ይኽ 11 ያህል የተኖሩና የተመነቡ ተረኮችን የያዘና ... በዚህ ዓመት በጠርሲዳ ከበደ ለንባብ የበቃ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ እንደ ዘመነኞቹ በብዛት የመደብ ልዩነቶች በየተረኮቹ የሚለውጥ ሳይሆን - አንድ ገጸ-ባህርይን በተለያዩ የስሜት ልዩነቶች በኩል ለማለት የተገነባ እጅጉን ‘እኔ’ ለሚል የመጀመሪያ መደብ ተራኪ ተጋልጥኦ ያለው ሥራ ነው።
እንደሚባለው ... አንድ ደራሲ - በተራኪው ገጸ-ባህርይና በራሱ የሕይወት ፣ የኑረት ተብሰልስሎት በኩል ከሚሾልኩ ተጽዕኖዎች ሙሉ ለሙሉ ያመልጣል ባይባልም እንኳን ያለው አቅም ቀላል የሚሉት አይደለም። ለዚህ እንደ ቅድመ-ምላሽ እንዲኾን ተሽቷል እንድንል የሚያደርገን - ከመጽሐፉ ርዕስ ሥር ‘የተኖሩ’ መባሉ - ከቅርብ ፣ ካዩት ፣ ከዳሰሱትና ከኖሩት (በእርግጥ ከዚህ ማምለጥ አይቻልም።) በቀረበ ሁናቴ ምናብ-አከል በኾነ መንገድ የተሰራ ሥራ መሆኑን ቀድመን ልብ እንድንል ያደርገናል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ - ያልሆነበት የሥነ-ጽሑፍ ጥጋት ወሽቀን ከመረዳት ቀድሞ የሚታደግ የብልህ ሰው መንገድ ነው።
ቅድመ ነገር - አርታዒው ባሰፈረው ማስታወሻ ላይ ትውልደ ፈረንሳዊቷን Ananis Nin’ን ‘In Favour of The Sensitive Man and Other Essays’ የሚል መጽሐፏን ጠቅሶ፤ ‘ጠርሲዳ’ በመጽሐፏ ውስጥ ባካተተቻቸው ተረኮች በኩል ‘ለምን እንደፃፈች’ ብንጠይቃት ከ Ananis Nin ጋር የተመሳሰለ ምላሽ ትሰጠናለች ይለናል።
‘ One Writer because one has to create a world in which one can live. ‘
ወይም ... [ ጋሽ ማሞ ውድነህ እንደተረጎሙት]
“አንድ ሰው ሌላው የሚኖርበትን ዓለም ለማመቻቸትና ለማጣፈጥ መጻፍ ይገባዋል።”
ሸጋ!!
እንዲህ ያሉቱ ጽሑፎች - ከኑረት ወደ ምናብ እጅጉን ተመንድገው የሐሳብና የቅርጽ ጣጣዎችን ተሻግረው የሚያንሸራሽሩ ለዘመኑ የሕይወት ምልልስ የቀረቡ ናቸው። ‘ነኝ ፤ ሆንኩ ...’ እና ‘ነው ፤ ናት ...’ ከሚሉ ሐረጋት የሚነሱት ተረኮቹ - የራስን እና ከራስ ወደሌላው ባሉ ተሃዝቦታዊ ሽክርክሪቶች የተሰፋው ይኼ መጽሐፍ ‘ነጋሪ’ ወይም የሆነውን [በኑረትም በምናብም ...] ተራኪ ነው ማለት ይቻላል።
ተራኪዋ - በየተረኮቹ በምትለዋውጣቸው ስሜታዊ አዘንብሎቶችና እነርሱንም ፍለጋ ከምትኼድባቸው ምልልሶች ጋር እንድንሽከረከር ማድረጉ የተቻላት ነው። ‘ውሃዬን ሸጬ ኮዳ የገዛኹለት’ በሚለው ተረኳ የመጀመሪያ መስመሮች ላይ ያለውን እንደምስክር እናምጣው።
“ ... ሕመ[ሜን] ... የሚያልፍ የሚያገድመው ነፋስ እንደ ስንጥር ይቆሰቁሰዋል። በነጋ በጠባ ቁጥር እንደ አዲስ እታመመዋለኹ ፤ ... “
ዘመናችንን ላይ ያረበበውን ጽልመታዊነት በእነዚህ ገለጻዎች ታሸክምልናለች።
