በ2025 የመጀመሪያ 6 ወራት ዉስጥ በተለያዩ ሐገራት የደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ ዓለምን 135 ቢሊዮን ዶላር አከሰሩ።
ለኢንሹራስ ኩባንዮች የጠለፋ ዋስትና የሚሰጠዉ ስዊስ ሪ የተሰኘዉ ኩባንያ እንዳስታወቀዉ፤ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት ዉስጥ የተፈጥሮ አደጋ ያደረሰዉ ኪሳራ ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም።
መቀመጫውን ሱሪሽ-ስዊትዘርላንድ ያደረገዉ ኩባንያ እንደሚለው፤ ቃጠሎ፣ የዉኃ ሙላት፣ ርዕደ መሬትና መሰል አደጋዎች ካወደሙት ሐብትና ንብረት ዋስትና ወይም ኢንሹራስ የነበራቸዉ 80 ቢሊዮን የሚያወጡት ብቻ ናቸዉ።
ኢንሹራንስ ከተገባላቸዉ ንብረቶች ወይም የተፈጥሮ ሐብቶች ከፍተኛ ጥፋትና የኢንሹራስ ወጪ ያስከተለዉ ጥር ላይ ሎስአንጀለስ-ዩናይትድ ዉስጥ የደረሰዉ ቃጠሎ ነዉ - 40 ቢሊዮን ዶላር።
በተያያዘ ዜና፤ ትናንት ፈረንሳይና ስጳኝ ዉስጥ የተቀጣጠለዉ እሳት በፍጥነት እየተዛመተ ነዉ። ደቡብ ፈረንሳይ ዉስጥ አንዲት ሴት በቃጠሎው ሞተዋል፤ 12 ቤቶች፣ 12ሺ ሔክታር መሬት የሸፈነ ሰብልና ደን ዉድሟል።
ደቡባዊ ስጳኝ ታሪፋ በተባለች በሐገር ጎብኚዎች የምትዘወተር አካባቢን ያጋየዉ እሳት ደግሞ 1500 ሰዎችና 500 መኪኖችን ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሸሹ አስገድዷል።
አሜሪካ ሎስ ፓደሬስ የተባለዉ አካባቢ የተነሳዉ ቃጠሎም የአካባቢዉን ደን እያጋየ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
DW
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

