Monday, 10 March 2025 10:34

አደገኛ የኳስ ፍቅር “ክለብ አይቀየርም!”

Written by  ወ. ማ
Rate this item
(2 votes)

ሰሚት ኮንደሚኒየም ግቢ ከምትገኘዉ ፀጉር ቤት ደንበኛዬ ዘንድ ወረፋ እየጠበቅኩኝ ሳለሁ ነበር...ምሳ አብረን በልተን እቤት ጥዬው የወጣሁት ባሌ፣ ቱታውን ለባብሶ በዚያ ጠራራ ጸሃይ ፈጠን ፈጠን እያለ ረዥሙን የኮብል ስቶን መንገድ ተያይዞት ያየሁት... ወዴት እየሄደ ነው? በሰንበት...በዚህ ፀሃይ...ከፋርማሲ ዉጭ ወደየትም ሄዶ የማያውቀው ሰውዬ... እንኳን ግቢው ውስጥ ጎረቤታችን ያለውን አባወራ እንኳን አራት አመት አብረን ኖረን ስሙን የማያውቀዉ ሰዉዬ... ማን ዘንድ እየሄደ ነዉ ይባላል?
ስልኩ ላይ ስደውል...ሰራተኛችን አነሳችው...ስልኩንም አልያዘም!...ጎሽ!... እንግዲህ ምን ቀረኝ? አቋርጬ ወጣሁ... ይባስ ብሎ ከኮንደሚኒየሙ ግቢ ውጭ ወደሚያስወጣዉ መንገድ ታጥፎ ወደ መንደር ዉስጥ አቀና፡፡ የዚህን ነገር መጨረሻ ለማየት ጓጓሁ... ትንሽ እንደሄደ ወደ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በሚወስደዉ መንገድ ሲታጠፍ...ለቀብር ካልሆነ ደጀሰላም የማይደርሰዉ ሰውዬ መቸም ቤተ ክርስቲያን አይገባምና...የት እየሄደ ነዉ ልበል? ግን እንዲለይልኝ ነዉ መሰለኝ ከደጀሰላሙ ቅጥር ዘው ብሎ ገባ፡፡ ከሰው ጋር ለመገናኘት ቤተ ክርስቲያን መቀጣጠር ተጀመረ? ነገር ግን ... ከርሱ ዉጭ ማንንም ሰው በዙሪያው አላየሁም... በጣም የገረመኝ ነገር ...እጅግ በጣም የገረመኝ ነገር....እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ ሲንበረከክ ማየቴ ነበር...ውስጤ ራደ፡፡ ...እየፀለየ ነው...ባሌ እየፀለየ ነዉ...ንሰሃ እየገባም ሊሆን ይችላል...ስለት እየተሳለም ሊሆን ይችላል...ብቻ ቤተ-እምነት ገብቶ ሲንበረከክ አየሁት... ለመጀመሪያ ጊዜ...ወንድሜን!! ባሌ የሆነ ነገር ሆኗል ማለት ነው፡፡
...እዚያው እስኪወጣ ጠበቅኩት...
“...ተከትለሽኝ ነበር ማለት ነዉ?”
“ወንድ ልጅ ፈትተሽ ከለቀቅሽው ተሸራርፎ ነዉ የሚመለሰው” ትል ነበር አያቴ...
“ማን ይሸራርፈኛል ብለሽ ነዉ? እራስሽ ሸራርፈሽ ጨርሰሽኝ...”
“ለኮንደሚንየም አሮጊት ታንሳለህ እንዴ?...”
“ይልቅ አያትሽ ከመከሩሽ ሁሉ “ከባልሽ ኪስ ምንም ነገር አትውሰጂ” ያሉሽን ነው የምወድላቸው--”
“...በጠራራ ጸሃይ ምንም ሳትነገረኝ ወጥተህ ስትነካው ዝም ማለት ነበረብኝ? ግን ምንድነው የሆንከዉ?”
“ማለት?”
“ያስጨነቀህን ነገር ምንድነዉ?”
“ለሰዉ አይነገርማ...”
“ቀልዴን አይደለም!...ምንድነዉ ያስጨነቀህ?”
