1) እኛ ሰላም ያጣነው እንዲሁ በድንገት አይደለም፤ ሆን ብለን ሰርተንበት (ለፍተንበት) እንጂ። ዛሬም ለመሳሪያ ይዘፈናል። ዛሬም የገዳይ ልጅ ነኝ ይባላል። ፉከራ አለ። እኛ ከእንትና የበለጥን ጀግኖች ነን ይባላል። ዛሬም ልጆች በጦርነት ድምፅ መሃል ያድጋሉ።
ከዛ፣ ምን መዓት መጣብን?
2) በቅርብ ታሪካችን ውስጥ ሰዎች የሰሩት ትልቁ ስህተት መንግስትን እንደ ጓደኛ ማሰባቸው ነበር። መንግስት መቼም ቢሆን ያንተ ጓደኛ አይደለም። መንግስትን መግራት አትችልም። መንግስት የምትጠላቸውን ሰዎች ሲያጠቃ አንተም አብረኸው ልታጠቃ ትችላለህ፤ ነገር ግን መንግስት አድኖ በልቶ ሲጨርስ፣ ወደ እሱ በጣም ተቃርቦ የሚገኘው ማን እንደሆነ ገምት?
#NoMore ብለህ ጮኸህ፣ ድምፅህ ሰልሎ ወደ ቤትህ ልትገባ ስትል፣ A little more ብሎ ለእራት ያውልሃል። መንግስት ውለታ አይቆጥርም። እነዚህ ደግሞ የባሱት ናቸው ስንል፣ አብረን ያጠናከርናትና በር የከፈትንላት (Enable ያደረግናት) ዓመፅ እንዳለችም ማስታወስ ደግ ነው። ለነገ ይጠቅም ይሆናል።
3) ወላጆቻቸው ሕይወታቸውን ኦርጋናይዝ ሊያደርጉ ሲሞክሩ የሚበሳጩ (ነፃነት የሚፈልጉ) ሰዎች፣ ለምን የጓደኞቻቸው ሕይወት ላይ 60 በመቶ አክሲዮን እንዳላቸው ይሰማቸዋል?
ተቃርኖ የዓለም ገፅ ስለሆነ ወይስ ኑሯችንን በተለየ መልኩ እየደገምን የምንኖር ሆነን?
4) "እያንዳንዱ በራሱ መንገድ ይኑር" (To each their own) ጥሩ አባባል ነው።
የሕይወት ትርጉም በእጃችን የለም። እንደ እቃ ሸመታ የተመቸንን ነው የምንመርጠው። በዛ ውስጥ የዳኝነት ወንበርን ተሻምተው የሚገዙ ብዙ አሉ። አትፍረድ የሚለውን ትዕዛዝ ለአማኞች ትተን፣ ስለሕይወት ውስብስብነት፣ ስለሰዎችም መልከ ብዙነት፣ እሱንም ስለመቀበል፣ "ራስህ ሁን፣ ሌሎችንም እንዲሆኑ ፍቀድ" (Be and let others be) ለሚለው ሐረግም አሜን ብንል!
5) ድል ለአርሰናል! እና ለሰፊው ሕዝብ ፡)
Agegeheu Asegid-
ከዝግጅት ክፍሉ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ መጠነኛ አርትኦት ተደርጎበታል፡፡ ኦሪጂናል ጽሁፉን እንደወረደ ከጸሃፊው ፌስቡክ ገጽ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

