የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጥምረትን በመወከል በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድድር የቀረቡትን የኢሕአፓ አመራር ይሳቅ ወልዳይን ራስን ከእጩነት የማግለል ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል። ቦርዱ ለውሳኔው በምክንያትነት የጠቀሰው፣ ከእጩነት የመልቀቅ ጥያቄ የሚስተናገደው እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ታትመው አገር ውስጥ በመግባታቸው ለምርጫው 12 ቀናት ብቻ ሲቀሩ የቀረበው ጥያቄ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ነው። ይሳቅ ወልዳይ ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉት ኢሕአፓም ሆነ ጥምረቱ ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆን ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ ዕጩው ይሳቅ ወልዳይ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበሉና በእጩነትም ሆነ በተወዳዳሪነት እንደማይቀጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በእጩነት መቅረብ "መብት እንጂ ግዴታ እንዳልሆነ" የገለጹት ይሳቅ፣ ለቦርዱ ያቀረቡት ማሳወቂያ እንጂ ጥያቄ አለመሆኑንና ቦርዱ የጠቀሰው የጊዜ ገደብ ፓርቲዎች ሌላ እጩ ለመተካት በሚፈልጉበት ጊዜ ብቻ የሚሠራ መሆኑን ተከራክረዋል። የምርጫ አዋጁ ራስን ለማግለል የጊዜ ገደብ ባያስቀምጥም እጩን ለመተካት ግን ከአንድ ወር በፊት መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ ይሳቅ ግን የድምጽ መስጫ ወረቀት ቢታተም እንኳ "አልሳተፍም" ያሉ እጩዎች ድምፅ ዋጋ እንደማይኖረው (null and void) ተቆጥሮ ውድድሩ ሊቀጥል እንጂ ማንም በግድ እንዲወዳደር ሊያስገድደው እንደማይችል አቋማቸውን አስታውቀዋል።

