Tuesday, 26 May 2026 08:32

ያለደመወዝ የኢትዮጵያ ሕፃናትን ሕይወት የሚታደጉት አሜሪካዊቷ ሐኪም

Written by 
Rate this item
(0 votes)
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በሚገኘው ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉት አሜሪካዊቷ የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሚሼል ዬትስ፣ አስደናቂ የሕክምና ተዓምራትን እያደረጉ ይገኛሉ። በቅርቡ እንኳ ሳይንሳዊ ግምቶችን በመቀየር፣ ገና በማለዳዋ ተወልዳ የሰውነት ክብደቷ 700 ግራም ብቻ የነበረችን ሕፃን በከፍተኛ ክትትልና እንክብካቤ ከሞት አትርፈው ለእናቷ እቅፍ አብቅተዋል። ላለፉት 12 ዓመታት በሆስፒታሉ ያገለገሉት ዶ/ር ሚሼል፣ ከሶስት ልጆቻቸው; ሁለቱን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የወለዱ ሲሆን፣ ከትውልድ ሀገራቸው ርቀው እናቶችና ሕፃናትን በቅንነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
የሚያስደንቀው ነገር፣ ዶ/ር ሚሼልን ጨምሮ በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የሚያገለግሉ ሁሉም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ለሚያበረክቱት የላቀ አገልግሎት ከሆስፒታሉም ሆነ ከሀገር ምንም ዓይነት ደመወዝ ወይም ክፍያ አይቀበሉም። የዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚደገፈው በትውልድ ሀገራቸው ከሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከአብያተ ክርስቲያናትና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚላክላቸው የገንዘብ ድጋፍ ነው። ከቤተሰብ መራቅና ማኅበራዊ ኩነቶች ላይ አለመገኘት ከባድ ቢሆንም፣ የመክፈል አቅም የሌላቸውን ወገኖች ማከምና የሕፃናትን መዳን ማየት ሁሉንም ድካም የሚያስረሳ ትልቅ በረከት መሆኑን ሐኪሟ በታላቅ እርካታ ይገልጻሉ።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤፍሬም ገብረሥላሴ እንዳብራሩት፣ እንደ ዶ/ር ሚሼል ያሉ ቅን ሰዎችን ማሰባሰብ መቻሉ ሆስፒታሉ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ሆስፒታሉ ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ፣ በየዓመቱ እስከ 40 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ አቅመ ደካማ ታካሚዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ይህ ዓይነቱ ግብረሰናይ ተግባር የብዙ ምስኪኖችን ተስፋ ከማለምለሙም በላይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ታላቅ የሰብአዊነት አርአያ ነው።
EBC-
Read 3016 times