Monday, 10 March 2025 19:36

ኦክሎክ ሞተርስና ማህበራቱ ችግራቸውን በእርቅ መፍታታቸውን አስታወቁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ኦክሎክ ሞተርስና አንዳንድ ማህበራት በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በእርቅ መፍታታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይሄ ይፋ የተደረገው ዛሬ ጠዋት ረፋድ ላይ የኦክሎክ ሞተርስ ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም የሽማግሌና የማህበራቱ ተወካዮች በተገኙበት በድርጅቱ ዋና መ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

ኦክሎክ ሞተርስ ባሰራጨው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ከጥቂት ወራት በፊት በተሳሳተ መረጃና ጉዳዩን በጥልቀት ካለመረዳት የተነሳ ከድርጅታችን ጋር የሽያጭ ውል በመግባት ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ተስማምተን በጋራ እየሰራን ካሉ በርካታ ማህበራት ውስጥ በተወሰኑ ማህበራትና ግለሰቦች አማካኝነት በድርጅቱ ላይ የስም ማጥፋት ተግባር ተፈፅሞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ማህበራቱና አባላቱ ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመሩና በጊዜው የተነገራቸውን መረጃዎች መለስ ብለው በማጣራትና ከድርጅታችን ጋር በመነጋገር፣ በሀገራችን ባህል ወግ መሰረት፣ ችግሩን በእርቅ ፈተን በመስማማት ወደ ትግበራ ስራ ገብተናል ብሏል፤ ድርጅቱ በመግለጫው።

ኦክሎክ ሞተርስና ማህበራቱን በሽምግልና ለማስታረቅ እልህ አስጨራሽ ጥረት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ የማታ ማታ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ገንዘብ የሚፈልጉ ገንዘብ፣ መኪና የሚፈልጉ ገንዘብ እንዲወስዱ የተስማሙ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት 20 ያህል አባላት መኪና እንደሚረከቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ገንዘብ የሚፈልጉ ደግሞ በ45 ቀናት ውስጥ ገንዘባቸውን እንደሚወስዱ ተነግሯል፡፡

በእርቅ ስምምነት ላይ የደረሱት የማህበራት ተወካዮች በሰጡት አስተያየት፤ "ወደ ህግ መሄድ ጊዜ የሚፈጅና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስከትል በመሆኑ ችግራችንን በእርቅ ለመፍታት ተስማምተናል" ብለዋል፡፡

በኦክሎክና ማህበራቱ መካከል እርቅ ለማድረግ ተነሳሽነቱን የወሰዱት የሽማግሌዎቹ ተወካይ እንደገለጹት፤ መጀመሪያ ላይ ከሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አላገኙም ነበር፡፡ "በተለይ ማህበራቱ ከኦክሎክ የተላክን መስሏቸው ዕርቁን አሻፈረን ብለው ነበር፤ ዓላማችን በሁለቱ መካከል ሰላምና እርቅ መፍጠር መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ነው የተስማሙት" ብለዋል፤ በሰጡት መግለጫ፡፡

የኦክሎክ ሞተርስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ካሣሁን በበኩላቸው፣ መጀመሪያ ላይ በማህበራቱ በኩል ስለድርጅቱ የተሳሳተ መረጃ ይሰራጭ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ለአብነት ያህልም፡- ኦክሎክ ከማህበራቱ አባላት 1.2 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ አንድም መኪና አላስመጣም የሚለው ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በራሱ በድርጅቱ የተመዘገበ የመኪና መገጣጠሚያ ፈቃድ የለውም የሚል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

"እውነቱ ግን ኦክሎክ ሞተርስ በመቀሌና በአዲስ አበባ በስሙ የተመዘገበ የመኪና መገጣጠሚያ ያለው ሲሆን፤ ከመኪና ፈላጊዎች የማህበራት አባላት የተሰበሰበው ገንዘብ 1.2 ቢሊዮን ብር ሳይሆን 41 ሚሊየን ብር ነው፡፡" ብለዋል፤ ሥራ አስኪያጁ፡፡

ኦክሎክ ከአባላቱ ገንዘብ ሰብስቦ ምንም መኪና አላመጣም የሚለውም ትክክል አይደለም ያሉት አቶ ታመነ ካሣሁን፤ የማህበሩ አባላት እስካሁን 800 ተሽከርካሪዎችን በካሽና በብድር ወስደዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሽማግሌዎቹ ቡድንም እኒህን የተሳሳቱ መረጃዎች በራሳቸው መንገድ አጣርተው፣ እውነታው ላይ መድረሳቸውን በራሳቸው አንደበት ያረጋገጡ ሲሆን፤ እርቅ ላይ የተደረሰውም ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በእርቅ መፈታቱን ያደነቁ የተለያዩ ማህበራት ተወካዮች፤ ሌሎችም በክስ ሂደት ላይ ያሉ ማህበራት ችግራቸውን በእርቅ የሚፈቱበት ሁኔታ ይመቻች ዘንድ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ከኦክሎክ ሞተርስ ጋር የእርቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው ከ60 ማህበራት ውስጥ 16 ያህሉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ20 ዓመት በፊት የተመሰረተውና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማራው ኦክሎክ ሞተርስ፤ በትግራይ መቀሌ ከተማና በአዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ባስገነባቸው የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎቹ ከ16 በላይ የተለያዩ ሞዴል ተገጣጣሚ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስመጣት እየገጣጠመ ለደንበኞቹ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

Read 607 times