እፍረት ብጤ ይታይበት ነበር...
“የሰሞኑን ሁኔታዬን እያየሽ...”
“ማለት?”
“ደብሮኛል..። ታዉቂ የለ?”
“በርግጥ በዛ በተረገመ ኳስ ተናደህ እንቅልፍ ሁሉ እምቢ እንዳለህ አዉቃለሁ...ሌላ የተፈጠረ ነገር አለ?”
“...እንቅልፌንም...ሰላሜንም ነሳኝ... ለምን እርግፍ አድርጌ አልተወዉም፡፡”
“...ስለ ኳስ እያወራኸኝ አይደለም አይደል?”
“...አንቺ ምን አለብሽ?”
“የነነዌ ንጉስ” አምላክ የህዝቡን ሃጢያት ይቅር እንዲል ዘንድ...የእርሱን ያህል መጨነቁን እጠራጠራለሁ... ስንት “እግዚኦ” የሚያስብል ነገር ባለበት ሀገር የኔን ባል ጭንቀት እዩልኝ፡፡
* * * * *
ሃያ አመት ሊሞላዉ ነዉ...ያኔ...እኔ ለስራ ልምድ እንዲሆነኝ በፀሃፊነት የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ከሄድኩባት እርሱ ደግሞ ለሆኑ ፈረንጆች አስተርጓሚ ሆኖ ተቀጥሮ መጥቶ ከሚኖርባት...መብራት እንኳን ከሌላት የወረዳ ከተማ ስንኖር...ያኔ.. ድሮ...ድሮ ሳውቀውም... ይህ ሰው በኳስ ፍቅር አቅሉን የሳተ ነበር፡፡
መቸም የማልረሳዉ፣ የሳምንቱ አጋማሽ አንዱ ቀን ነበር...ከቢሮ በጊዜ ወጥቼ...ከደከመችዉ ጉልት ለእራት የሚሆን ነገር ሸማምቼ... የሌሊት ፒጃማዬን ሸክፌ ...አፈር አፈር የሚሸት ኦና ቤቱን አሰናድቼ ልጠብቀዉ ቤቱ ሄጄ...ወግ ወጉን ተያይዤ ሳለሁ ከምሽቱ 1 ሰኣት አካባቢ መጣና ተደናግጦ እያየኝ...”ፍቅር? ...ባልጠፋ ቀን ዛሬ ትመጫለሽ እንዴ?” አለኝ
ከመደንገጤ ማፈሬ ... “ምነዉ? ዛሬ ምን አለ?” አልኩት
“ዛሬኮ ኳስ አለብኝ...”
“ኳስ ኳስ ኳስ...ይህ የምትጫወቱት ኳስ ? ...በጨለማ ልትጫወቱ?”
“በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ጨዋታ አለ... እሱን ማየት እፈልጋለሁ...ማለቴ ነው...”
“አብረሃቸው የምትሰራቸዉ ፈረንጆቹ ቴሌቪዥን አላቸዉ እንዴ?”
“የላቸዉም!”
“እና?”
“ከተማ ሄጄ ? “
“ከተማ ስትል ? ከመሸ 30 ኪሎ ሜትር ተጉዤ ኳስ አያለሁ እያልከኝ ነው? በምንድነዉ የምትሄደው?”
“መኪና እንኳን አስፈቅጃለሁ... ጓደኞቼም አሉ...ለምን አብረን አንሄድም?”
የዛን እለት እንዴት ዘልዬ አልቧጨርኩትም ግን??? መቸ ልቧጭረዉ ኑሯል?
“እኔ ነኝ በዚህ ምሽት ከጓደኞችህ ጋር ከተማ የምሄደዉ? ሄድኩ እንበል...ሆቴል አብሬያችሁ በእኩለ ሌሊት ኳስ ልይ?.. የሚያውቀኝ ሰው ቢያየኝስ?” አንዘፈዘፈኝ፡፡
“እሺ ምን አድርግ ትይኛለሽ?”
