Saturday, 22 March 2025 12:59

ጊዮርጊስ ታዛ ስር

Written by  መሀመድ ነስሩ
Rate this item
(9 votes)

ሰንበትን በዚያ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ያያቸዋል፡፡ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ስር፤ መናኛ ልብስ ለብሰው ባነጠፉት ጨርቅ ላይ ሲመፀወቱ፡፡
… ፈፅሞ ያላሰበው ቦታ ላይ ነው ያያቸው፤ ኮከብ ቆጣሪ ሊገምተው የማይችል የመሰለው ቦታ ላይ፡፡ ለማመን ተቸግሮ ነበር፡፡ ግንባራቸው ላይ የተጋደመው ጠባሳ ነው ጥርጣሬውን የከላት፡፡ እንደ መንገድ ላይ የትራፊክ መስመሮች ዘና ብሎ የተጋደመው ጠቋራ ጠባሳ! …
ሰውየውን የማወቅ ፍላጎቱ ጣራ ነካ፡፡ አዲስ ነገር በማወቅ የሚያገኘው ደስታ፣ ከወይን ጠጅ በላቀ ነብሱን ያስተፈስይለታል፡፡ ከሴት ገላ በላይ ውስጡን ያሞቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ “የልመና ሙያ” ላይ ሊያደርግ ላሰበው ጥናት ጥሩ መነሻ እንደሚሆኑት አመነ፡፡ ከቀናት በኋላም ዘባተሎ ለብሶ፣ ፀጉሩን ከማበጠሪያ አኳርፎ፣ ለተበጣጠሰ ሸራ እግሩን ድሮ… ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አቀና፡፡
… ከሰውየው አጠገብ ተቀመጠ፡፡
 “አዲስ ትመስላለህ … ጃል?!”
“አዎ… አባት !”
“ፊትህ የመከራ በትር ያረፈበት አይመስልም፡፡ ምን ገጠመህ ታዲያ ልጄ?!”
ያጠናውን  ቃለ ተውኔት መጫወት   ነበረበት፡፡
“ቤተሰቦቼ አልቀዋል፡፡ የምኖርባት ቤት አባቴ የባንክ እዳ ነበረበትና መንግስት ወረሰው፡፡ እንዳልሸከም የጀርባ ህመም አለብኝ፡፡ ምርጫ ሳጣ ልለምን በቃሁ አባቴ፡፡”
ፊቱ የሀዘን ጥላ አጠላ፡፡
…በሀዘኔታ ተመልክተውት ፊታቸውን ወደ መንገደኛ መለሱት፡፡
ወጪ ወራጅ …. ሂያጅ መንገዱን ሞልቶታል…. ጥጋቱን የኔ ቢጤዎች ተደርድረዋል፡፡
ቅዳሴ ይሰማል፡፡ መንገደኞች ደፋ ቀና እያሉ ያልፋሉ፤ እየተሳለሙ፡፡ ምእመናን ነጠላ እንደተከናነቡ በሩን ይስማሉ፡፡
ገሚሶቹ ወደ ውስጥ ዘልቀው ታድመዋል፡፡
… ናሆም አዛውንቱን አስተዋለ፡፡ የተጎሳቆለ ሰውነት የላቸውም፡፡ ጠይም ፊታቸው በችግር እሳት የተጠበሰ አይደለም፡፡
“አባት …”
“አቤት ልጄ”
“እንዴት ነው ስራው?”
“ይመስገን ለፈጣሪ…. ሰው ደግ ነው ይመፀውታል፤ የእኛ ሰው ሀይማኖተኛ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሄር ልቡ አድሯል፡፡ የተቸገረን መርዳት ልማዱ ነው፡፡ ይመስገን ለፈጣሪ ልጄ ይመስገን!”
ናሆም ስሜታቸውን ከገፅታቸው ለማጥናት እየሞከረ ያዳምጣል፡፡
እኝህ ሰው ዛሬ ያሉበት ቦታና ከቀናት በፊት የታዩበት ቦታ እጅግ የተራራቁ ናቸው፡፡ እርቀታቸው በሰማይና በምድር ሊመሰል ይችላል፡፡
ሆቴል … ጊዮን ሆቴል ሙሉ ልብስ ለብሰው ከረባት አስረው… ከሁለት ወጣቶች ጋር ደብሊው ቢ ኤም የቤት መኪና እያሽከረከሩ ሲወጡ ነበር ያያቸው፡፡
አይኖቹ  የድሮ አይኖቹ ነበሩ … ሰውየውም እራሳቸው፡፡
“ይቅርታ አድርጉኝልኝና አባቴ…”
“ምነው ልጄ?!”
“ምን ያህል ጊዜ ሆነዎ?”
“ምኑ?”
“እዚህ ቦታ መቀመጥ ከጀመሩ …”
የውሃ ጠብታ ድንጋይ እንዲሰብር…ቀስ በቀስ ነው…. የሚስጥሩን ቅርፊት መስበር የፈለገው፡፡ ለዘብተኛ ሆኖ በልዝብት ቃላት ወደ ግቡ እያዘገመ ነው፡፡
“ይመስገን ፈጣሪ፤ ይኸው ሦስተኛ አመቴ መጣ፡፡” ፊታቸውን አነበበ፡፡ ኩራትና ትካዜ የተዳቀሉበት መጢቃ ስሜት!
“ቤተሰብ ልጆች የለዎትም?”
“አረ አለኝ ልጄ… ምን የመሳሰሉ ሁለት ሸበላዎች አሉኝ…”
ቃላት እየመረጠ … ጥያቄዎችን ከመልሶቻቸው ስር ማሶክሶክ ቀጠለ፡፡
