በአረርቲ ከተማ አስተዳደር አረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ላይ እየተሰራ ያለው ቤተክርስቲያን እየተጎበኘ ባለበት ሰዓት፣ ለፊኒሺንግ ሥራ የተረበረበው እንጨት ተደርምሶ በርካታ ምዕመናን ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።
እስካሁን ትክክለኛ የሟቾችና ተጎጂዎች ቁጥር አልታወቀም። አሁንም ሰዎችን ከተናደው ርብራብ የማውጣት ስራ እየተሰራ ነው።
የአረርቲ ከተማ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ፤ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑና ከእንጨት ርብራቡ ሥር ያልወጡ ሠዎች በመኖራቸው የጉዳት መጠኑን መገመት አስቸጋሪ እንደሆነ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጿል።
ከሆስፒታል በተረጋገጠው እስካሁን የ22 ሠዎች ሕይወት ማለፉን፣ በተጨማሪ 55 ሰዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አሳውቋል።
ለተጎጂዎች የመጀመሪያ ሕክምና በአንድ ሆስፒታል እና በ4 ጤና ጣቢያዎች እየተሠጠ ሲሆን፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሠባቸው 5 ተጎጂዎች ለተጨማሪ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል።
ተጎጂዎችን ለማትረፍ ኅብረተሠቡ ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ አሁንም ድረስ ከርብራቡ ሥር ያልወጡትን ዜጎች ሕይወት ለማትረፍና ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው።
Tikvah-
ቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና

