ሲነገር የነበረው ሁሉ እውነት ነው ማለት ነው?
“ዝርዝሩን ቆይ ቁጭ ብለን ትረዳለህ፣ አሁን ልረዳህ ነው ያገኘሁህ”
“ሰው ሳትሆን ምን ትረዳኛለህ? መንገዴን ባታሰናክለኝ እንደረዳኸኝ እቆጥረዋለሁ”
“እውነት እውነቱን ብቻ ንገረኝ፣ ወዴት ነው የምትጓዘው”
“እየሸሸሁ ነው”
“ከምን”
“ከሞት”
“ሞት ምንድነው”
“ሞት አላውቅም እያልኸኝ ነው? እያሾፍህ መሆን አለበት”
“አላውቅም ምንድነው”
“እንዴት ፍጡር ሆነህ ሞትን አታውቅም?”
“ትንሽ የተፈጥሮና የስልጣኔ ልዩነት አለን። ለዚያ ይሆናል ያላወቅሁት። እና ሞት ምንድነው”
***
“ሞት፡ ማንኛውም ባረን ለመጀመሪያም ለሁለተኛም ለሦስተኛም ጊዜ ስትነግረው የሰውን ልጅ ሞትና አሟሟት አምኖ ለመቀበል ይከብደዋል። በፈጣሪው አምሳል የተሠራ ፍጡር በእንቅፋት ይሞታል ብትለው ሊገባው አይችልም። የሞታችሁ ነገር እኔን እንኳን ለብዙ ዘመን ምድርን ያጠናሁትን ባረን ሁልጊዜ እንዳስገረመኝ ነው። ከሞታችሁ የበለጠ ደግሞ አሟሟታችሁ ያስገርመኛል። የምትሞቱበትን ጊዜ አታውቁም። አለማውቃችሁ ጥሩ፣ ግን ስትጓዝ እንደነበር በሆነ ምክንያት ልትሞት ትችላለህ። በበሽታ ልትሞት ትችላለህ። መኪኖቻችሁ ተጋጭተው ልትሞት ትችላለህ። እሳት ሊበላህ፣ ውሃ ሊወስድህ ይችላል። ከሕይወት ወደ ሞት ሽግግራችሁ ድንገተኛ ነው። እና አትመለሱም ደግሞ፣ ወይስ ትመለሳላችሁ? እሱን ፈጣሪያችሁ ነው የሚያውቀው። ኃያልና ደግ ፈጣሪ ነው ያላችሁ፣ ግን አበላሽቶ ነው የሠራችሁ”
***
“ሰማያዊው ጦርነት ባይቀድመን፣ ጉዞህን ቀጥለህ ለሁለተኛ ጊዜ ስንገናኝ ራስህን የተሻለ መንፈሳዊና አካላዊ ሁኔታ ላይ ታገኘዋለህ”
“ጦርነቱ መቼ ተጠናቆ እየሱስ ለመጀመሪያው ትንሳኤ ወደ ምድር የሚመለስ ይመስልሃል?”
“ምን ሊያደርግ ይመለሳል? ደግሞስ እየሱስ ብቻ ነው የሚመጣው? ቡድሃስ? ሞሀመድስ? ሙሴስ? ሌሎችስ አይመጡም? ደግሞስ ማን ያውቃል። ስለዚያች ቀን ከእግዚአብሔር በቀር መላእክትም ቢሆኑ፣ እየሱስም ቢሆን፣ ማንም ቢሆን የሚያውቅ የለም ይል አይደለም እንዴ መጽሐፋችሁ? ታዲያ ራሱ እየሱስ እንኳን የማያውቀውን ነገር እኔ ባረኑ እንዴት አውቃለሁ ብለህ ነው”
ባረኑ ሳቀና ቀጠለ፦
“ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ሊሆን ይችላል፣ ወይም መቼምም ላይሆን ይችላል፣ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ መጠበቅ አስፈላጊ እንዳልሆነ ነው። በመጠበቅ የሚመጣ ጊዜ የለም፣ ሁሉም ጊዜ ተሰጥቶ ያበቃ ነው”
***
የጊዜ ነገር
…በዙሪያዬ ማንም ምንም አልነበረም። በፀሀይና በሙቀት እየተቃጠልሁ በዚህ የቀትር ውቅያኖስ ባረጋው በረሃ መሀል ሳቋርጥ አንዳች ግዙፍ ነገር ከፊቴ ገጠመኝ። ቆምሁ።
“ምንድነህ ማነህ?” አልሁት። ፍርሀት የሚባል ነገር ከውስጤ ጠፍቷል።
“ጊዜ ነኝ” አለኝ።
“ጊዜ?”
