• 2.5 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል ተብሏል
በአጠቃላይ 2.5 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የተነገረለት "እንግዱ" የተሰኘ ልብ አንጠልጣይ ትሪለር ይዘት ያለው አዲስ ፊልም፣ ከመጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
በሳዳም ነጌሶ ተደርሶ ዳይሬክት የተደረገው ፊልሙ፤ በልባም ፒክቸርስ ተዘጋጅቶ በሳዳም ፊልም ፕሮዳክሽንና በሶሎዳ ስቱዲዮ መቅረቡ የተነገረ ሲሆን፤ የ1 ሰዓት ከ32 ደቂቃ እርዝማኔ ያለው ነው ተብሏል፡፡
ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በፊልሙ ዙሪያ ፕሮዲዩሰሮቹና ተዋናዮቹ በሪፌንቲ ሞል (ቦሌ ቡልቡላ) ለሚዲያ ባለሙያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሰጥተዋል፡፡
"እንግዱ" የተሰኘውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከ8 ወር በላይ እንደፈጀ የተገለጸ ሲሆን፤ በፊልሙ ላይ ከ35 በላይ ታዋቂና አጃቢ ተዋናዮች እንደተሳተፉበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከፊልሙ መሪ ተዋናዮች መካከል፡- አንጋፋው ተዋናይ ሰለሞን ሙሄ፣ ኤደን ገነት፣ ታዋቂው ኮሜዲያን ደረጄ ሀይሌ፣ ጌዲዮን ፍቃዱና አሰፋ ገ/ሚካኤል ይገኙበታል፡፡
የፊልሙ ቀረጻ እዚሁ አዲስ አበባ የተከናወነ ሲሆን፤ ከ65 በመቶ በላይ በሪፌንቲ ሞል ህንጻ ላይ መቀረጹ ተነግሯል፡፡
እንግዱ የተባለው ገጸባህርይ 7 ዓይነት ማንነቶችን ወይም ሰብዕናዎችን የያዘ መሆኑ ፊልሙን ለየት ያደርገዋል ያለው ደራሲና ዳይሬክተሩ ሳዳም ነጌሶ፤ የዚህን መነሻ ሃሳብ የወሰደው እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም ከተሰራው Split የተሰኘ የሆሊውድ አስፈሪ ትሪለር ፊልም መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በፊልሙ ላይ እንግዱን ሆኖ የተወነው ጌዲዮን ፍቃዱ በሰጠው አስተያየት፤ "ስክሪፕቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነበው ልሰራው የማልችለው ነበር የመሰለኝ፡፡ በአንደ ሰው ላይ ሰባትና ከዚያ በላይ ማንነቶችን ማሳየት ፈታኝ ነበር፡፡ እንደምንም ግን ተወጥቼዋለሁ" ብሏል፡፡
"እንግዱ" ፊልም በትላንትናው ዕለት በዓለም ሲኒማ ለአርቲስቶችና ለፊልሙ ቤተሰቦች ለዕይታ የበቃ ሲሆን፤ መጋቢት 5, 6 እና 7 እንዲሁም መጋቢት 12, 13 እና 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሁሉም ሲኒማ ቤቶች በይፋ እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