የአርሰናልን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ድል ለመዘከር "WE CHAMPIONS 2026" የተሰኘ ታሪካዊ የእግር ኳስና የመዝናኛ ፌስቲቫል የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊካሄድ ነው። በቫርደስ ኢንተርቴይመንት አዘጋጅነትና በአዋሽ ባንክ (አዋሽብር ፕሮ) ዋና ስፖንሰርነት የሚከናወነው ይህ ዝግጅት፣ ከ30 ሺህ በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን፣ ዓለም አቀፍ ሌጀንዶችንና የሚዲያ ባለሙያዎችን በአንድ ላይ የሚያሰባስብ ታላቅ መድረክ ነው። ዝግጅቱ የሀገራችንን ባህል፣ እንግዳ ተቀባይነትና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
በዚህ ደማቅ መርሃ ግብር ላይ የቀድሞው የአርሰናል እና የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ተጫዋች ኤማኑኤል ኢቡዌ በልዩ እንግድነት የሚገኝ ሲሆን፣ ታዋቂው የለንደኑ "Arsenal Fan TV" (AFTV) ተወካዮችም በቦታው ይገኛሉ። ዝግጅቱ በአጠቃላይ በAFTV የዩቲዩብ ቻናልና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ በመሆኑ የሀገራችንን ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በዕለቱ መድረኩን የሚያደምቁ ከ10 በላይ ታዋቂና ወጣት ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን የተሰለፉ ሲሆን፤ ታደለ ሮባ፣ ልጅ ሚካኤል (ፋፍ)፣ ሳሚ ዳን፣ አስጌ ዴንዳሾ፣ ራሄል ጌቱ፣ ሮቤል ሚዲቅሳ፣ ዮ ማሪዮስ፣ ሚክ ዋን፣ አማኑኤል የማነ፣ አዲስ ሙላት እንዲሁም እውቁ የአፍሮቢትስ ሙዚቃ ተጫዋች ፍራንኪዬ ዲ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ለፌስቲቫሉ መግቢያ የሚሆን ትኬትን በአዋሽ ብር ፕሮ፣ በአዋሽ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በስታዲየም በሚገኙ ጊዜያዊ የትኬት ጣቢያዎች መግዛት እንደሚቻል አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

