Monday, 10 March 2025 10:21

“ነጋ ደሞ፤ ሥራ ልግባ”

Written by  ዮርዳኖስ እስጢፋኖስ
Rate this item
(2 votes)

“ነጋ ደሞ፤ ሥራ ልግባ” ግጥም ከጋሽ ማቲያስ ከተማ (ወለላዬ) “የእኔ ሽበት” የግጥም መድበል ውስጥ የተወሰደ ግጥም ነው። በጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን “መሸ ደሞ፤ አምባ ልውጣ” ድምጸት የተጻፈ ይመስላል። ጋሽ ጸጋዬ ግጥሙን የጻፈው ነፍሱ የጥበብን ንግሥት ስትፈልግና ስታገኝ የሚሰማውን ዕርካታ ለመግለጽ መሆኑን በፋሲል ይትባረክ “ምትቀጥ በቅኔ አክናፍ” መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተቀምጧል፤

“ጋሽ ጸጋዬ ‘መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ’ በተሰኘው ግጥሙ፣ የፍቅረኛውን ገላ የናፈቀ አፍቃሪ በሌሊት እሷ ወዳለችበት አምባ ሲሄድ ያሳያል። ፍላጎቱን አርክቶ ወደ ቤቱ ቢመለስም በማግስቱ ሌሊት እንደገና ፍላጎቱ ከትናንትናው ይበልጥ አይሎ ይመለስበታል። ፍቅረኛውን ሲያቅፋት ለሚሰማው ለዚያ የደስታ ሥሜት ተገዢ ይሆናል። አፍቃሪው ቀኑን ሙሉ የሚያሳልፈው በአምባው ጫፍ የምትኖረውን ፍቅረኛውን የሚያገኝበትን ሰዓት በጉጉት በመጠባበቅ ነው። ግጥሙን በጥሞና ስናነበው ግን ቀጠሮው ሌላ ዓይነት ትርጉም እንዳለው እንረዳለን። ባለቅኔው ከጥበብ ንግሥት ጋር ያለው የየዕለት ቀጠሮ መሆኑንም እንገነዘባለን። በምናብ ክንፍ ጥበባዊ ችሎታው ወደ ጥበብ አምባ እንዴት እንደሚከንፍ ይገልጻል። በፈጠራ ሥራው ሥሜቱ በትፍሕስት እንዲረካ ምክንያት የሆነው የፈጠራ ሥሜት ውሽንፍር በውስጡ ሲነሣ፣ ያንንም በቃላት አማካኝነት ጠልፎ ሲያስቀረውና ተጨባጭ ሲያደርገው የሚሰማውን ደስታና ዕርካታ ያንጸባርቅበታል”
ጋሽ ጸጋዬ ከጥበብ ንግሥት ጋር ላለው ቀጠሮ በማስግቱ እንደገና እንደሚነሣው ሁሉ ጋሽ ማትያስም ከስደት ሕይወት ኑሮ ጋር ለያዘው የየዕለት ቀጠሮ ማልዶ ይነሣል፤። ጋሽ ጸጋዬ የጥበብ ንግሥትን ጋሽ ማትያስ ደግሞ የስደት ሕይወት ትርጉምን የሚፈልጉ ይመስላሉ። በርግጥ የጋሽ ጸጋዬ ከፍ ይላል። የስደት ሕይወት ትርጉም ኀሠሣም ቀላል አይደለም። ጋሽ ማትያስ ግጥሙን የሚጀምረው “በስደት ዓለም ያለህ ይሄን አላልኩም ካልክ ዋሽተኸኛል ማለት ነው። ለነገሩ አንተ ያሻህን ሁን፤ እኔ ግን እንዲህ ሆኛለሁ” በሚል መግቢያ ነው። ይለጥቅና፤
“ሰዓት ልቆጥር ጊዜ ላምጥ
ልሽከረከር በሐሳብ ማጥ
በማይለቀኝ በዚያ አዙሪት
ስንገላታ ልውልበት
ሳይመሽልኝ ዛሬም ጠባ
ልሂድ ደሞ፤ ሥራ ልግባ” ይላል።
በመሬት የሰሜን ጫፍ (north pole) ላይ ተንጠጥሎ መኖር ከሚያመጣቸው ጉዳዮች አንዱ የጭለማና ብርሃን አለመመጣጠንና እሱን ተከትሎ የሚስተዋለውን የዓየር-ንብረት ሁናቴን መጋፈጥ ነው። ይህን ጉዳይ “ጉርሻና ቅምሻ” በሚለው በቅርቡ በጻፈው የወግ ስብስብ መጽሐፉ ሸጋ አድርጎ ተርኮታል። ከቁር ጋር የተያያዘውን ጉዳይ በዚህ ግጥሙም እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፤
“እንዳይበርደኝ የደረብኩት
በለጥ ይላል ከኔ ክብደት
ይሄም አንሷል ለበረዶ
ተቆልሏል ዛሬም ወርዶ
ልብሴና እኔን ተሸክሜ
ስንቀሳቀስ ስሄድ ቆሜ
የሚጎተት የድሮ ሱቅ
እመስላለሁ አቤት! ሳሥቅ።”
አንዳንድ ዲያስፖራ “ብር ላክ ሲባል” እንዳው ላመል ያህል ይነጫነጫል፣ ይበሳጫል፣ ይቆጣል። ይሁን እንጂ ዘመድ አዝማድ፣ ወዳጅ፣ ጎረቤትና ጓደኛ የብር ተማጽኖውን ድንገት ቢያቆም፣ ጥቂት የማይባል ዲያስፖራ የስደት ሕይወቱ ትርጉም ሊያጣበት ይችላል። ብላቴናው “ትርጉም ያጣብኛል የስደት ሕይወቴ!” እንዲል። ጥቂት የማይባል ዲያስፖራ የስደት ሕይወቱ ትርጉም የሚሰጠው፣ ከስንፍናው የሚበረታው፣ ለደንታቢስነቱ ወኔ የሚያገኘው፣ ለናፍቆቱ ብርታትና ለድካሙ ምርኩዝ እንዲሁም ለክብሩ ድጋፍ የሚያገኘው የገንዘብ ዐቅሙን ወደ ማኅበራዊ ዕውቅና (social status) ሲቀይር ነው ማለት ይቻላል። ይህን በተመለከተ ግጥሙ እንዲህ ይላል፤

