ከዕለታት አንድ ቀን አያ ጅቦ አራት ልጆቹን ማለትም መዝሩጥን፣ ማንሾለላን፣ ድብልብልንና ጣፈጦን ይዞ በሌሊት መንገድ ይሄዳሉ፡፡ እየተጓዙ ሳለ ድንገት ከቤቷ የወጣች አህያ ያገኛሉ፡፡
ይሄኔ አባት ጅብ፤
“ልጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ በጣም አርጅቻለሁና፣ ይቺን አህያ እኔ ነኝ የምበላት! እናንተ ራቅ ራቅ ብላችሁ ትጠብቁኛላችሁ” አለ፡፡
ይኔ መዝሩጥ፤
“አባዬ ኧረ አንድ ብልት እንኳን አጋራን?” ይለዋል፡፡
“አይሆንም! ምንም አላቀምስህም” ይላል አባት፡፡
ይሄኔ ማንሾለላ ይነሳና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይላል፡፡
አያ ጅቦም፤ “እንካ ጆሮዋን ብላው” ይለዋል፡፡
ቀጥሎ ድብልብል ይመጣና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይለዋል፡፡
“አንተ ሽሆና ይደርስሃል” ይላል አያ ጅቦ፡፡
ቀጠለና ጣፈጦ ጠየቀ፡-
“አባዬ የእኔንስ ነገር ምን አሰብክ?” አለ፡፡
“አንተ ቆዳዋን ካገኘህ ያጠግብሃል” አለ፡፡
ልጆቹ አባታቸው አህያዋን ዘርጥጦ ጥሎ ሲበላ ዘወር አሉ፡፡
አያ ጅቦ ዋና ዋናውን የአህያዋን ብልት እንደበላ፤ ድንገት የአህያዋ ጌታ ሲሮጥ መጣ፡፡
አያ ጅቦ ፈርጥጦ መውጫ የሌለው የጫካ ጥግ ውስጥ ገብቶ ይሰረነቅና እየጮኸ ልጆቹን ይጠራል፡፡ ልጆቹ ቀርበው ወደ ጫካው ይጠጉና፤
“አባታችን ምነው ትጮሃለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
አያ ጅቦም፤
“አድነኝ ልጄ መዝሩጥ?” ይላል፡፡
መዝሩጥም፤
“አባቴ ምን ሰጥተኸኛል እንደበላህ እሩጥ!” ይለዋል፡፡
”አድነኝ ልጄ ማንሾለላ!” ይላል አያ ጅቦ፡፡
“ምን ሰጥተኸኛል ካንድ ጆሮ ሌላ!?” ይለዋል ማንሾለላ፡፡
“አድነኝ ልጄ ድብልብል?”
“አይ አባት! ሸሆና ለማን ውለታ ይሆናል?!”
ቀጥሎ አያ ጅቦ ጣፈጦን ጠየቀ!
“አድነኝ ልጄ ጣፈጦ?!”
“ማን የጎረሰውን ማን አላምጦ?” አለ ጣፈጦ፡፡
መላወሻም አጋዥም ያጣው አያ ጅቦ፤ እዚያው ተወጋና ሞተ፡፡
* * *
ዛሬ እኔ ነኝ ዋናው ጅብ ማለት አይሠራም! ቀድመው ያላሰቡበት ግለኝነትና ሆዳምነት ምን ላይ እንደሚጥለን አለማሰብ የማታ ማታ ያላጋዥ ያለመጠጊያ ያስቀራል፡፡ ከካፒታሊዝም ምርኮኝነታችን ጀምሮ ስግብግብነት፣ በዝባዥነት፣ ዘረፋና ግፍ ይበረከታል፡፡ ያላየነው የገንዘብ ትርፍ ማህበራዊ መልካችንን ያዥጎረጉረዋል፡፡ እንኳን ሊያተርፈን ራሳችንን ያጎልብናል፡፡ “አድነኝ ልጄ እገሌ” ቢባል ምላሽ አይኖረውም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ መግባባትና መስማማት ያለብን ሰዓት ነው፡፡ ስለ ሃይማኖት መግባባታችን፣ ስለ አንድነት መግባባታችን፣ ስለ ድንበር መግባባታችን፣ ስለ ዓለማቀፍ እንቅስቃሴዎች መግባባታችን--- እጅግ አስፈላጊና ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅም ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶችን በነፍጥ ለመፍታት መሞከር የሚያስከትለውን አሰቃቂ ጥፋትና እልቂት አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ከስህተታችን አሁንም የተማርን ግን አይመስልም፡፡ ለሁለት ዓመት በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የከረመችው ትግራይ አመራሮች፣ አሁንም ለዳግም ጦርነት እየተንደረደሩ መሆኑ ያስፈራልም፤ ያስደነግጣልም፡፡ በአማራ ክልል ከታጣቂዎች ጋር እንደ ዘበት የተጀመረው ጦርነት በጊዜ በውይይት አለመቆሙ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ በኦሮሚያም ከታጣቂ ቡድን ጋር ፍሬያማ ድርድር ማድረግ አለመቻሉ ህዝቡን ለእልቂትና ለመከራ እየዳረገው ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ የሳሱ ድንበሮችና መንግሥት አልባ አገራት ወደ አሰቃቂ እልቂት ሊያመሩ እንደሚችሉ ከበቂ በላይ ማሳያዎች አሉ፡፡ እነ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሊቢያ ወዘተ-- ለመነሻ አስረጅነት የቆሙ ተጨባጭ ምሳሌዎቻችን ናቸው! ነገ በየአገሩ ይኸው ሁኔታ ላለመከሰቱ ምንም አስተማማኝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዋስትና የለም፡፡ በትናንሽ የፖለቲካ አታካራ ተሞልተን፣ ትናንሽ ሙሾ በማውረድ ጊዜያችንን ከምናባክን፣ ትልቁን የዓለም አቀፍም አገር አቀፍም ስዕል (The Bigger Picture) የምናይበትን ዐይናችንን እንክፈት፡፡ ምዕራባውያን፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ጥንታዊ ታሪክ ያላቸው አገራት (ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና አሁን ደግሞ የእኛው አገር ኢትዮጵያ) ላይ ያነጣጠሩት ያለ ነገር አይደለም፡፡ ባህል የሌላቸው ባለ ባህሎቹን እየገደሉ ነው፡፡ የቅርቦቹ ሶማሊያና ሊቢያ በመንግሥት- አልባ ሁኔታ ውስጥ መሆን፣ በማን ይሁን በማን ለመጠቃታቸው ሰፊ በር ከፍቷል፡፡
ወደ ሊቢያ በጣሊያን አዛዥነት ስለዘመተው ያለዕዳው ዘማች የኤርትራ ወጣት (ደራሲው አበሻ ይለዋል) እንዲህ የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ ስለ ሊቢያ በረሀ ነው፡-
“የመሸበር ስሜት፣ ሐዘን፣ ተስፋ ቢስነትና ፀፀት ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ የበረሀው ስዕል አሰቃቂ ነው፡፡ አንዲት ዛፍ አትታይም፡፡ አንዲትም የሳር አገዳ የለችም፡፡ የውሃ ነገርማ ባይነሳ ይሻለዋል፡፡ ወደየትም አቅጣጫ መንቀሳቀስ አይታሰብም፡፡ ግራ፤ ቀኝ፤ ወደፊት፣ ወደኋላ፣ ወደየትም መሄድ አይቻልም ምክንያቱም የትም ይሁን የት ህይወት በአሸዋ ተከባ ነው የምትገኘው፡፡ በየትም ቢዞሩ ጠጠር ኮረት ድንጋይ፤ እና የአቧራ ክምር!
ያ በረሀ እንደባህር ሰፊ፤ ግን በጥላቻ የተሞላ! ባህር ውስጥ ቢያንስ ዓሣ ማየትና የማዕበል ድምጽ ማድመጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ሊቢያ በረሃ ግን አንዲትም ወፍ አትዘምርም፡፡ አትበርም፡፡ ያ ክፍቱ ደመና አልባ ሰማይ የጋለ ምድጃ ነው፡፡ በዚያ ጠራራ ንዳድ ውስጥ ያለ ሰው፣ ያ መሬት፣ የህይወት ይሁን የሞት መለየት ይሳነዋል፡፡ ይህን መሬት ከአረንጓዴው፣ ከንፋሳማው እና ከለሙ የኢትዮጵያ ምድር ጋር ማነፃፀር ከንቱ ድካም ነው! የሲዖልና የገነት ነው ልዩነቱ!?”
ስለ አበሻ የጦርነት ብቃት የሚገርም ትንተናም አለው- በሊቢያ በረሃ፡- አበሻ ፣ ጣሊያንና አረብ የውጊያ መንፈስ ምን ይመስላል?
ለአበሻ፤ ጦርነቱ ምንም ውጤት ያስከፍል ወደፊት መግፋት ነው፡፡ (ግፋ በለው እንደማለት) በጣሊያኖች፤ አዛዥህ እንዳለህ ተዋጋ ነው፡፡ ጠላት ግንባር ቢፋጠጥህም ካልታዘዝክ አትተኩስም፤ ካልታዘዝክ ብትታረድም ፀጥ በል ነው!
ለአረቦች ወደ ጠላትህ ፈጥነህ ሩጥ፡፡ ሁኔታው የማያዋጣ ከመሰለህ ነብስህን ለማዳን ፈርጥጥ ነው፡፡ የየተዋጊውን ባህሪ ለእኔ ብሎ መስማት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጊዜው አስጊ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችንን በቅጡ እናስተውል፡፡ ሩቅ የሚመመስሉንን ዕጣ ፈንታ ስናይ፣ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” እንበል፡፡ “ጎረቤትህ ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ማለት የአባት ነው!!