“… አሀ… ታዲያ ከዚህ ከመጽዋት የሚገኝ ገንዘብ ከነቤተሰብ ያኖራል?!”
“እሱስ አዎ! የእኛ ሰው ቸር ነው ብዬህ የለ!?”
“እህ… ታዲያ ልጆችዎ ምንም አይሰሩም?”
መልስ ለመስጠት  ዘገዩ፡፡
“አባቴ!”
“አቤት ልጄ”
“ሰምተውኛል?”
 “እ?”
“ልጆችዎ አይሰሩም?”
“… ይሰራሉ እንጂ … ይመስገን ለፈጣሪ፤ የሁለት ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች ናቸው፡፡”
“ምን አሉኝ?”
ሰምቷል፡፡
በደመነፍስ ነው መጠየቁ፡፡
“ሁለቱም ልጆቼ ጥሩ ስራ አላቸው፡፡ ስራ አስኪያጆች ናቸው…. ክብሩ ይስፋ ለመድሀኒያለም!”
“ምን ድርጅት ውስጥ ነው የሚሰሩት?”
“የግል ድርጅት ነው ልጄ”
“የማን ናቸው ድርጅቶቹ?”
“የኔ!”
የናሆም ግርምት እንደ እርችት ወደ ሰማይ ተተኮሰ፡፡
“የርስዎ?!”
“አዎ ልጄ”
መደመሙን መደበቅ አልቻለም፡፡ ድብን ካለ ገጠር ወጥቶ መሀል ከተማ እንደተጣለ ባላገር ድንብርብር አለው፡፡ የአምልኮ ስርአቶችን በቅጡ ሳይረዳ ቤተ አምልኮ እንደገባ አዲስ አማኝ ብዥ አለበት፡፡
“እና… እንዴት…ለምን?”
መጨረስ ከበደው፡፡
“እንዴትና ለምን ትለምናለህ ልትለኝ ነው?”
“ገብቶዎታል አባቴ”
“ሰፊ ታሪክ አለው፡፡” አሉ ጌሾ ወቅጠው እንደጋቱት ሰው ፊታቸውን አቆምጭጨው፡፡
“እባክዎን ባጭሩ ያጫውቱኝ?!”
አትኩረው ተመለከቱት፡፡ ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት!
የተደበቀ ነገር በመግለጥ የሚረካ የሚመስል ትጉህ ወጣት!
“ይኸውልህ ልጄ… ልጆቼን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኜ ያሳደግኩዋቸው እኔ ነኝ፤ እናታቸው ነብስ በማወቂያቸው ዋዜማ ነው የሞተችብኝ! …”
በትካዜ ተዋጡ፡፡ በትዝታ መርከብ ተሳፈሩ፡፡ ከሰኮንዶች በኋላ፤
“…እንግዲህ በህይወቴ ያሉኝ እነዚህ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ዘመድ አዝማድ የለኝ ሚስት ያለኝ! ቢሆንም በልጆቼ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ታዲያልህ በአንድ የተረገመ ቀን ናዝሬት ቅርንጫፍ ላለው የንግድ ድርጅቴ ከመጀመሪያ ልጄ ጋር እቃ ጭነን ስንጓዝ የጭነት መኪናው ፍንግል አለ፡፡”
አሁንም በዝምታ ቡሉኮ ተጆቦኑ፡፡
“እሩቅ እንደሚያስቡ ያስታውቃሉ!” አለ ናሆም፡፡
“እኔ ይህች ጭረት ነበረች ጉዳቴ” ግንባራቸው ላይ የተጋደመውን ጠባሳ እየጠቆሙት፡፡
“ለክፉ አልሰጠኝም፤ ልጄ ግን ክፉኛ ተጎዳ፡፡ ለሳምንት ነብሱን አያውቅም ነበር፡፡”
መተከዙን አላቆሙም፡፡ አንድ አረፍተ ነገር ሲያገባድዱ አራት ነጥባቸው ቁዘማ ነው፡፡
“ሳሳሁ!... ሳሳሁ ልጄ... ጨነቀኝ፡፡ ይህን ልጄን ማጣት የአይኔን ብርሀን ማጣት ሆነብኝ፣ ልቤትን ማጣት ሆነብኝ እናም… ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳልኩ፡፡”
“ምን ብለው?”
“ልጄን በህይወት ካተረፍክልኝ ለአምስት አመት ያህል በሳምንት ሰንበት ለምኜ፣ ገንዘቡንም ለቤተክርስቲያኗ ገቢ እንደማደርግ ተሳልኩ!”
ወደ ላይ አንጋጠው፤
“ሞገስ ይብዛ ለአምላክ…. ልጄ ከነሙሉ ጤንነቱ ተነሳልኝ፡፡”
ናሆም በነገሩ እየተደመመ፤ “ደህና ይሁኑ” በማለት ቦታውን ለቀቀ፡፡ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ቢገጥመውም፣ ቤቱ የደረሰው “ለጥናቴ ጥሩ መንደርደሪያ አገኘሁ” ብሎ እያሰበ ነበር፡፡      
(አዲስ አድማስ፤ ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም)



Read 5370 times