“አለቃዬ ተኮሳትራ
በእኔ ሳይሆን በሷው ሥራ
ሰላም ስላት እንዳላየች
ገፋ አድርጋ ታልፈኛለች።
ሥራው ደግሞ ተርመጥምጦ
ሲጠብቀኝ ዓይን አፍጦ
ትቼው ልሄድ አስብና
መለስ ስል እንደገና፤
ያቺ እናቴ የአገርቤቷ
ጠባቂዬ በጸሎቷ፤
እኅቴና ያ ወንድሜ
እህል ሲያጡ እኔ ቆሜ፤
ያሳደገን እኛን ለፍቶ
አባታችን ፊቴ መጥቶ
ድቅን ሲል ሁሉን ትቼ
ከሥራው ጋር ተስማምቼ
እውላለሁ ምን ይደረግ
ሳጸዳና ስጠራርግ።”

“መለስ ስል እንደገና…” የምትለው ሐረግ ዓይነተኛ አያያዥ ነች። “ምን ይዤ ልመለስ?” ዓይነት ሥሜትን ታጭራለች። ጋሽ ፈቃደ አዘዘም “ፓስፖርቴን ልቅደደው” የሚል ተመሣሣይ ሥሜት ያዘለ ግጥም ያለው ይመስለኛል። ፓስፖርቱን ሊቀድደው ይዳዳውና አያስችለውም። ሐሳቡን ቀይሮ የስደት ሕይወትን ይጋፈጠዋል። ከዚህ በተጓዳኝ በውጭ ሀገራት ሲኖሩና ሲቆዩ፣ ሠርተው እንዳልሠሩ ደክመው እንዳልደከሙ የሚያደርግ አንዳች መንፈስም ያለ ይመስላል። ይህ ዓይነቱ ስሜት ብሩን “በትነው በትነው” ፣ ሕይወትን “ዘንጋት ዘንጋት” የሚል የሚያልፈሰፍስና ደንታቢስ የሚያደርግ ድንገት የሚወር ሥሜት ይመስላል። በግጥሙ ውስጥ በጥቂቱ ተመልክቷል፤
“ምን ብሠራ ብዙም ባገኝ
ዕርካታና ደስታም የለኝ።
ወይ ለእነሱ አላሳለፍኩ
ወይ ገንዘቤን በቅጥ አልያዝኩ።”
ጋሽ ማትያስ በዚህ ዓይነት የሥሜት ውጥረት ላይ ሆኖ ሕይወቱ ልታመልጠው በይ በይ ሲላት፣ መኖር አልያዝለት ሲለው፣ አጋር ፍለጋ ይማትራል። ይህን መዝረክረክ እንድትሰበስብለት፣ የስደት ሕይወቱን ቅርጽ እንድታስይዝለት የሚያስበው እኅት ወይም ሚስትን (ሴት ልጅን) ነው። “እስቲ መላ በይኝ፣ መላ ካንቺ ይገኛል፤ እኔማ ወንድ ነኝ ይደናገረኛል” እንዲሉ! ከዚህ ባሻገር ሚስት ማግባት ቢሻም፣ ትዳሩን የሚያየው እንደ strategic alliance እንጂ እንደ ፍቅረኞች ጥምረት አይመስልም። “ይሻል እንደሁ መተጋገዝ!” - ይላል፤
“አገሬ ላይ ቤት ሠርቼ
ያቺ ጩኒን ቶሎ አምጥቼ
ሁለታችን በርብርብ
አጠራቅመን ይዘን ገንዘብ
ከዚህ አገር ቶሎ ልሂድ
እኖራለሁ በትንሽ ንግድ፤
ወይ አርፌ ትዳር ልያዝ
ይሻል እንደሁ መተጋገዝ
ብዬ እያልኩኝ ሳሰላስል
ከሥራ ጋር ስብሰለሰል
አንዱን ስይዝ አንዱን ስጥል
