የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ በገንዘብ ምህንድስና ሊፈታ የማይችል የማምረት አቅም ማነስ ችግር ነው ሲሉ ታዋቂው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ክቡር ገና በቅርቡ ባወጡት ፅሁፍ ገለጹ። መንግስት የብርን ዋጋ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ፣ ድጎማዎችን በማንሳትና ጥብቅ የፋይናንስ ፖሊሲ በመከተል የአይ ኤም ኤፍ ፕሮግራምን መተግበር መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል ብሎ ተስፋ ቢያደርግም፣ ኢኮኖሚው ግን በቤተ ሙከራ የሚሰራ ሳይሆን በልበ ሙሉነት፣ በማበረታቻዎችና በጠንካራ ተቋማት ላይ የሚቆም ህያው ስርአት ነው ብለዋል። አሁን ላይ የሚታየው የውጭ ምንዛሬ ፍሰት መሻሻልና የጥቁር ገበያ ልዩነት መጥበብ በመንግስት ፖሊሲ ስኬት ሳይሆን፣ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ ወርቅና ቡና ያሉ ምርቶች ዋጋ በመጨመሩ የመጣ “እድለኛ አጋጣሚ” መሆኑንና እንዲህ አይነቱ ጊዜያዊ ገቢ ሲቀንስ እውነተኛው መዋቅራዊ ድክመት መጋለጡ እንደማይቀር ባለሙያው አስጠንቅቀዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የቻይናን የዕድገት ጉዞ እንደ ማወዳደሪያ ያነሱት ክቡር ገና፤ ቻይና የገንዘቧን ዋጋ ቀንሳ ዝም ብላ ወደ ውጭ የሚላክ ምርት እስኪበቅል አልጠበቀችም ብለዋል። ሀገሪቱ የምንዛሬ ተመኗን የመራችው በኢንዱስትሪ ስትራቴጂ፣ በጠንካራ ተቋማዊ ዲሲፕሊን፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ታግዛ እንደነበር አስታውሰዋል። ባለሀብቶች በቻይና የገበያ መዛባቶችን የታገሱት በሀገሪቱ የረጅም ጊዜ አቅጣጫ ላይ እምነት ስለነበራቸው እንደሆነና ፋብሪካዎች፣ ወደቦችና የኤሌክትሪክ አቅርቦት በተግባር ይገነቡ ስለነበር እንደሆነ አብራርተዋል። ቻይና የገበያ ዋጋን ማጠፍ የቻለችው ገበያው ቻይና ከስር ጠንካራ መሠረት እየገነባች መሆኑን ስላመነባት ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሁኔታ ፍጹም የተለየ ነው፤ ሀገሪቱ የገንዘብ ሊበራላይዜሽን (ነፃ ገበያ) ለመተግበር እየሞከረች ያለችው በውስጥ ግጭቶች፣ በመሰረተ ልማት መታነቅ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከፍተኛ በሆኑ የገቢ ምርቶች ጥገኝነት ውስጥ ሆና ነው። ባለሀብቶች የዋጋ ግሽበትን ወይም ቢሮክራሲን ሊታገሱ ቢችሉም፣ መንገዶች ክፍት መሆናቸውን፣ መብራት አስተማማኝ መሆኑን ወይም ግጭት ወደ ኢንዱስትሪ መንደሩ መቼ እንደሚስፋፋ ያለውን አለመረጋጋት ግን አይታገሱም። የማምረት አቅም በሌለበት ሁኔታ የገንዘብ ዋጋን ማርከስ ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ከማሳደግ ይልቅ፣ እንደ ነዳጅ፣ ማሽነሪ፣ መድሃኒትና ማዳበሪያ ያሉ አስፈላጊ የገቢ ምርቶች ዋጋን በማናር የኑሮ ውድነቱንና የምርት ወጪን በእጅጉ እንደሚጨምረው አቶ ክቡር ገና አብራርተዋል።
በመጨረሻም ኢኮኖሚስቱ ክቡር ገና ባቀረቡት ማጠቃለያ፤ የኢትዮጵያ ዋነኛ ፈተና የገንዘብ ፖሊሲ ሳይሆን “የልማት ሞዴሉ ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ ነው ብለዋል። ሀገሪቱ “ማረጋጋትና ነፃ ገበያ መፍጠር” በሚል አስተሳሰብ ብቻ ከተመራች፣ አንዱን ቀውስ አረጋግታ ሌላው ውስጥ የምትገባ የዘላለም ማስተካከያ ሰለባ ሆና ትቀራለች። ፋብሪካዎች በስፓሬድሺት ስሌት አይገነቡም ያሉት ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት የማክሮ ኢኮኖሚ ማስተካከያ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂካዊ ግልጽነት፣ አስተማማኝ የትራንስፖርት ኮሪደሮች፣ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ስብስብና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ መረጋጋት ነው ብለዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

