የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ የመድኃኒት አጠቃቀም ቁጥጥር መመሪያ (ቁጥር 1138/2026) አውጥቷል። ይህ መመሪያ ፋርማሲዎች ያለ ሐኪም ትክክለኛ ማዘዣ ማንኛውንም የፀረ-ተህዋሲያን (አንቲባዮቲክስ) እና በሕግ የተገደቡ መድኃኒቶችን ለደንበኞች እንዳይሸጡ በጥብቅ ይከለክላል። በተጨማሪም ሆስፒታሎች የክትትል ኮሚቴ እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ሐኪሞች በአንድ ወረቀት ላይ ከሦስት መድኃኒት በላይ እንዳያዙና የአንቲባዮቲክስ ማዘዣዎችም ከ7 ቀናት በላይ እንዳያገለግሉ ገደብ ጥሏል።
ይህ አሠራር ዜጎች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት በመውሰድ ለከፍተኛ የመድኃኒት መላመድ (Drug Resistance) አደጋ እንዳይጋለጡና ትክክለኛውን ሕክምና በትክክለኛው መጠን እንዲያገኙ ለማስቻል የተዘረጋ ነው። ፋርማሲስቶች መድኃኒት ከመስጠታቸው በፊት ጥራቱንና የአገልግሎት ማጠናቀቂያ ቀኑን የመፈተሽ እንዲሁም ለታካሚው በቂ የምክር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው። የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ይህንን አዲስ ሕግ በሚጥሱ ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ እስከ ሥራ ፈቃድ መሰረዝ የሚደርስ ጥብቅ ቅጣት እንደሚጣል አስጠንቅቀዋል።

