Thursday, 13 March 2025 20:34

"የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎት ማዳበርና ማበረታታት ነው"

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የአፍሪካ ወጣቶች የሮቦቲክስ ፈጠራ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት 3ኛው የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በታላቅ ድምቀት ተከፍቷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ፣ ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ ለማብቃት ወሳኝ ምዕራፍ ነው" ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለወጣቶች የቴክኖሎጂ ክህሎት እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
የኢትዮ ሮቦቲክስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይክረም መኮንን በበኩላቸው፤"ከዛሬ መጋቢት 4 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፈጠራ ችሎታቸው ይወዳደራሉ፤ ውድድሩም በዲዛይን፣ በኢንጂነሪንግና በአውቶኖሚ ኮዲንግ ላይ ያተኩራል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎት ማዳበርና ማበረታታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ያሉት አቶ ሰናይክረም፤ የውድድሩ አሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማትና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተፈረመ የምስክር ወረቀት ይበረከትላቸዋል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ "እንደ አህጉር መጪውን ትውልድ የሚያጎለብት የዲጂታል ቴክኖሎጂና የምህንድስና ትምህርት ባህል መፍጠር ላይ ማተኮር አለብን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የውድድሩ አሸናፊዎች ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ይፋ የሚደረጉ ሲሆን፤ ለፍጻሜ የሚበቁ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
Read 585 times