“አዎ። የነበርሁ ያለሁና የተሰጠሁ”
“ኧረ ባክህ፣ ቀልደኛ። እሺ አቶ ጊዜ፣ ‘አቶ’ ልበልህ ወይስ ሌላ ማዕረግ አለህ?”
“የሁሉም ማዕረግ ባለቤት እኔ ነኝ፣ ሁሉም ከእኔ እየተዋሰ ነው የሚወስድ”
“ጊዜ እንዴት በአካለ ገጽ ሊገለጥ ይችላል?”
“ሁሉም ባለ አካለ ገፅ እኔ ውስጥ ነው ያለው፣ አንተ አሁን እኔ ውስጥ ነው ያለኸው”
“እዚህና እዚያ ለየብቻ ቆመን እንዴት እኔ ውስጥ ነው ያለኸው ትለኛለህ”
“መስሎህ ነው”
“እውን ጊዜ የምትባለው አንተ ነህ?”
“ጊዜ ነኝ፤ ስንቱን ከወደቀበት አመድ ላይ የማስነሳ፣ ለበደለኛ አበሳውን ለፃድቅ ዋጋውን የማልነሳ፣ ስንቱን ገናና እንዳልነበረ የምደመስስ። የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ እኔ ጊዜ ነኝ”
***
የፍቅር ነገር
…ምድራችን ለዘላለም ፀሐይን ስትዞር ትኖራለች። የእኔም ልብ ከዚህ ወዲያ ከአንዲት ፀሐይ የመሰለች የሴት ልጅ ምህዋር መውጣት የምትችል አልመስልህ አለኝ። ልቤ አሁን ላይ ከሀገረ-ዘላለማዊት ምህዋሯ ተጎትታ ወጥታ የምትዞረው በሰማንያ ስምንቷ ዙሪያ ነው። በሀይለኛው የሰማንያ ስምንቷ የስበት ወጥመድ ተይዤያለሁ። ምድር በፀሐይ፣ ጨረቃ በምድር ስበት ተይዘው እንደቀሩት ሁሉ እኔም የሰማንያ ስምንቷ የፍቅር ግራቪቲ እስረኛ ሆኜ እንዳልቀር ሰግቼያለሁ።…ቢሮዋ ሄጄ ያየኋት እለት ሌሊቱን ሁሉ በእንቅልፍ ልቤ ሳስባት ነው ያደርሁት። ተኝቼም ነቅቼም የማልመው እሷን ነበር። …
***
የትናንሽ ማንነቶቻችን ነገር
…የሰው ልጅ ሲወለድ ንፁህ ነው፣ ሰው ብቻ ነው። እያደገ ሲሄድ በትናንሽ ማንነቶች ይቆሽሻል። መጀመሪያ በሃይማኖት ጣሳ ውስጥ ያስገቡታል፤ ከዚያ በጎሳ፣ በብሔረሰብና በሀገር ብሔርተኝነት ገመድ ይተበትቡታል፤ ከዚያ የታሪክ፣ የፖለቲካና የርዕዮተ-ዓለም ሸክም ይጭኑታል። አደግሁ፣ በሰልሁ ሲል እውነቱን በእነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ውስጥ አጥሮ ይገነባል። በዚህ አጥር ውስጥ እንደኳተነ በመጨረሻም እውነተኛ ማንነቱን ሳያውቅ ያልፋል። …
***
የኢትዮጵያ ነገር