“አንተን ብዬኮ ነዉ የመጣሁት...ካንተ ቤት ላድር...ካንተ ጋር ላድር...” ነደደኝ፡፡
ዝም አለ፡፡
“...ለመሆኑ የአለም ዋንጫ ዛሬ ማታ ነው እንዴ?” አልኩት፤ በንዴትም ግራ በመጋባትም ውስጥ ሆኜ...ያው አባቴ “ብራዚል የዋንጫ ጨዋታ አለባት” ሲል ሰምቼ አውቃለሁኝ፡፡
ከት ብሎ ሳቀና...”እንደሱ አይደለም የኔ ፍቅር..የክለቦች ጨዋታ ነዉ...ዛሬ ጦርነት አለብን...ሮም እንዘምታለን”
ምኑም ሊገባኝ አይችልም ነበር...
“አርሴናል ከሮማ ጋር የሞት ሽረት ጨዋታ አለበት...ሌላ ጊዜ በደንብ አስረዳሻለሁ”
“አታስረዳኝ! ...ለመሆኑ አርሴናል ምንድነው? ሮማ ምንድነው?”
“የእግር ኳስ ከለቦች ናቸው....” ሳቁ... አለማወቄን ያሳብቃል...
“ዛሬ ከኔና ከዚህ አርሴናል ነው ምናምን ካልከው አንዱን ትመርጣለህ!”
ዝም አለ፡፡
“ሰምተኸኛል ...አንዳችንን ትመርጣለህ!”
“ጥሩ ጥያቄ አይደለም... እንደሱ አትበይኝ...በእናትሽ...” አለኝ፡፡
...ይህ አርሴናል የሚባል ጋኔን ምንድነው? ጦርነት አለብኝ ይላል እንዴ ...አይመልሰዉ ከሄደበት!!
* * * * *
...ለጋ ፍቅሬን ትቶት፣ ለጋ አእምሮዬን ጎድቶት፣ ለጋ ሰዉነቴን ንቆት...”ኳስ” ብሎ ...”አርሴናልን” ብሎ እዚያች ኦና ቤት ጥሎኝ ሊሄድ የወሰነውን ሰዉዬ፣ እኔም እርመ-ቢሷ አግብቼዉ ሚስቱ ልሆን ስወስን...ከኳስ ልለየው እንደማልችል ማመን ነበረብኝ፡፡
ኳስ ካለበት ሁሉ አለ... በተለይ አርሴናል ከተጫወተ...ደግነቱ እናቱም አባቱም የሞቱ ጊዜ አርሴናል ጨዋታ አልነበረውም እንጂ... የቀብራቸዉ ዕለትም ቢሆን ቴሌቪዥን ያለበት መሄዱ አይቀርም ነበር፡፡ እኔን እንኳን ይቀብረኛል...ምክንያቱም በዛሬ ጊዜ ጨዋታዉ የሚተላለፍበት ሰዓት ከቀብሬ ሰዐት ጋር ከገጠመ “በስልኩ ያያል”...ከቀብር መልስ ከሆነ ደግሞ ቤት እንደገባ “65 ኢንቹን ይከፍተዋል”... እኛ ቤት እድር ሳንከፍል ቀርተን የምንቀጣበት ጊዜ አለ...መብራትም ውሃም ተቆርጦብን ያውቃል... ዲ ኤ ስ ቲቪ ክፍያ ግን በፍጹም አይሳትም፡፡... በጠባብዋ የኮንደሚኒየም መኝታ ክፍላችን ወስጥ 32 ኢንች ቲቪ አለኝ... የርሱን ኳስ እንዳልሻማበት...
ይኸዉ ሁለት አስርት ዓመታትን ልንደፍን ተቃርበን ...ዘንድሮ ላይ...ዛሬ ላይ...ዉዱ ባሌ... ስለ ኑሮ ውድነት...ስለ ሰላም...ስለ ሀገር...ስለ ጤና ...ስለ ነገ...ሳይሆን ስለ ኳስ ይሳላል፡፡
“...ቅዱስ ሩፋኤል ምን እንዲያደርግልህ ነዉ የምትማጸነዉ?” አልኩት
“ኳስ ከሚባል ነገር እንዲገላግለኝ...እንድረሳ...እንዳርፍ...ሳልናደድ እንድውል...እንዲያደርገኝ...”