በአካሌ በመንፈሴ
ተሽመድምጄ ደክማ ነፍሴ
ዛል ብሎ አካላቴ
አዘግማለሁ ወደቤቴ።”
ዲያስፖራ ገንዘብ ካልላከ የስደት ሕይወቱ ትርጉም ላይሰጠው ይችላል ማለት ግን ሀገርቤት ሆነን ከውጪ የሚላክልንን ገንዘብ ማባከኑ (extravaganza) ልክ ነው ወይም ደግሞ በረባ ባልረባው፣ ለትልቁም ለትንሹም ወደ ውጪ መመልከቱ ልክ ነው ማለት አይደለም። በውጪ ሀገራት የሚገኙ ወገኖቻችን በምን ዓይነት አድካሚ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሠርተው ብሩን እንደሚልኩ ብናውቅ ገንዘቡን በአግባቡ እንጠቀምበት ነበር። ይህ የስደተኞች ድካም በሌሎች ስደተኞች ሕይወትም እንደተመለከተው የዕንባ፣ የላብ አንዳንዴም የደም ውጤት ሊሆን ይችላል። ጋሽ ነቢይ መኮንን “የኛ ሰው በአሜሪካ” መጽሐፉ ላይ ይመስለኛል፣ አንድ ሰው ሲሠራ ውሎ ዝሎ ቤት ሲደርስ፣ ምግብ ለማኘክ እንኳ ዐቅም እያነሰው ጭማቂ ጠጥቶ እንደሚተኛ ጽፎ ነበር። ጋሽ ማትያስም ወደ ግጥሙ ማገባደጃ ይህንን ነጥብ ያነሣል፤
“መቼም አያልቅ የኔ ፍርጃ
ደግሞ አለብኝ ያ ደረጃ
እንደምንም ከሱ አልፌ
ከዕዳ ፖስታ ተቃቅፌ
እወድቃለሁ ተሸንፌ።
እንደገና በሐሳብ ማጥ
ተዘፍቄ ልርመጠመጥ
በማይለቀኝ በዛ አዙሪት
ስንገላታ ልውልበት
ላይመሽልኝ ዛሬም ጠባ
ልሂድ ደሞ፤ ሥራ ልግባ።”
መድበሉ ሌሎችም ተመሣሣይ ማኅበራዊ ኑሮንና የስደት ሕይወትን የሚዳሥሡ ግጥሞች አሉት። ሁለቱን እነሆ፤

መርፌ
አንድ ቀን ተነሥቶ፣
መርፌ ተቆጥቶ፣
መርፌ ተበሳጭቶ፣
አልሰጥም ያለ ቀን
ያንን ቀዳዳውን፣
ክር አንጀቴን በላኝ
እንጃለት መግቢያውን።

ያነሡት የለም ወይ
ያ በላይ መረሳ* የኮሜዲው አባት፣
ልጁ ግዳጅ ሊሄድ ተደግሶ ሽኝት፣
ሣቅ ጨዋታው ደምቆ ሲደነስ ሲጨፈር፣
ልጁ እደጅ ወጥቶ ከወዳጆቹ ጋር፣
የት ሄደ ብሎ ሲል በላይ ተቆጥቶ፣
ሊነሣ ነው ቢሉት ማስታወሻ ፎቶ፣
ምን ያስቸኩለዋል አዬ የልጅ ነገር፣
ያነሡት የለም ወይ ሲሄድ ወደዛ አገር
ብሎ እንደቀለደ ልጅዬው ነገረኝ
አንድ ቀን በድንገት ቡና ቤት አግኝቶኝ።
(*በላይ መረሳ እውቅ ኮሜዲያንና የጥበብ ባለሙያ ነበር።)
መልካም ንባብ!!

 



Read 137 times