Saturday, 22 March 2025 12:06

አፈኛ ሴት፤ የአምስት ዳኛ ሚስት ነኝ፤ ትላለች (አዋቄ ሞሽሪያ ተ እቸሹ እራሻ መቾ ገውሱ) - ወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(11 votes)

አንዳንድ ተረቶች በአንድ ወቅት አልደመጥ ሲሉ፣ በሌላ ወቅት ተደግመው መነገራቸው ግድ ይሆናል፡፡ የሚከተለውም እንደዚያው ነው፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ሦስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሰፊ መስክ ላይ እየጋጡ ሳሉ፤ ሦስት ጅቦች የሚበላ ፍለጋ ሲዘዋወሩ ያገኙዋቸዋል፡፡
ጅቦቹ ገርሟቸዋል፡፡
አንደኛው ጅብ፤
“እነዚህ አህዮች እንዴት ቢጠግቡ ነው በእኛ ሰዓት፤ በእኛ ግዛት እንደዚህ ተዝናንተው የሚግጡት?”
ሁለተኛው ጅብ፤
“እውነትም የሚገርም ነው፡፡ የተማመኑት ነገር ቢኖር ነው እንጂ እንዲህ ያለ ድፍረት አይፈጽሙም ነበር”
ሦስተኛው ጅብ፤
“ታዲያ ለምን ችሎት ተቀምጠን አንፈርድባቸውም?” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡
አህዮቹን ከበቡና ተራ በተራ ሊጠይቋቸው ተሰየሙ፡፡
የመጀመሪያዋን አህያ ጠሩና ጠየቋት፡፡ የማህል ዳኛው ነው የሚጠይቃት፡፡
“እሜቴ አህያ፤ ለመሆኑ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት፣ በጠፍ ጨረቃ፣ እንዲህ ዘና ብለሽ የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው?”
እሜቴ አህያ፤
“አምላኬን፣ ፈጣሪዬን ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ግፍ የሚሰራን አምላኬ ዝም አይለውም፡፡ መአት ያወርድበታል፡፡”
የማህል ዳኛው ጅብም፤
“መልካም ሂጂ፡፡ ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት”
ለሁለተኛዋ አህያም ጥያቄው ቀረበላት፤
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት
ፍንጥዝጥዝ ብለሽ የምትግጪው?”
ሁለተኛይቱ አህያም፤
“ጌታዬን፣ አሳዳሪዬን ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ጥቃት የሚያደርስን ማንምም ቢሆን ጌታዬ አይምረውም፡፡ ይበቀልልኛል ብዬ በማመን ነው” ስትል መለሰች፡፡
ማህል ዳኛው ጅብ፤
“መልካም፡፡ አንቺም ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት” አላት፡፡
ሦስተኛይቱ ቀረበች፡፡
ማህል ዳኛ ጅብም፤
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው ይሄ ሁሉ መዝናናት?” አላት
ሦስተኛይቱ አህያም፤
“እናንተን፣ እናንተን፣ የአካባቢውን ገዢዎች ተማምኜ ነው ጌቶቼ”
ዳኛውም፤
“መልካም፡፡ ሁላችሁም ፍርዳችሁን ጠብቁ” አሉና ሸኟት፡፡
ዳኞቹ መምከር ጀመሩ፡፡
ግራ ቀኝ ዳኞች አስተያየት ከሰጡ በኋላ፣ የማህል ዳኛው ጅብ እንዲህ አሉ፡-
“የመጀመሪያዋን ብንበላት እንዳለችው አምላክ አይለቀንም፡፡ ይበቀልላታል፡፡ ሁለተኛዋን ብንበላት ምናልባት አሳዳሪ ጌታዋ ተከታትሎ ያጠፋናል፡፡ ይቺን ሦስተኛዋን እኛን የተማመነችውን ብንበላት ማናባቱ ይጠይቀናል!?”  ሲል መሪ - ሀሳብ አቀረበ፡፡
ሁለቱ ጅቦች ባንድ ድምጽ፤
“እውነት ነው፡፡ እኛን የተማመነችውን እንብላት!” አሉ፡፡
እነሱን የተማመነችው ላይ ሰፈሩባት፡፡