“ከኳስ ነዉ ወይስ ከአርሴናል የሚገላግልህ?...”
“ተይኝ እባክሽ!...”
“ባለፈው አመት ዋንጫ አልበላችሁም እንዴ?” አልኩት
ሳቀ... እኔ መቸም አይገባኝም... ስለ ኳስ ያለኝ እውቀት ሁሌም ያስቀዋል...ግን አንድ ነገር አውቃለሁ...ይህ አርሴናል የሚባል ነገር ክፉ መንፈስ ነዉ... በጠበል እንኳን ከቤቴና ከባሌ ውስጥ የማይወጣ ድግምት... እነዚያን ሁሉ አመታት...
“መቼም አንበላም!”... “ከአርሴናልን ምንጭ ውሃ የጠጣ ሁሌም ይጠማል”... ከመፅሐፍ ቅዱስ ሁሉ መጥቀስ ያምረዋል...
“ነገ... ነገ ...ነገ ለከርሞ... ለከርሞ...ለከርሞ እያልን ኖርን...ስንት አመት ሙሉ ጠበቅን... በቃኝ!! ሁለተኛ ኳስ አላይም! መልአኩ ይረዳኛል!” አለ፡፡
ያመረረ ይመስላል...ግን...የማውቀው ሰውዬ እንዲህ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም፡፡
“ለምን ሌላ ክለብ አትቀይርም? ዋንጫ የሚበላ...” አልኩት፡፡
“ሆሆሆ!!! ... እንዴት ይሆናል???”
“ምን ችግር አለዉ?”
”ጾታህን ቀይር” ቢባል እንኳን እንደዛ አይንገሸገሽም፡፡
“የኔ እመቤት...ሃገር ሃይማኖትና ሚስት አይቀየሩም!”.አለ
“ይህን ያህል?” አልኩት
“...ሚስት እንኳን ልትቀየር ትችል ይሆናል...ብቻ ክለብ አይቀየርም!!!”
ባንዴ ቁስሌን ቧጠጠው!
ያኔ...ያበስልኩትን እራት እንኳን ሳልበላ... በዛ ጨለማ ፌስታሌን ሸክፌ...የእውር ድንብሬን ወደ ቤቴ ስመጣ መች ገደደው?...ተከትሎኝ...ቤቴ ስገባ አረጋግጦ ከመሄድ በስተቀር...ትንሽ እንኳን አግደርድሮኝ ነበር እንዴ?...ዳሩ የት እሄድ ነበር? ሰዉ አላውቅ...ወንዝ አላውቅ... ተራራ አላውቅ...ከርሱ በስተቀር! እናም ዛሬ ላይ ቆመንም “ሚስት ትቀየራለች” ይበለኝ?
“... አንድ ነገር ልንገርህ? ... መቼም ዋንጫ አትበሉም!... መቼም!!!” አልኩት
“እሺ...!” አለ፡፡
“እረግሜአለሁኝ...ያኔ... በዚያ ጨለማ...ተዋርጄ... አፍሬ... ጠባብዋ ክፍሌ ስገባ...በልጅነት ቅን ልቤ...ምርር ብዬ እያነባሁኝ እረግሜአለሁኝ!!” እንባዬ አቀረረ...
“...ሮምን በሄነሪ ሀትሪክ አፈራርሰን የመጣንበት ምሽት ነበርኮ...” አለ፡፡
ባይሳክልኝም...ልቧጭረው ሞክሬ ነበር...
በድንጋጤው ውስጥ ሆኖ ... “ኧረ እማ...ስንት ዘመን አልፎ... ልጆቻችን እንኳን ጎርምሰው...ዛሬ ላይ እንዲህ አይነት ምሬት...ኧረ በስማም... ለምን ጥንቅር ብሎ አይቀርም!” አለኝ፡፡
...በርግጥ ዘመን ቂም ያስረሳል እንዴ?
“...አንድ ነገር ልምከርህ አልኩት...” ትንፋሽ እያጠረኝ...
“ምን ?” አለኝ
“እኔን ይቅርታ ጠይቅ... ምናልባት ለሚቀጥለው አመት ዋንጫ ትበሉ ይሆናል!”

 

Read 244 times