Wednesday, 29 October 2025 15:18

ኢትስዊች የመረጃ ማዕከሉን ከብሔራዊ ባንክ ወደ ዘመን ባንክ አዘዋወረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ኢትስዊች የመረጃ ማዕከሉን ከብሔራዊ ባንክ ወደ ዘመን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ማዘዋወሩን ገልጿል። ትናንት በአዲስ አበባ፣ ሸራተን አዲስ 12ኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዷል።
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትስዊች አክሲዮን ማሕበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ደስታ፣ የ1 ሺሕ ብር አክሲዮን የትርፍ ድርሻ ወደ ብር 486 ማደጉን ገልጸዋል። አክለውም፣ በተቋሙ አማካይነት ከ740 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን ጠቁመው፣ ይህ የገንዘብ ዝውውር ከ287 ሚሊዮን በላይ በሆነ ግብይት የተፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ከ577 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከአንድ የፋይናንስ ተቋም ወደ ሌላኛው በተደረገ የገንዘብ ማስተላለፍ የተዘዋወረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፣ ይህ ከአጠቃላይ የግብይት መጠን 128 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህሉን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።
አቶ ሰለሞን "የኩባንያው አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል ከ 2 ቢሊየን 500 ሚሊዮን ተሻግሯል" ያሉ ሲሆን፣ የኩባንያው ዓመታዊ ገቢ 2.2 ቢሊየን ብር መድረሱንም አስታውቀዋል። እንዲሁም ኩባንያው ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 1 ነጥብ 42 ቢሊየን ብር መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትስዊች ካከናወናቸው ዓበይት ክንውኖች መካከል፣ በብሔራዊ ባንክ ስር የነበረውን የመረጃ ማዕከል ወደ ዘመን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት እንዲዘዋወር ማድረጉ ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ተቋሙ በዋና መስሪያ ቤትነት የሚያገለግለውን ባለ12 ፎቅ ሕንጻ ለመግዛት መቻሉንም ጨምረው አስታውቀዋል።
በሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ባለቤትነት የሚተዳደረው ኢትስዊች አክሲዮን ማሕበር፤ በፋይናንስ ተቋማት፣ በአገር ውስጥ የክፍያ ስርዓት እና በብሔራዊ የክፍያ ስርዓት መካከል የእርስ በርስ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
 
 
Read 815 times