የፌዴራል ዳኞች አሥተዳደር ጉባኤ፣ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የውርስ ችሎት ተመድበው ሲሰሩ የነበሩትን ረዳት ዳኛ ታምሩ አያሌውን "ከባድ የስነ ምግባር ጥሠት" ፈጽመዋል በማለት ከዳኝነት ሥራቸው አሰናብቷል። ረዳት ዳኛው በእጃቸው ላይ ከነበረ የውርስ መዝገብ ጋር በተያያዘ ከተከራካሪ ወገኖች ጋር ህገ-ወጥ ግንኙነት በመፍጠር "ተገቢ ያልሆነ ጥቅም" መጠየቃቸውን ጉባኤው በይፋ ገልጧል። በተጨማሪም የፍርድ ቤት ሚስጢርና መረጃ የሆኑ የባንክ ምላሾችን አስቀድመው ለተከራካሪ ወገን ጠበቃ አጋርተዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ረዳት ዳኛ ታምሩ አያሌው የቀረበባቸውን ይህንን ከባድ የሙስና እና የስነ-ምግባር ክስ እንዲከላከሉና ምላሽ እንዲሠጡ ባለፈው ሐምሌ 2017 ዓ.ም በጉባኤው በኩል መጥሪያ ቢሠጣቸውም ሊቀርቡና ሊከላከሉ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የአሥተዳደር ጉባኤው ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ከሥራ ገበታቸው እንዲሠናበቱ ጥብቅ ውሳኔ አሳልፏል።