‘ ... ነፋስ እንደ ስንጥር ... ‘
በእርግጥም ይኼንን ሐረግ የግጥም ስንኞች መሃል ባገኘው ‘እንዴት ያለ ነው!’ ብሎ ከማለፍ የተሻለ ትርጉም እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ።
እናም ... ይኼ መጽሐፍ ከቀደሙ ዓመታት በፊት ታትሞ ዛሬ ያገኘሁት ቢሆን ... የዚያን ዘመን ማህበራዊ ፣ ሥነ-ልቡናዊና በተለይም እንስታዊ የሆነ የሕይወትና የጊዜን ዕይታ ማሳያ እንደሚሆን እንደ አንድ ጥዑም ጥራዝ የምጠራው ነው።
* * *
ይኼንን መጽሐፍ ሁነኛ የሥነ-ጽሑፍ መጠሪያ ሥያሜ እንስጠው ብንል ተረኮቹን ‘Tales’ ልንላቸው እንችላለን። ‘Tales’ - ቀላል በኾነ የአተራረክ ዘይቤ - ድርጊቶችንና ውጤቶችን ከገጸ-ባህርያቱ እድገት ይልቅ እያጎላን ለመጻፍ የምንጠቀምበትመ አብዛኛውን ጊዜ ከአጭር ልቦለዶች (Short Stories) አነስ ብሎ የሚሰናዳ ነው።
ለምሳሌም ያኽል ... Charles and Mery Lamb ያሰናዱት ‘Tales from Shakespeare’ የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ታሪኮች ለዚህ አይነቱ የአጻጻፍ መንገድ ማሳያ ናቸው። ሌላው ይኼንን መጽሐፍ የተለየ የሚያደርገው - በየተረኮቹ መለዋወጥ ውስጥ ያለን የስሜት ባዳነት አለማስተናገዱ ነው።
በብዛት በአጫጭር ልቦለዶችና የግጥም ስብስቦች ላይ እንደሚስተዋለው፤ [በእርግጥ ለራሳቸው ዓውድ የተገባ አካሄድ ነው።] አንድን ታሪክ አንብበን ወደ ሌላኛው ታሪክ ለማለፍ የሚያዳግተን በተመሳሳይ የስሜትና የሐሳብ ዝግጁነት ውስጥ አለመቆማቸው ነው። የዚህ መጽሐፍ ተረኮች ግን ... ከ’ስናጥ ያላየኝ ስነጠር አሽትቶኝ ...’ ጀምረን ‘ባል በትዕዛዝ እንሰራለን!’ እስከሚለው ድረስ በተቀራራቢና በተዛማጅ የምናብና የስሜት ቅንፍ እያሰገረን ይቀጥላል።
ስለዚህ ... ሥነ-ጽሑፋዊ ፍሰቱ መልከኛ ነው ለማለት የሚያስችለንን ስልት ተጠቅማለች። በዚያውም እንደ አንድ ፍሰቱን እንደጠበቀ መጽሐፍ፣ በተረኮቹ ልዩነት የተቀመጠን Dynamics ብናነሳ ያስኼደናል።
እኒህ ከታች የምናመጣቸው የ’አንተ ዲዮቅልጥያኖሴ ፤ እኔ ፍልጥያባርኽ...’ እና ‘በኹለት እግር ሦስት ዛፍ’ መስመሮች የእኛን ሐገር ሁለት ቤተ-እምነቶችን መጽሐፍት [ማለትም - ገድል እና ሀዲስ ] ያካተቱ ገጸ-ባህርያቶች አሉባቸው። እንዲህ አይነቶቹ አገነባቦች - በቀጥታ ከእምነት መጽሐፍቶቹ አንቀጾችን ጠቅሶ - በእነዚያ ገጸ-ባህርያት በኩል ስብከታዊ አዘንብሎት ማሳየት፣ በእኛ ሀገር የተለመደ አይነት አካሄድ መሆኑ የምናስተውለው ነገር ነው ።
ይኼ መጽሐፍ ግን እንዲኽ አይነቱ አዝማሚያ በብዛት አይታይበትም። ገጸ-ባህርያቱ ከራሳቸው የኑሮ አረዳድና ከሕይወት ልምምዳቸው በስተቀር ተጽዕኖ መፍጠሪያ መንገድ አድርጋ አልተጠቀመችባቸውም፤ ጠርሲዳ። ለማሳያ ያኽል ...