ሳንዶብ ቆይቶ ኢትዮጵያ መሄድ ከንፁህ ቤት ወጥቶ ጭቃ ውስጥ እንደመግባት ነው። ሀገሬን ስለማልወድ አይደለም እንደዚያ የምለው፣ ጨለምተኛ ሆኜም አይደለም። እውነታው እንደዚያ ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያን በተቀባባ እውነት እየለደሱ እያቀረቡ ሀገር ወዳድ መስሎ መታየት አያዋጣም፣ ለማንም አይጠቅምም። የሚጠቅመው እውነታውን ተረድቶ ሀገሪቱን ለማሰልጠን ቆርጦ መነሳት ነው። ኢትዮጵያውን ያለፈ ታሪካቸውን ኩራት እያንቀራጩ (እና በእሱም እየተናጩ) ፈዘው የቀሩ ህዝቦች ሆነዋል። ኢትዮጵያውያን በታሪክና ትርክት፣ በጎሳ ፖለቲካና በአሮጌ ልማድ ውስጥ ተሰንቅረው ቀርተዋል። ሁለ ዓለማቸውን ስንቅሩ ውስጥ ሠርተዋል። ራዕያቸው ከስንቅሩ ወጥቶ ወደ ሁለንታው ዓለም መቀላቀል አይደለም፤ ይብዛም ይነስ ራዕያቸው አንዱን ወደ ቀዳዳው ገፍቶ ስንቅሩ ውስጥ የተሻለ ቦታ መያዝ ነው። …
***
የጦርነትና የህዋ ስልጣኔ ነገር
…አዎ፣ የሰው ልጅ ለህዋ ስልጣኔ የሚሆን ገንዘብ የለውም። ምክንያቱም፣ ምድር ላይ ያለውን ችግር አልፈታም። ቢሊዮኖች ዶላር በሙስና ይዘረፋል፣ ቢሊዮኖች ዶላር በባለሀብቶች ከንቱ ቅንጦት ይወድማል፣ ቢሊዮኖች ዶላር እየመደበ አንዱ ሀገር ሌላውን ይሰልላል፣ ትሪሊየኖች ዶላር ለጦር መሣሪያ መግዣና ለጦርነት ማድረጊያ ይወጣል፣ ጦርነቱ ትሪሊየኖች ዶላር ያወድማል። ጦርነቱ ያወደመውን ለመጠገን እንደገና ትሪሊየኖች ዶላር ይወጣል። ባለ መከራው እንባው ታብሶ፣ የወደመው ተጠግኖ ሳያበቃ እንደገና ትሪሊየኖች ዶላር የሚያጠፋ ሌላ ጦርነት ይፈነዳል። ምድር ያለቺው በዚህ የጥፋት አዙሪት ውስጥ ነው። ታዲያ እንዴት የሰው ልጅ ለህዋ የሚሆን ገንዘብ ሊኖረው ይችላል? እንዴትስ በቢሊየን የሚቆጠር ህዝብ እየተራበ፣ እየተሰደደና በበሽታ እያለቀ ለህዋ ምርምር ገንዘብ የማውጣት ሞራል ሊኖረው ይገባል? የህዋ ስልጣኔ ለሰው ልጅ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና ነው። ይህ የሚሳካው ግን የሰው ልጅ ስር የሰደዱ ችግሮቹን ፈቶና ትናንሽ ማንነቶቹን አውልቆ ጥሎ ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት መገንባት ከቻለ ብቻ ነው።
***
የፕላኔታችን መልካም እጣ
የብዙ ሰዎች ሕልም መጓዝና ጥበብን ማድነቅ ይሆናል። በአንድ ፕላኔታዊ ፌደሬሽን በታቀፈች፣ ሰላም ፍትሕና ስልጣኔ በሰፈነባት ዓለም ላይ ስፖርት፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም የምድራችን ቀዳሚ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ይሆናሉ።

Read 189 times