***
የጌቶች አስተሳሰብ ምን እንደሚመሰል ተገዢ ወዳጆች ማወቅ አለባቸው፡፡ ሎሌነቱን በቅጥ አለመያዝ የመጨረሻውን ቀን ከማፋጠን አያልፍም፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” የሚለውን ተረት፣ በአፉ የሚንጣጣ ሁሉ በጊዜ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ መጨረሻው፤ “ያመኑት ፈረስ ይጥል በደንደስ” ነውና፡፡ “እናቴን ያገባ  ሁሉም አባቴ ነው” ለሚሉ የዋሀን ሁልጊዜ ፋሲካ ሊመስላቸው ቢችልም፣ ለሁሉም ጊዜ አለውና “ምነው ምላሴን በቆረጠው” የሚያሰኝ የፍርድ ቀን እንደሚኖር አሌ አይባልም፡፡ “እንብላም ካላችሁ እንብላ፣ አንብላም ካላችሁ እንብላ” በሚል ጅባማ ፍልስፍና ውስጥ መበላላት መሪ መርሀ-ግብር መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡
“ለጋማማ አህያም ጋማ አላት
አያስጥልም እንጂ ጅብ ሲዘነጥላት” ሲባል የከረመው ያለ ነገር አይደለም፡፡
“እነሆ ብዙ ዘመን አለፍን፡፡ ከሁሉም የተረፈን ብዙ ምላሶችና እጅግ ጥቂት ልቦች ናቸው” ይላል ሲጆርጅ የተባለው ፀሀፊ፡፡ በሀገራችን በቅንነት ሃሳብ የሚሰጡና በሎሌነት ሀሳብ የሚሰጡ መለየት አለባቸው፡፡ “ውሸት አለምን ዞሮ ሊጨርስ ሲቃረብ እውነት ገና ቦት ጫማውን እያጠለቀ ነው” መባሉ በምክንያት እንጂ በአቦ - ሰጡኝ አይደለም፡፡ በየአገሩ፤ የንጉስ አጫዋቾች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ የጋራ ባህሪ ግን አላቸው - ንጉሱ ሲያስነጥሱ ማስነጠስ፡፡ አድር ባይነት፡፡ በመካያው ራሱ አድርባዩ ማንነቱ ይጠፋበትና፤ “የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ” ማለት እንኳ ይሳነዋል፡፡ “ነገር አንጓች እንኳን ለጌታው ለራሱም አይመችም” ነውና ፍፃሜው አጓጉል መሆኑ እሙን ነው፡፡
የትእዛዝ ሁሉ ጉልላት ለህሊና መታዘዝ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ ህሊናውን ሲክድ አታላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ብልጥ ለማኝ፤ “ጌታዬ ጌታዬ፣ አምና የሰጡኝን ልብስ አምስት ዓመት ለበስኩት” እያለ ይኖራል፡፡ በእውቀት ያልተደገፈ ድፍረት፤ የህሊና ማጣት ምርኩዝ ነው፡፡ ወትሮም “መራዡ ተኳሹ” ሲል የኖረ፣ “በራዡ ከላሹ” ማለት ከጀመረ ሁለተዜ ጥፋት ነው፡፡ ሀገራችን አያሌ አድር - ባይ አይታለች፡፡ ለሀገራችን ጎታቿም አጥፊዋም “አሾክሹዋኪው” ነው፡፡ ከታሪክ መማር እርም በሆነባት አገር፣ ቀለሙን እየለዋወጠ አድር - ባይ  ሁሉ እየመጣ፤ “እንቅፋት በመታው ቁጥር ቲዎሪ ድረስ (ያውም እውነተኛ ቲዎሪ ካለው) እያለ፤ “መንገድ ባስቸገረው ቁጥር “መመሪያ ማሪኝ” እያለ ህሊናውን እየሸጠ ይኖራል፡፡ ልባም አይደለምና አፍ ያወጣል፡፡ ምላሹ እየረዘመ፣ አንጎሉ እየጨለመ ይሄዳል፡፡ አበው “ከመሃይም ምላስ ይሰውረን” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ማህታማ ጋንዲ እንግሊዝን “በመጨረሻ ባዶህን ትወጣለህ!” ማለቱን አንርሳ፡፡
“ቅዳሴ ሲያልቅበት ቀረርቶ አከለበት” እንዲሉ፣ በምላሱ የሚተዳደር ሰው፣ ውሸት ማብዛቱ ግዱ ነው፡፡ እውቀተ - ቢስ መሰረቱ ለእውነት ረሃብ ያጋልጠዋል! “አፈኛ ሴት፣ የአምስት ዳኛ ሚስት ነኝ፤ ትላለች” የሚለው የወላይታ ተረት ኢላማ ይሆናል፡፡



Read 6913 times