አንዳንዶች የኦርቶዶክሳዊያንን ሞት በሰሙ ቁጥር ጣታቸውን ቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ ሲጠቁሙ አያለሁ፡፡ በእኔ ዕይታ እነዚህ ወገኖች ሁለት ስህተት እየሰሩ ነው፡፡ ቀዳሚው ቅዱስ ሲኖዶሱ ለምን ዝም ይላል ሲሉ ከዚህ ቀደም ሲታገል የኖረ ከማስመሰላቸው ይያያዛል፡፡
አቡነ ገብርኤል "የማውቀውን እናገራለሁ" በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደነገሩን፤ የዘመናችን መራራ እውነት ኢትዮጵያዊያን ኦርቶዶክሶች እውነተኛ ሲኖዶስ የሌለን እጓለ ሙዑታን መሆናችን ነው፡፡
ስለሆነም ሲኖዶሱ ለሚጠብቃቸው በጎች ጥሩ እረኛ አልሆነም ፤ በጎቹ ሲገደሉ ለምን ዝም ይላል፤ የቤ/ክ ቴሌቭዥን ድምጹ ጠፋ ወዘተ ብለው የሚተቹ ሰዎችን ሳይ ቢያንስ እረኛ አለ ብለው በማመናቸው እገረማለሁ፡፡ የሟቾችንም ሀዘን በተለመደና የመነቸከ ወቀሳ ውስጥ እያቀለሉት እንዳይሆን እሰጋለሁ::
ዛሬ የዘመን ምጸት ሆነና ኦርቶዶክሳዊያን እየታገሉ ያሉት ከሚያሳድዷቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳቸውም አባቶች ጋር ነው፡፡ ሩቅ ሳንሔድ ከወር በፊት የምስራቅ ወለጋ አገረ ስብከት የፃፈውን ደብዳቤ እናስታውስ፡፡ ይህ ደብዳቤ በጨዋ ቋንቋ የአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል የተረከቡትን በወርቅ የተለበጠ ጥንታዊ ጽላት ሰውረዋል አልያም ሰርቀዋል ሲል ይከሳል፡፡ የሚያስደነግጠው ተራው ምዕመንና አባቶች ቦታ መቀያየራችን ብቻ አይመስልም፡፡ ትልቁ ዜና፤ ጥያቄው የደረሰው ቅዱስ ሲኖዶስ የሌባ እናት ልጇን አታማም ብሎ ነገሩን አለባብሶ መያዙ ነው፡፡
እንደ መውጫ
የቤተ-ክርስቲያን አስተምሮ መልከ ብዙ ነው፡፡ ቀነኗና ሕግጋቷም ጥልቅ ነው፡፡ ይህም ሆኖ አባቶችን አትናገሩ እያሉ ሕግ እያጣቀሱ ሊያስተምሩ የሚሞክሩ ሰዎች አይገቡኝም፡፡ ወዳጄ፤ አባቶች ከቤተ-ክርስቲያን በላይ አይደሉም፡፡ ቤተ-ክርስቲያን የምዕመናን ሕብረት ናት፡፡ ቤተ-ክርስቲያን ዐቢይ መልኳ ሰው ነው፡፡ ሰው ሲታረድ እየሞተች ያለችው ቤተ-ክርስቲያን ናት፡፡ አንዳንድ የቤተ-ክሕነት ጥቅም ተጋሪዎች ግን ቤተ-ክርስቲያን ትሙት አባቶች ግን ይዳኑ ይሉናል፡፡ እንዴት ሆኖ?
ሌሎችማ ጭራሽ በከፋው ጊዜ አንገታቸውን እንደ ሰጎን ቀብረው ግርግሩ ሲያልፍ አባቶች ላይ አፍ የሚከፍት ትውልድ መጣ ብለው ይዘባበቱብናል፡፡ እውነታችሁን ነው?
በነገራችን ላይ ከመቶ በላይ ሰው አጠመቅን የሚሉን የመስቀል አደባባይ ሐዋርያትና ተቋማት አዕላፍት ሲሞቱ የት እየተደበቁ ነው ሲያልፍ ከፊት የሚመጡት? ደግሞስ ሕንፃ ቤተ-ክርስትያን ለማሰራት በየቦታው ወንበር ዘርግተው ራሳቸው ቀድመው በሀብት የሰሩትስ የትኛው ጎሬ ውስጥ ተወሽቀው ነው ሰሞኑን የማይታዩት? የደጀሰላም በር ዘግተው ለሰው ነፍስ ድኅነት እንሰራለን የሚሉት የጉዞ ማኅበራትስ ምን ዋጣቸው?
በማእረግ ጌታቸው-