“...እኔ ግን በትምህርታቸው መሃል ስሟን እንኳ መጥራት ደስ ሳይላቸው ያነሷት ንግስት ፍልጥራብያ ጋር ተተክያለኹ ፤ ንግሥትነቱ እና ፍቅሩን አብዝታ ብታገኝም አንዳች ጎድሏት አይኹኑ የኾነች ምስኪን ሴት ፤ እኔ እየኾንኩት እንዳለ። ከጥቂት ወራት በፊት ያነበብኹት ገድለ ፊቅጦር ውስጥ እየዋኘኹ ነው። የራሴን ቅናት ፈራኹት ፤ ንግስት ፍልጥራቢያ ላይ ሰፍሮ የነበረው ቅናት ልቤን የወረሰው መሰለኝ ፤ ያ ‘በላይዋ ቁጣን ተሞልታ እንደሚናደፍ እባብ ትወራጭ ጀመር።’ የተባለው ቅናቷ፤ ...”
‹አንተ ዲዮቅልጥያኖሴ እኔ ፍልጥራብያኽ...’ ገጽ 99
“...መላኢካው ጅብሪል (ዐ.ሰ) ለመጀመሪያ ጊዜ ወህይ (የአላህ ቃል) ይዞ የመጣ ጊዜ ከፍተኛ ፍርሃትና ጭንቀት ላይ ሳሉ ኸዲጃ(ረ.ዐ) ያጽናኗቸውን ማጽናናት ከደራሳነት ጊዜዬ ታስታውሳለች። ‘ ምንም አይነት ጭንቀት አይገባም ፤ የኸዲጃ ነፍስ በበላይነት የሚቆጣጠረው አምላክ እምላለኹ! የአላህ መልእክተኛ ነቢይ ተደርገኽ ለዚኽ ሕዝብ ሳትላክ አልቀረኽም። አንተ መልካም ሰብዕናን የተላበስኽ ፣ ለቤተሰብኽ ጥሩ ፣ በቃልኽ የምታድር ፣ እውነተኛና ዘወትር ለተቸገሩ ሰዎች የምትደርስ ለጋስ ሰው በመኾንኽ አላህ በምንም መንገድ አያሳፍርኽም!...”
‹በኹለት እግር ሦስት ዛፍ’ ገጽ 105 - 106
* * *
የመጽሐፉ የመጀመሪያ ተረክ የሆነው ‘ስናጥ ያላዬኝ ስነጠር አሽትቶኝ...’ - አንድ በራሷ ‘እኔ’ በምትለው ማንነቷ እና ‘የውስጤ ሴት’ ብላ በምትጠራት መካከል ባለ ውጥረት ውስጥ እየታገለች ያለችን ገጸ-ባህርይ የሚያሳየን ተረክ ነው።
ይኼንን ተረክ - በተለይ የገጸ-ባህርይዋን ውስጣዊ ተዋቅሶ የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች ከ Multiple Personality አሊያም ከሌላ አረዳዶች አንጻር የተሻለ ትንተና ቢሰጡበት እመኛለሁ።
እንደ መውጫ እንዲኾነን ... ከተኖሩትና ከተመነቡት ታሪኮች መሃል ‘እጅጉን ለስሜት የቀረቡ’ የተወሰኑ ያኽል መስመሮችን አስፍረን ... መጽሐፉ ከዚህ በተሻለ የሕይወትና የዕለት ተዕለት ድግግሞሻዊ መልክ ውስጥ አስገብተው የሚያብሰለስሉ ተረኮችን እንደያዘ መስክረን እንሰነባበት።
“... ደሕና እንደነበርኩ ነው ‘ማውቀው ቤት ስገባ ፤ ከሰዓታት በኋላ ግን ብዙ በማልቀሴ ጭንቅላቴን መሸከም ተሳነኝ ፤ ምላሴ ወደ ኋላ ሲመለስ ታወቀኝ፤ ሰውነቴ ለኹለት ቀን ምግብ ባለመብላቱ ዝሏል ፤ ዐይኖቼን የሚቆጠቁጥ ነገር ሰላም ነሳኝ። ፍራሼ ላይ ኩርምት እንዳልኩ እንቅልፍ ወስዶኛል። ስነቃ እኩለ ሌሊት አልፏል፤ እንደምንም ተነስቼ ነፍሴን ለማቆየት ያኽል ውሃ ጠጣኹ። ውሃው የተሰነጠቀ የደረቀ.መሬት ላይ የፈሰሰ ይመስል ውስጤ ሲጨስ ተሰማኝ። ...”
‹ውሃዬን ሸጬ ኮዳ የገዛኹለት’ ገጽ 73
“...እርሱ እኒኽን ምስኪን እናት ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ኹለት ሰዎች ሲሞቱባቸው ፤ አንዳቸውን እንኳን ለጥበቃው አያስቀርላቸውም ነበር ? ጨካኝ ነው።...”
‹ኹለት ትንታ ተኩል’ ገጽ 116
ደህና እንሁን!! መልካም ንባብ!

