የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “በትግራይ ክልል የሚፈጠረው ችግር ኢትዮጵያን የማተራመስ አቅም አለው” በማለት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ የፌደራል መንግሥቱ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ደጋፍ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡
ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንቱ፣ "የእኔ ፍላጎት ጦርነትን ማስወገድ ነው፡፡ ሌላ ጦርነት ማካሄድ ሳይሆን ጦርነትን ለማስወገድ የሚያስችሉ ሁሉም አስፈላጊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው” ሲሉም ተደምጠዋል።
"እዚህ ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትን ማስቀረት መቻል ስላለብን፣ እንዲሁም ሌሎች ጠላቶች ገብተው ይሄን ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን ዕድልም መከልከል ስላለበት፣ ፌደራል መንግስት ለዚህ ‘በቂ ነው’ የሚለውን ድጋፍ መስጠት ‘አለበት’ የሚል ዕምነት አለኝ" ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በትግራይ ክልል የሚፈጠረው ችግር ኢትዮጵያን የማተራመስ አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል። አክለውም፤ “ከኤርትራ ጋር ግንኙነት መፍጠር ካስፈለገ፣ የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎች በመካድ አይደለም የሚፈጠረው” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በዛሬ መግለጫቸው፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ለማፍረስ “እየተደረገ ነው” ያሉት እንቅስቃሴ በፍጥነት እንዲገታም ጥሪ አቅርበዋል።