Thursday, 13 March 2025 20:28

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከዩኤን ውመን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከዩኤን ውመን ጋር የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ “ይረዳል” የተባለለትን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። በባንኮች ላይ በአመራርነት የሚሰሩ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ስለመሆኑም ተገልጿል።

ዛሬ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የዩኤን ውመን የኢትዮጵያ ተወካይ ሲሲል ሙካሩባጋን ጨምሮ፣ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተገኝተዋል። በመድረኩ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ከመነሻ ካፒታል እና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከማግኘት አንጻር የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚገጥማቸው ተጠቅሷል።

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በሴቶች አቅም ግንባታ፣ ዕኩል ተጠቃሚነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛ ስራዎች እንደተሰሩ ተገልጿል። ይሁንና ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ሴቶች በስራ ፈጠራ እና ኢኮሚያዊ ተሳትፎ ላይ ጠንክረው እንዳይወጡ እንዳደረጋቸው ተነግሯል።

በመድረኩ ላይ ከቀረበው ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በኢትዮጵያ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ለሴቶች ብድር የሚሰጡት ከ13 በመቶ ባነሰ መጠን ነው። ይህም ከወንዶች እንጻር ሲመዘን “አናሳ ነው” ተብሏል።

በተጨማሪም፣ አሁን በስራ ላይ በሚገኙ ባንኮች ላይ በሃላፊነት እየሰሩ ያሉ ሴቶች 12 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የሴት ሃላፊዎችን ብዛት ከወንድ አቻዎቻቸው አንጻር 25 በመቶ ገደማ እንዲደርስ ካስቀመጠው ግብ አንጻር አናሳ መሆኑን ተጠቁሟል።

በዚህም ተጨባጭ ዕምርታዎችን የሚያሳዩ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል። እንዲሁም ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ካጠናከሩ፣ አጠቃላይ መብቶቻቸውን ማስጠበቅ “ይችላሉ” ተብሏል።

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሚተገብራቸው፣ በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ አቶ በግዱ ሃይለመስቀል የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ባንኩ ከUN Women ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ “ይረዳል” የተባለለት ይህ የመግባቢያ ሰነድ በባንኩ የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ምክትል ቺፍ ኦፊሰር ወይዘሮ ሐረገወይን አምሳለ እና በUN Women የኢትዮጵያ ተወካይ ሲሲል ሙካሩባጋ አማካይነት ተፈርሟል።

Read 315 times